በትግራይ የሴቶች ጥቃትን በመቃወም የተከፈተው ዘመቻ  | ወጣቶች | DW | 25.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

በትግራይ የሴቶች ጥቃትን በመቃወም የተከፈተው ዘመቻ 

በትግራይ ክልል የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን የሚቃወም እንዲሁም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ዘመቻ በማሕበራዊ ሚዲያ እየተደረገ ነው። “ይኾኖ” በሚል ሃሽታግ ሰሞኑን ከሚካሄደው ዘመቻ ጎን ለጎን ድርጊቱን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የሚደረገው ጥረትም ቀጥሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:09

የ“ይኾኖ” ዘመቻ ትኩረት ስቧል 

ከሁለት ሳምንት በፊት በትግራይ ክልል ሽረ እንደስላሴ ከተማ አቅራቢያ ከምትገኘው ዓዲ ዳዕሮ ከተማ የተሰማው ዜና በትግራይ የሴቶች ጥቃት ጉዳይ ዳግም ትኩረት ተሰጥቶት አጀንዳ እንዲሆን አድርጓል። ዜናው የዓዲ ዳዕሮ ከተማ ህዝብ በተለይም ሴቶች ብሶታቸውን ለማሰማት አደባባይ መውጣታቸውን የተመለከተ ነበር። የከተማይቱ ነዋሪዎች ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ካደረጋቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱ የሴቶች ጥቃት እና ጥቃት ተፈጽሞ በሚገኝበት ሰዓት የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ዝቅተኛ መሆኑ ነው። 

ይህን ሁነት ተከትሎ በፆታ ተኮር ጥቃቶች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉ የሴቶች መብት ተሟጋች እንስቶች ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ላይ ለማድረግ ሞክረው ተከልክለዋል። የሴቶች መብት ተሟጋቾቹ የተቃውሞ ሰልፉን ለማድረግ አሁንም ጥረታቸውን አላቆሙም። ከዚሁ ጎን ለጎን ፆታዊ ጥቃቶች ለመቃወም እና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ እያካሄዱ ይገኛሉ። “ይኾኖ” በሚል ሃሽታግ የሚካሄደው ይሄው ዘመቻ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን ትኩረት ስቦ ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኗል።  

በትግራይ ፆታ ተኮር ጥቃቶች ትኩረት እንዲያገኙ ከሚንቀሳቀሱ ሴቶች መካከል የሆነችው ዶክተር ሄለን ቴድሮስ በምትሰራበት መቐለ ሆስፒታል ሴቶች በባሎቻቸው፣ የፍቅር ጓደኛቸው አልያም ሌላ ሰው ጥቃት ደርሶባቸው ለህክምና እንደሚመጡ ትናገራለች። እንደ ዶክተር ሄለን ምልከታ በሁሉም የዕድሜ ደረጃ የሚገኙ ሴቶች ፆታዊ ጥቃት የሚፈፀምባቸው ቢሆንም “ለአቅመ ሄዋን ባልደረሱ ሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል” ትላለች። 

ከሁለት ዓመት በፊት የወጣው የማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተወ በትግራይ ክልል 12 በመቶ ሴቶች በየዕለቱ ፆታዊ ጥቃት ያስተናግዳሉ። በክልሉ ከሚኖሩ ያገቡ ሴቶች መካከል 18.7 በመቶ በባሎቻቸው አካላዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ 81 በመቶ በትግራይ ገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች በወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው አልያም የቅርብ ሰው ተገድደው ትዳር እንዲመሰርቱ ይደረጋል። በተለይም በትግራይ ገጠር አካባቢዎች ከፆታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ ያለው ሁኔታ የከፋ ነው። በርካታ ሴቶች ከተደፈሩ በኋላ ደፋሪዎቻቸውን እንዲያገቡ ይደረጋል።

በትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመቃወም ከሚንቀሳቀሱ መካከል የሆነችው ዳናይት መኮንን ጥቃቱ አሳሳቢ ከመሆኑም በተጨማሪ “ፍትሕ በማግኘት ላይ ያሉ ክፍተቶች ችግሩን የተባባሰ አድርጎታል” ትላለች። በትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ እነዚህን ጥቃቶች ለመከላከል እንደ እርሷ ያሉ ወጣት ሴቶች የማሕበረሰቡ ግንዛቤ ለማሳደግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ይገኛሉ። ወጣቶቹ የተፈፀሙ ጥቃቶች የማጋለጥ እና ፆታ ተኮር ጥቃት ትኩረት እንዲያገኝ የማድረግ ስራዎች እየከወኑ ነው። 

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ተስፋለም ወልደየስ 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች