የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የፍርድ ሂደት
ሐሙስ፣ ግንቦት 12 2013
ዛሬ በአዲስ አበባ ያስቻለው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የህገ-መንግስትና ፀረ-ሽብር ወንጀል ችሎት በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የክስ ሂደት ላይ የግራ ቀኝ የክርክር ማቆሚያ ሀሳብን ለመስማት በሰየመው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ እና 2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ ከማረሚያ ቤት እንዲሁም ሶስተኛ ተከሳሽ አብዲ ዓለማየሁ በዋስ ተይዘው ቀርበዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ተከሳሾች ተጠርጥረው በተከሰሱበት እና በተመሰከረባቸው ወንጀል ላይ እራሳቸውን እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ በፈቀደው መሰረት ሶስቱም ተከሳሾች በሁለት ሁለት ተከላካይ ምስክሮች ወንጀሉን አልፈጸምንም፤ በእለቱም ውለን ያደርንበት ስፍራ በነዚህ ምስክሮቻችን ይታወቅልናል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
ይሁንና ከሳሽ አቃቤ ህግ ባቀረበው የክርክር ማቆሚያ ሃሳብ የይደመጥልኝ ጥያቄ መሰረት ፍርድ ቤቱ ዛሬ የግራ ቀኝ የክርክር ማቆሚያ ሃሳቦችን ለማድመት ተሰይሟል፡፡ በዚህም መሰረት አቃቤ ህግ ተከሳሾች ለፖለቲካ ጥቅም በሚል ተልዕኮ ወስደው ታዋቂ ሰዎችን ለመግደል መንቀሳቀሳቸውን፤ ምንም እንኳን የኋላ ኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም ቢሉም ሸሽተው ከተደበቁበት መያዛቸው ይታወቅልኝ ብሏል፡፡
ተከሳሾች ሟች አርቲስት ሓጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለበት አካባቢ የሚኖሩና ከዚያው አከባቢ መያዛቸውን፤ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸውም በወቅቱ ስለማመናቸው፤ እንዲሁም አርቲስቱ ተገድሎበታል የተባለው መሳሪያ በአንደኛ ተከሳሽ ወንድም ከተቀበረበት ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ ከቀለሃው ጋር ተመሳክሮ በፎረን ሲክ ምርመራ መረጋገጡም ይያዝልኝ ብሏል አቃቤ ህግ በክርክሩ፡፡
ሌላው በተንቀሳቃሽ ምስል እና በምስል ተሰንዶ ለፍርድ ቤት የቀረበው የሰነድ ማስረጃ ተከሳሾች ሟችን ለምን፣ እንዴት እና የት እንደገደሉ በወቅቱ ማብራራታቸውንም በክርክር ማቆሚያ ሃሳቡ አካቷል አቃቤህግ፡፡
አቃቤ ህግ በዚሁ በቀጠለው የክርክር ማቆሚያ ሃሳቡ 1ኛ ተከሳሽ ሃምሌ አንድ ቀን 2012 ዓ.ም ወዲያ በተያዘው አጋጣሚ ወንጀሉን ስለመፈጸሙ በአማብራራት እራሱንም ለማጥፋት ማሰቡን ከገለጸ በኋላ በቅርቡ በችሎት ፊት ወንጀሉን በመካድ ተደብድቤ በግዴታ የተናገርኩት ነው ማለቱ ተቀባይነት የለውም ብሏልም፡፡
ለዚህም እንደማሳመኛ ሃሳብ ያቀረበው ተጠርጣሪው ሃምሌ አንድ ተይዞ ሀምሌ 03፣ 07 እና 08 ያለምንም የአካል ጉዳት ፍርድ ቤት ቀርቦ መዳኘቱ፣ በተያዘበት አጋጣሚና ሰሞንም በግልጽ በህዝብ ፊት ሲሰንቀሳቀስ መታየቱ እንዲሁም በቅርቡ እንኳ ተከሳሹ ለፍርድ ቤት ክፉኛ መደብደቡን ቢገልጽም ችሎቱ የጠየቀውን ጠባሳ ለማሳየት አለመቻሉ ይያዝልኝ ሲልም አክሏል፡፡
የዚሁ ተከሳሽ ተከላካይ ምስክሮች በዚያ ወንጀሉ በተፈጸመ እለት ምሽት ተከሳሹ ቤት እንደነበር በአንድ ቃል ቢመሰክሩም ለቀረበላቸው መስቀለኛ ጥያቄ እርሰበርስ የሚጋጩ ጀሃሳቦችን ሰጥተዋልም ብሏል፡፡
በመሆኑም አንደኛ ተከሳሽ የተከሰሰበት ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ ሶስትን በመተላለፍ ወንጀል ፈጽሟል በተባለው መሰረት የቀረቡበት ማስረጃዎች በቂ በመሆናቸው ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቋል አቃቤ ህግ በክርክር ማቆሚያ ቃሉ፡፡
በግድያ ወንጀሉ በተባባሪነት ተሳትፏል ሲል የከሰሳቸው 2ኛ እና ሶስተኛ ተከሳሾችንም በተመለከተ ዐቃቤ ህግ ተከሳሾቹ በወቅቱ ከሸሹበት ስለመያዛቸው፣ ምንም እንኳ ተከሳሾቹ ክሱን ቢያስተባብሉም ተከላካይ ምስክሮቻቸው በምስክር አሰጣጥ ሂደቱ መስቀለኛ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ለመመለስ እምብተኝነት ማሳየታቸው እና ተመሳሳይነት ያልነበራቸው ምስክርነትም ጭምር መስጠታቸው ግንዛቤ ይወሰድበት ብሏል፡፡
በዚሁ መሰረትም ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ ከ1ኛ ተከሳሽ ጥላዬ ያሚ ጋር “እንዝረፍ” በሚል የቀረበለት የዝርፊያ ወንጀል ለመፈጸም ተስማምቶ በወንጀሉ የተሳተፈ በመሆኑ በ1996 በወጣው የወንጀል ህግ 541 መሰረት ውሳኔ እንዲፀናበት እንዲሁም ወንጀሉን አይቶ ለፍትህ አካላቱ ለማሳወቅ አልቻለም የተባለው ሶስተኛ ተከሳሽ አብዲ ዓለማየሁ በተከሰሰበት 443/1 እንዲወሰንበት ሲል ጠይቋል፡፡
የተከሳሾች ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው የክርክር ማቆሚያ ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ በፍርድ ቤቱ ተጠይቀው በጽሁፍ ማቅረብ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ተከላካይ ጠበቆቹ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ክርክሩን በጽሁፍ እንዲያቀርቡ በማዘዝ፤ ክርክሩ የመዝገቡ አካል ሆኖ እንደሚያያዝ አሳውቋል፡፡ በዚሁ መሰረትም መዝገቡን መርምሮ በተከሳሾች ላይ ፍርድ ለመስጠ ፍ/ቤቱ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ችሎቱ ከዚህ ቀደም በሰጠው ብይን አንደኛ ተከሳሽ ወንጀሉ የተፈጸመበትን ሂደት ለፖሊስ ያስረዳበት የድምጽና ምስል ማስረጃ፣ አርቲስቱ የተገደለበት ሽጉጥ ከዚሁ ከአነድኛ ተከሳሽ ቤት መገኘቱና በፎረንሲክ ተረጋግጧል ማለቱ አይዘነጋም፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ