1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የተከሰተ ውኃ ሙላት ከፍተኛ ጉዳት አስከተለ

ሰኞ፣ መስከረም 11 2013

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ፣ ደራ፣ ሊሞከምከም ወረዳዎችና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በሚገኙ አንዳንድ ቀበሌዎች የጣና ሐይቅ ከመጠን በላይ ሞልቶ ወደኃላ በመመለሱ፣ የእርሻ ማሳዎች፣ መኖሪያ ቤቶችና እንስሳት በከፍተኛ ሁኔታ በውሀ መጥለቅለቃቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እየገለፁ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/3incb
Äthiopien Tana See
ምስል DW/Y. G/Egziabhare

15ሺህ አርሶአደሮች ተፈናቅለዋል፣ 9ሺህ ሄክታር የእርሻ ማሳ በውኃ ተጥለቅልቋል

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ፣ ደራ፣ ሊሞከምከም ወረዳዎችና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በሚገኙ አንዳንድ ቀበሌዎች የጣና ሐይቅ ከመጠን በላይ ሞልቶ ወደኃላ በመመለሱ፣ የእርሻ ማሳዎች፣ መኖሪያ ቤቶችና እንስሳት በከፍተኛ ሁኔታ በውሀ መጥለቅለቃቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እየገለፁ ነው፡፡ መንግስትም መጥቶ ከመመልከት ውጪ ያደረገልን ድጋፍ የለም ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡ ዋገጠራ፣ አባ ጋሾና ዳሞት የተባሉ ቀበሌዎች ጉዳቱ ያየለባቸው ቀበሌዎች ናቸው ብለዋል፤ መንግስት በበኩሉ የሁለት ህፀናት ህይወት ማለፉንና ከ15 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መፈናቀላቸውን አመልክቷል፣ እርዳታም ወደ አካባቢው እየሄደ እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡ 


በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ ነዋሪው አቶ ገብሬ ጌቱ በስልክ ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የሐይቁ ውሀ ወደ ኋላ በመመለሱ በእርሻ ማሳቸውና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ አቶ ደመወዝ ፀጋ የተባሉ ሌላው የወረዳው ነዋሪ ሜዳዎችና የእንስሳቱ መኖ በውሀ በመጥለቅለቁ እንስሳቱ በምግብ እጥረት እየተጎዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ መንግስት እስካሁን ያደረገው ምንም ዓይነት እርዳታ እንደሌለ ነው አርሶ አደሮቹ የሚናገሩት፡፡ የፎገራ ወረዳ አደጋ መከላከል ጽ/ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ ወ/ሮ ሙሉነሽ አስረስ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ አንዳንዶቹ በውሀ ተጎጂዎች ከተከበቡበት አካባቢ ለመውጣት ፍላጎት ስለሌላቸው እንጂ እርዳታ ተዘጋጅቶ እየጠበቃቸው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ህሊና መብራቱ ለዶይቼ ቬሌ እንዳሉት ጣና ሐይቅ ሞልቶ ወደኃላ በመፍሰሱ በደቡብ ጎንደር 3 ወረዳዎችና በማዕከላዊ ጎንደር 1 ወረዳ በሚገኙ 16 ቀበሌዎች የውሀ መጥለቅለቅ ደርሷል፡፡ በአደጋው ሁለት ህፃናት ህይወታቸው ሲልፍ፣ 15ሺህ አርሶአደሮች ተፈናቅለዋል፣ 9ሺህ ሄክታር የእርሻ ማሳ በውኃ ተጥለቅልቋል ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ህሊና እንደሚሉት ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች አስፈላጊው የምግብና ለመጠለያነት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲደርሳቸው በክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በኩል ጥረት እየተደረገ እንደሆ አመልክተዋል፡፡

ከጨረጨራና ርብ ግድቦች ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ የሚነሱ ችግሮችም በቀጣይ በጥናት ላይ ተመስርቶ የሚሰሩ ሥራዎች እንደሚኖሩና ሥጋቶች የሚወገዱበት ሁኔታ እንደሚኖር ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ አየርትንበያ መስሪያ ቤት የምዕራብ አማራ ማዕከል የትንበያ ባለሙያ አቶ ጥላሁን ውቡ እንዳሉት የዝናብ ሁኔታው እስከጥቅምት ሊቀጥል ስለሚችል ኅብረተሰቡ አሁንም ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ