1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የቀጠለው ጦርነት እና የሰላማዊ ሰዎች ስጋት

ማክሰኞ፣ የካቲት 12 2016

በአማራ ክልል በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውግያ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአይን ምስክሮች ተናገሩ ። በክልሉ በተለይ በምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች እየተደረገ ያለው ውግያ በከተሞች የእንቅስቃሴ ገደብ አስከትሎ ለእንግልት እያጋለጣቸው መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4cczn
Tigray-Krise in Äthiopien
ምስል Eduardo Soteras/AFP

በአማራ ክልል ጦርነቱን ተከትሎ ረሃብ እንዳይከሰት ነዋሪዎች ሰግተዋል

በአማራ ክልል በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውግያ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአይን ምስክሮች ተናገሩ ። በክልሉ በተለይ በምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች እየተደረገ ያለው ውግያ በከተሞች የእንቅስቃሴ ገደብ አስከትሎ ለእንግልት እያጋለጣቸው መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም “ሰላማዊ ተቃውሞን ማፈን እንዲያቆሙ” የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቅርቧል። 
ባለፈው ሳምንት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉባት የመራዓዊ ከተማ አቅራቢያ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ያለው ውጊያ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአይን ምስክሩ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የመርዓዊው ግድያ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቁ
«መርዓዊ ትንሽ ወጣ ብሎ ባችማ የሚባል ቀበሌ አለ፤ የሜጫ ወረዳ አንዱ ቀበሌ ነው። እዚያ አካባቢ ከፍተኛ ውጊያ ነው የሚካሄደው በፋኖ እና በመንግስት ወታደሮች መካከል ከፍተኛ ትንቅንቅ ነው ያለው እንቅስቃሴው ከባድ ነው። አሁን በማወራህ ሰአት የጦር ሄሊኮፕተር እየሰለለች ነው   »
ባለፈው ሳምንት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉባት በተገለጸው መርአዌ  አሁንም ወጣቶች እየታደኑ እንደሚታሰሩ አስተያየት ሰጭው ይናገራሉ።  ከጥቃቱ በኋላ በከተማዋ ውስጥ ያለው ሁኔታ ከባድ መሆኑንም ገልጸዋል።  
«ከጥቃቱ በኋላ ህብረተሰቡ እየተሰቃየ ነው ያለው ፤ የሚገርምህ ወጣቱ አሁን እየታሰረ ነው ያለው ። ትናንትና አሁን ብዙ ወጣቶች ፤ የሚገርምህ ነገር እንዲያውም ልቀርጽ ነበር ቪዲዮ ማለት ነው ፤ መስመር ላይ እየተደባደቡ ነበር እያንብረከኩ ፤ ከዚያ በባጃጅ እየወሰዱ የሚገርም ነገር ማለት ነው።» 
በክልሉ ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ወርቅ ከተማ አቅራቢያም በተመሳሳይ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል ውጥረት መንገሱን ተከትሎ በከተማዋ የንግድ ተቋማት መዘጋታቸውን እና ውጥረት መስፈኑን  አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  የመርዓዊው ግድያ፣ አማርኛ የአፍሪቃ ኅብረት የስራ ቋንቋ እንዲሆን መጠየቁ ፣ የራድዮ ቀን 
«ደብረወርቅ ላይ ትናንት ሱቆች በከፊል ዝግ ነበሩ ፤ያው ህዝባዊ አመጽ ነው ፤ የንግዱ ማህበረሰብ፤ ዛሬ መጠጥ ቤቶችም ተጨምረዋል፤ እና በጥቅሉ ዛሬ ጸጥ ረጭ ያለ ነው። የባጃጅ እንቅስቃሴ ብቻ ነው ያለው በከተማዋ »
በደብረወርቅ ከተማ እና ዙሪያው ከውጥረት ያለፈ ብዙም የተኩስ ድምጽ እንደሌለ የገለጹት አስተያየት ሰጭው ምናልባት ይንግዱ ማህበረሰብ የአመጽ እርምጃ የሚወስድ ከሆነ ለነዋሪው አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳይከሰት ያሰጋል ብለዋል። 
« አሁን በእርግጥ የተኩስ ድምጽ የለም ። ውጥረት ብቻ ነው ፤ ወታደሮችም ከካምፕ ውጭ እንቅስቃሴያቸው እየቀነሰ ነው፤ እና በዚህ ሁኔታ ላይ ነው ። የንግዱ ማህበረሰብ ነው አሁን አስፈሪ ነው ተብሎ የሚታሰበው ።  »
ከወገል ጤና ከተማ በስልክ ያነጋገርናቸው ሌላው አስተያየት ሰጭ  በከተማው አካባቢ የተለየ ነገር አለማስተዋላቸውን ነገር ግን የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ለግዳጅ ትፈለጋላችሁ መባላቸውን ተከትሎ የመጓጓዣ እጥረት እንዳይከሰት አስግቶናል ፤ ይላሉ ።ስለ መርዓዊ ከተማ ግድያ የዓይን እማኝ ምስክርነት
« የመንግስት ሰራዊት ነው ያለው አሁን ፤ በጸጥታው የሚታይ ችግር የለም ። ያው እንዳለ ነው። የተወሰነ በፖሊስ በሚሊሻ ህዝቡ እንዲህ ሆን እንዲህ ተንገላታን የሚል ነገር አለ። በተለይ የትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ወደ ግዳጅ ትሄዳላችሁ ተባልን ካልሆነ በስተቀር ጉልህ የሆነ ችግር የለም።  »
ሃሳባቸውን ያካፈሉን የመርአዌ ከተማ ነዋሪው እንደሚሉት በከተማዋ ከደረሰው ጥቃት በኋላ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ከተማዋን ለቆ መውጣቱን ነው ። በከተማዋ አቅራቢያ ውጊያው መቀጠሉን ተከትሎ የሰብአዊ እርዳታ በወቅቱ ካልቀረበ በቀር ህዝቡ ለረሃብ መጋለጡ እንደማይቀር ይናገራሉ።   
«ዝቅተኛ ነዋሪው የሚሄድበት ያጣው ፣ ዘመድ የሌለው ምናምን በጣም እየተራበ ነው ህዝቡ ፤ ይሄ ዝቅተኛ ነዋሪ አለ አይደል ፤ አረቄ የሚሸጠው ፤ ጠላ የሚሸጠው ፤ እነርሱ እነርሱ በጣም እየራባቸው ነው። በእርግጠኝነት በዚህ ሳምንት እርዳታ ምናምን ካልገባ በእርግጠኝነት በረሃብ ራሱ በጣም ብዙ ሰው ይሞታል »
በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የነገሰው ውጥረት እና ውጥረቱን ተከትሎ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ዜጎችን ለመታደግ  መወሰድ ባለበትእርምጃ ላይ የክልሉ መንግስት አስተያየት ለማካተት ወደ ክልሉ የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ስልክ ብንደውልም ። በሌላ ፕሮግራም መያዛቸውን ጠቅሰው «አሁን አስተያየት መስጠት አልችልም» ብለዋል።
ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም አምንስቲ ኢንተርናሽናል “የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሕጋዊ አሰራርን ወደ ጎን በማለት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰዎችን በገፍ ማሰር ማቆም» አለባቸው ሲል  ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። 
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ