1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል: ጭምብል ተጠቃሚው ከ 5 % በታች ነው ተባለ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 23 2013

በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም ከ5 ከመቶ በታች እንደሆነ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውወቀ። የመከላከያ ክትባት የሚወስዱ ወገኖች ቁጥርም አነስተኛ ነው ተብሏል። የሀይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸው ክትባት እንዲወስዱ መክረዋል። 

https://p.dw.com/p/3spoX
Covid-19-Graffitis | Äthiopien
ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአማራ ክልል

የኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን ከገባ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። የክልሉ ጤና ቢሮ እንዳመለከተው በዚህ ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል ብቻ ከ10 ሺህ 353 ወገኖች በቫይረሱ ሲያዙ 239 ደግሞ ህወታቸው አልፏል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታሪኩ በላቸው ሰሞኑን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ህብረተሰቡ በእጅጉ የተዘናጋ በመሆኑ በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቀን ቀን እየጨመረ ነው፡፡በተለይ ቀደም ባሉት ጊዚያት በተደረገ ጥናት በአማራ ክልል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም፣ እጅን መታጠብና መራራቅ የተባሉ የመከላከያ መንገዶችን የሚጠቀመው የክልሉ ነዋሪ ከ12 ከመቶ እንደማይበልጥ አቶ ታሪኩ ተናግረዋል፡፡ መዘናጋቱ አሁንም መቀጠሉንና የመከላከያ መንገዱን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ወደ 5 ከመቶ መውረዱን ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

ክትባትን በተመለከተም በሚነዙ የተሳሳቱ ወሬዎች መከተብ ከሚገባቸው ውስጥ 53 ከመቶ የሚሆኑት መከተብ አልቻሉም ብለዋል፡፡ ይህንን የተዛባ አመለካከት ለመመለስ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በእርዳታ ያመጣነውን መድኃኒት ባግባቡ መጠቀም ካልቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚበላሽና ተጨማሪ የእርዳታ ክትባት ለማግኘትም ተፅዕኖ ስለሚኖረው ህብረተሰቡ ክትባቱን እንዲወስድ መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የባሕር ዳርና ደሴ ሀገረሰብከት ጳጳስ አቡነ ልሳነክርስቶስ ማቲዎስ ክትባቱን መውሰዳቸውንና ምዕመኑ የሀኪሞችን ምክር በመስማትና ለአሉባልታ ቦታ ባለመስጠት ክትባቱን እንዲወስድ ጠይቀዋል።

ከመካነየሱስ ቤተክርስቲያን መጋቢ እሱባለው ጌታቸው ክትባቱ ከሐይማኖት ጋር የሚገናኘው ምንም ነገር ባለመኖሩ ተከታዮቻቸው እንዲከተቡ አሳስበዋል፡፡
ሰሞኑን በአማራ ክልል የሚገኙ የ6 ሐይማኖት ተቋማት አመራሮች አስተሪካ ዜንካ የተባለውን የኮቪድ 19 ክትባት ወስደዋል፡፡ 

ዓለምነው መኮንን
ልደት አበበ