በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሰው የአብዴን አቤቱታ
ሐሙስ፣ ሰኔ 3 2013የአብዴን ሊቀመንበር አቶ ሀሰን መሀመድ ሰሞኑን ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት በአፋር ብሔራዊ ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ ያሉ የምርጫ አስፈፃሚዎች በልዩ ወረዳው ገዢ ፓርቲ ግፊት ከአካባቢ በለቀቁ፣ በሕይወት በሌሉና ዕድሜያቸው ለምርጫ ባልደረሱ ሕጻናት ስም የምርጫ ካርድም እንዲወጣ አድርገዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክተው 10 ገፅ ማመልከቻ ግንቦት 18/2013 ዓ ም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቢያስገቡም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙ ነው አቶ ሀሰን የተናገሩት። ሁኔታው እልባት ካላገኘ ከምርጫው ለመውጣት እንደሚገደዱም አመልክተዋል። በአፋር ብሔራዊ ክልል የአርጎባ ልዩ ወረዳ ገዢ ፓርቲ፣ የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አህዴድ) ሊቀመንበር አቶ አሊ ዘይኑ ተጠይቀው በጥቅሉ ድርጊቱ እንዳልተፈፀመና ዝርዝርና የተደራጀ ምላሽ የሚሰጡት ግን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሆነ በስልክ አስረድተዋል። የአፋር በየሄራዊ ክልል ምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ ጣሀ አሊ የቅሬታ ሪፖርቱ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ የአገር አቀፍ ፖለካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አብዱልቃድር አደም በበኩላቸው አብዴን ያቀረበው ክስ ከመራጮች ጋር የተያያዘ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ጉዳዩን በዋናነት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚፈታው መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ አርጎባ ብሔረሰብ በአፋርና በአማራ ክልሎች በሁለት ልዩ ወረዳዎች ይተዳደራል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ