1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በአፋር ክልል የጭፍራ ወረዳ ለሁለት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ኤሌክትሪክ እንደተቋረጠ ነው»ነዋሪዎች

ዓርብ፣ ነሐሴ 3 2016

ከጦርነቱ በኋላ የኤሌክትሪክ መስመሮቹ መጠገናቸውን የሚያነሱት አስተያየት ሰጪው ነዋሪ መስመሮቹ ዳግም ቢዘረጉም የኃይል አቅርቦቱ ግን አለመቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጭፍራ ዲስትሪክት ዋና ሃላፊ እንደሚሉት የችግሩ መንስኤ የኃይል አቅርቦት እጥረት ቢሆንም በጥቂት ቀናት አገለግሎቱን ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4jIZj
በአፋር ጭፍራ ከጦርነቱ በኋላ የተተከለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ
በአፋር ጭፍራ ከጦርነቱ በኋላ የተተከለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ምስል Seyoum Getu/DW

«በአፋር ክልል የጭፍራ ወረዳ ለሁለት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ኤሌክትሪክ እንደተቋረጠ ነው»ነዋሪዎች

በአፋር ክልል አውሲረሱ ወይም ዞን አንድ ጭፍራ ወረዳ ወሃማ ከተማ በሰሜን ኢትዮጵያው የትግራይ ጦርነት ምክንያት የተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሁለት ዓመታት ለሚጠጋው ጊዜም አለመመለሱን ነዋሪዎች ተናገሩ። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የአከባቢው ነዋሪዎች በአከባቢው በተፈጸመ የኤሌክትሪክ ጥገና በበርካታ ስፍራዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቀጠሉን ገልጸዋል። ሆኖም በነሱ አከባቢ እስካሁን መብራት ባለመመለሱ የለመዱትን አገልግሎት በማስቀረት ለእንግልት እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያው አስከፊ ጦርነት ወቅት ከአከባቢያቸው የተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት እስካሁንም አለመመለሱን ገልጸው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአፋር ክልል ፣ዞን አንድ ጭፍራ ወረዳ ወሃማ ከተማ ነዋሪ፤ የችግሩ አለመፈታት አሳስቦናል ይላሉ፡፡ “ከሰሜኑ ጦርነት መከሰት በኋላ በወሃማ እና አከባቢው ምንም አይነት የመብራት አገልግሎት አላገኘንም” ብለዋልም አስተያየት ሰጪው፡፡
ከጦርነቱ መቋጫ በኋላ የኤሌክትሪክ መስመሮቹ መጠገናቸውን የሚያነሱት አስተያየት ሰጪው ነዋሪ መስመሮቹ ዳግም ቢዘረጉም የኃይል አቅርቦቱ ግን አለመቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ “ጥገናው ተፈጽሞ መስመሩ ተዘርግቷል፡፡ ግን ኃይል የለውም፡፡ ምንም አይነት መብራት አልተለቀቀም” ነው ያሉት፡፡ ከጦርነቱ መቋጫ በኋላ ሌሎች አከባቢዎች የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ሲፋጠን በአከባቢያቸው ግን የመስመር መልሶ ጥገና ብቻ ተፈጽሞ ምንም ዓይነት የኃይል አቅርቦት አለመቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት 

ጭፍራ እና ካሳጊታ በተባሉ የአፋር ክልል ከተሞች መካከል በምትገኘው በዘህች የወሃማ ከተማ ለዓመታት የተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን አስተጓጉሏል የሚሉት ሌላኛው ነዋሪ፤ “በጦርነቱ መብራት ተቋርጦባቸው የነበሩ ሌሎች ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወደመሆን ስመለሱ እኛ ግን እስካሁን ከአገልግሎቱ ተቆራርጠናል፡፡ በዚህም ከጤና አገልግሎት እስከ ስልክ ቻርጅ ማድረጊያ መጥፋት በብዙ እንቸገራለን” ብለዋልም፡፡
ሌላም  አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ“ከ15 ሺህ አባወራዎች በላይ በከተማዋ የመብራ ተጠቃሚ ነበርን፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ግን የወፍጮ፣ ቴሌኮሚዩኒኬሽን እና የውሃ አቅርቦት ተስተጓጉሎብናል” ነው ያሉት፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም ሰሚ ማጣታቸውንም ነዋሪዎቹ አክለው አንስተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአፋር ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጭፍራ ደንበኞች አገልግሎት
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአፋር ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጭፍራ ደንበኞች አገልግሎት ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቅርንጫፍ ምላሽ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጭፍራ ዲስትሪክት ዋና ስራ አስከያጅ አቶ ተስፋማሪያም ኪሮስ እንደሚሉት ለአገልግለሎቱ ተቋርጦ መቆየት ዋናው መንስኤ የኃይል አቅርቦት እጥረት ቢሆንም በጥቂት ቀናት አገለግሎቱን ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ስርቆት እና ውድመት ደግሞ ከጦርነትም በከፋ አከባቢውን ጎድቶታል ነው ያሉት፡፡“አቅርቦት ስላልነበረ ነው፡፡ አሁን ግን በዚህ ሁለት-ሶስት ቀናት አገልግሎቱን መልሰው ያገኛሉ፡፡ ሌላው ችግር አብዛኛው ማህበረሰብ ከ300 በላይ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ምሰሶዎች በመፍለጥ እና ሽቦና ብረቶችን አውጥተው በመጠቀምና በመሸጥ ላልተገባ ጥቅም በማዋላቸው በመንግስት ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው አገልግሎቱ እንዲዘገይ ያደረገው ሌላው ጉዳይ ነው” ብለውታል፡፡

በአፋር የኤሌክትሪክ መስመር ቢዘረጋም አገልግሎቱ የለም
በአፋር የኤሌክትሪክ መስመር ቢዘረጋም አገልግሎቱ የለምምስል Seyoum Getu/DW

በሰሜን ያገረሸው ውጊያ በሌሎች አከባቢዎች የሚኖረው አንድምታይህም ተቋሙን ላልተፈለገ ወጪ ዳርጎታል ያሉት ኃላፊው የሆነ ሆኖ የእቃ ግዥ በመፈጸም በሚቀጥሉት ሁለት ሶስት ቀናት ውስጥ የኃይል አቅርቦቱን ለመፈጸም ዝግጅት ተጠናቋል ነው ያሉት፡፡
የአፋር ክልል በሰሜን ኢትዮጵያው የሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት አሌክትሪክን ጨምሮ መሰረተ ልማቱ ክፉኛ ከተጎዳባቸው አከባቢዎች ተጠቃሽ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ስዩም ጌቱ 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ