1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ከተሞች የሚከሰት ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ችግር መፍጠሩ ተገለጸ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 1 2016

በትግራይ ከተሞች በተደጋጋሚ የሚከሰት የኃይል መቆራረጥ እየፈተናቸው እንደሚገኝ ነዋሪዎች እና የአምራች ተቋማት ኃላፊዎች ተናገሩ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰሜን ሪጅን አንድ ከፍተኛ ኃላፊ ችግሩ በኃይል ማስተላለፊያ ላይ በደረሰ ጉዳት የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4jCsW
የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ
በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ የተለያዩ ክፍሎች ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ሐይል መቋረጥ እያጋጠመ መሆኑን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Million H. Selassie/DW

በትግራይ ከተሞች የሚከሰት ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ችግር መፍጠሩ ተገለጸ

በመቐለ የተለያዩ ክፍሎች ጨምሮ በሌሎች የትግራይ ከተሞች ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ሐይል መቋረጥ እያጋጠመ መሆኑ ተከትሎ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ገለፁ። የመቐለ የተወሰነ ክፍል የኤሌክትሪክ ሐይል ከተቋረጠ ከ40 ቀናት በላይ ተቆጥረዋል። በዚህም ትላልቅ ኢንዳስትሪዎች ጨምሮ በሐይል እጦት እና መቋረጥ እየተፈተኑ ነው።

በተለይም በተያዘው የክረምት ወቅት በስፋት እየታየ ያለው እና መቐለ ከተማ ጨምሮ በርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሚሸፍነው ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ሐይል መቋረጥ በነዋሪዎች ዘንድ የከፋ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ፈጥሮ ይገኛል።

በመቐለ በተለምዶ ሰብዓ ካሬ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ የኤሌክትሪክ ሐይል አገልግሎት ከተቋረጠ ከ40 ቀናት በላይ ማለፉቸው የሚገልፁት ነዋሪዎች፥ ከመቐለ ውጪም ቢሆን በሀገረሰላም እና ወጀራት አካባቢዎች ከወር በላይ ለሚሆን ግዜ የኤሌክትሪክ ሐይል ተስተጓጉሎባቸው ቆይቷል።

ወደ ቀያቸው የተመለሱ የትግራይ ተፈናቃዮች ደስታና መመለሱ የዘገየባቸው ተፈናቃዮች ቅሬታ

 በአስር ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ በሚኖርበት ከመቐለው ሰብዓ ካሬ መንደር ያነጋገርናቸው አቶ ማቴዎስ ገብረሕይወት፥ ነዋሪው በኤሌክትሪክ ሐይል እጦት ምክንያት ኑሮው ፈታኝ ሆኖ ይገኛል ይላሉ።

በትግራይ የኤሌክትሪክ ሐይል እጦት እና መቆራረጥ ከመኖርያ መንደሮች በዘለለ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችም እየፈተነ ያለ ሲሆን፥ አምራች ድርጅቶች ስራ አቁመዋል፣ ለሜሽኖች ብልሽት ተዳርገዋል፣ ስራቸው ለማስቀጠል በውድ ዋጋ ነዳጅ ወደ መግዛት የገቡም አሉ።

ትግራይ ገጠራማ አካባቢ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰሜን ሪጅን አንድ ከፍተኛ ኃላፊ ችግሩ በኃይል ማስተላለፊያ ላይ በደረሰ ጉዳት የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል።ምስል Million H. Selassie/DW

የሞሃ ለስላሳ መጠጦች ኢንዲስትሪ መቐለ ፋብሪካ ዋና ስራ አስከያጅ አቶ ኪዱ ሃይለዝጊ "ከፍተኛ የሐይል መቋራረጥ ይታያል፣ መቆራረጡ አንዳንድ የሜሽን ክፍሎች የሚጎዳበት ሁኔታ አለ። በማምረት ሂደታችን ላይ የግዜ ብክነት ይፈጥራል። በምርት ጥራትም አሉታዊ ተፅእኖ አለው" በማለት ያሉ ችግሮች ያብራራሉ።

በትግራይ «ሕግ ማስከበር» ዘመቻ መጀመሩ

ተቋማት እና ነዋሪዎች ለሐይል አቅራቢው ተቋም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰሜን ሪጅን በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሲሆን የሚሰጣቸው ምላሽ አጥጋቢ እንዳልሆነም ያነሳሉ። አቶ ማቲዎስ "ከአርባ ቀን በላይ ኤሌክትሪክ ማጣት ማለት በጣም የሚያሳዝን ነው። ሐላፊነት የማይሰማቸው እና ስራቸው በአግባቡ መስራት የማይችሉ ሰዎች እዛ ቦታ ላይ እንዳሉ ማሳያ ነው" በማለት ምሬታቸው ይገልፃሉ።

የሐይል መቋረጡ ዋነኛ ምክንያት በሐይል ማስተላለፊያ ላይ የደረሰ ጉዳት መሆኑ የሚገልፁት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሐይል አገልግሎት ሰሜን ሪጅን የትራንስሚሽን እና ሳብስቴሽን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፥ ችግሩ በግዚያዊነት እስከ መጪው ነሐሴ አምስት 2016 ድረስ ለመፍታት እንደሚሰራ፥ በዘላቂነት ደግሞ ተጨማሪ ጥረቶች እንደሚደረጉ አንስተዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ