1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ክልል ያለው የተረጂ ቁጥርና የባለስልጣናት መግለጫ መጣረስ

ቅዳሜ፣ ጥር 15 2013

በትግራይ ክልል ከ4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለአስከፊ ርሀብ መጋለጡን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ፣ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ በመንግስት የሚታወቀው በክልሉ ያለ ተረጂ ከ2 ነጥብ 5 አይበልጥም ብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/3oKho
Pressebild Red Cross, Rotes Kreuz | Äthiopien Tigray, Hilfe
ምስል ICRC

በትግራይ ክልል ያለው የተረጂ ቁጥርና የባለስልጣናት መግለጫ መጣረስ

 በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ህዝብ መፈናቀሉንና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ለርሀብ መጋለጡን የትግራ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ የጊዜዊ አስተዳደሩ ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሀ ደስታ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት 4 ሚሊዮን 500 ሺህ ህዝብ ለአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ እህል ተጋልጧል፡፡

 በተቻለ መጠን እርዳታ እየተዳረሰ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ቁጥሩ ባይታወቅም በርሀብ የሞቱ እንዳሉ ገልፀዋል፡፡

 የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህን ቢልም የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳን ጠቅሶ ብሔራዊ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ትናንት እንደዘገበው ደግሞ በትግራይ ክልል ለርሀብ ተጋልጧል እየተባለ የሚነገረው የተጋነነና በፌደራል መንግስት ያልተረጋገጠ ነው ብለዋል፣

 በተጨባጭ በክልሉ የተረጂው ቁጥርም 2 ሚሊዮን 500 ሺህ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ምትኩ፣ አብዛኛው እርዳታ ፈላጊ ከህግ ማስከበሩ በፊት በምግብ ዋስትና ማዕቀፍ ውስጥ የነበረ እንደነበረም አስረድተዋል፡፡

 አቶ ምትኩ እንደሚሉት ለ2 ሚሊዮን 500ሺህ እርዳታ ፈላጊ የክልሉ ህዝብ በ92 የእርዳታ ማሰራጫ ማዕከላት እርዳታ እየተሰጠው እንደሆነና በርሀብ ሞት ስለመመዝገቡ ግን መረጃ እንደሌላቸው አብራርተዋል፡፡

 ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር እርዳታ በአግባቡ ለተረጂው እየደረሰ እንደሆነ ያመለከቱት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ በአንዳንድ ወገኖች የእርዳታ እህል ለእርዳታ ፈላጊው አይደርሰውም እየተባለ የሚወራውም ሀሰትና የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ ኃይሎች ወሬ ነው ሲሉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ተናግረዋል፡፡

 እንደኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒሰቴር 71 ሚለሊዮን ብር የሚገመት መድኃኒትም በቅርቡ ወደ አካባቢው ተልኮ ለየጤና ተቋማት እየተከፋፈለ ነው፡፡

 በትግራይ ክልል የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ለወራት ደመወዝ ባለማግኘታቸው ለችግር መጋለጣቸውን በቅርቡ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ደመወዝ የሚከፈልበት አቅጣጫ በመቀመጡ ሰራተኞች በቅርቡ ደመወዛቸው እንደሚከፈል አመልክተዋል፡፡

 ዓለምነው መኮንን