« በትግራዩ ጦርነት ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት ይረጋገጥ» ተቃዋሚው አረና ትግራይ ፓርቲ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 29 2016በሁለት ዓመቱ የትግራይ ጦርነት ለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ጥሪ አቀረበ። የያለፈው ጦርነት እና ጥፋት ተጠያቂነት ባለመረጋገጡ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ሐይሎች ለሌላ ጥፋት እየተዘጋጁ ነው በማለት አረና ከሷል። በወቅታዊ የትግራይ ፖለቲካዊ ሁኔታ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ የሰጠው፥ በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ህወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ለትግራይ አደጋ ይዞ የሚመጣ እና ሐላፊነት የጎደለው አካሄድ እየተከተለ ያለ ሲል ገልፆታል። ዓረና እንደሚለው የህወሓት አመራሮች ልዩነታቸው የግል እና የቡድን ጥቅም ለማስከበር የሚደረግ ፍጥጫ የወለደው ነው ብሎ እንደሚያምን የገለፀ ሲሆን፥ ይህ የህወሓት የውስጥ ጉዳይ ሊሆን እየተገባው ሆን ተብሎ ክፍፍሉ ወደ ህዝብ ለማውረድ ብሎም የከፋ ግጭት ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብሏል።
አረና ትግራይ ለረሐብ አደጋው ሕወሓት ትኩረት አልሰጠም ሲል ወቀሰ
ፖለቲካዊ ልዩነቶች በውይይት እና ድርድር መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል የሚል ጥሪ በተደጋጋሚ ለዓመታት ማቅረቡ የገለፀው ዓረና ትግራይ ይሁንና አሁንም ሁሉም አካላት ካለፈው ጥፋት ሳይማሩ ጭምር አደገኛ መንገድ ይዘው ቀጥለዋል ሲል ወቀሳውን ሰንዝሯል። የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ "አሁንም ወደ ጦርነት የሚወስዱ መንገዶች እየታዩ ያሉት እና የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመ ያለው፥ ባለፈው ሁለት ዓመት ለነበረው ጦርነት ከሁሉም ወገን ተጠያቂነት ባለመረጋገጡ ነው። ከሁሉም ወገን፥ ከህወሓት ይሁን ከሻዕብያ እንዲሁም ብልፅግና ወገን የጦርነቱ ተጠያቂዎች ስላልቀረቡ አሁንም የጦርነት ፍላጎት አለ። ለዚህም ዋነኛ መፍትሔ የሚሆነው የጦር ወንጀል ይሁን ዘር የማጥፋት ወንጀል የፈፀሙ አካላት፥ ለዓለምአቀፍ ፍርድ ቀርበው ሲዳኙ ብቻ ነው፤ ጦርነት የችግሮች መፍትሄ አድርጎ መመልከት የሚቆመው ብለን እናስባለን" ብለዋል።
አረና ትግራይ የፕሪቶሪያ ስምምነት በአስቸኳይ ይተግበር አለ
ሁለቱ ህወሓት ውስጥ ያሉ ቡድኖች አንዱ ሌላውን ከአስመራ እና አዲስአበባ ጋር ካሉ ሐይሎች በመመሳጠር እርስ በርስ ይካሰሳሉ ያሉት የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፥ ከሁለቱ የህወሓት ቡድኖች መካከል አንዱ ከኤርትራ ሐይሎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ፓርቲያቸው እንደሚገነዘብ ጨምረው ገልፀዋል።አቶ ዓምዶም "ከሁለቱ ቡድኖች አንዱ ከሻዕብያ ጋር እየተገናኘ ነው። የሚሰሙ ውንጀላዎችም ሓቅነት ያላቸው ናቸው። ከውጭ ሐይሎች ጋር እየተገናኘ ነው ተብሎ የሚወነጀለው ሐቅ አለው። ይህ ሊቆም ይገባል። የሁለቱ ህዝቦች ወይም መንግስታት ግንኙነት ሊደረግ ከሆነ ደግሞ ይፋዊ በሆነ መንገድ ህዝብ አውቆት ነው ሊደረግ የሚገባው። ውስጥ ለውስጥ የሚደረግ ግንኘነት ጦርነት የሚያባብስ፣ ሌላው ሐይል ደግሞ ሌላ ደጋፊ እንዲፈልግ የሚያደርግ እንዲሁም ውጥረቱ ወደሌላ አካባቢ እንዲሻገር የሚገፋ አደገኛ አካሄድ ነው" ብለዋል።የአረና ፓርቲ አቤቱታ
በዚህ የዓረና ክስ ዙርያ ከህወሓት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ይሁንና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከሳምንታት በፊት፥ ጉባኤ ያደረገው ህወሓት ሲወቅሱ በስም ባይጠቅሱትም "ደጀን ይሆነናል ያሉት የውጭ ሐይል" ተማምነው እየተንቀሳቀሱ ነው ብለው ነበር። ለዚህ ውንጀላ በወቅቱ ምላሽ የሰጡ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ አማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው ክሱ ውድቅ በማድረግ ከየትኛውም የውጭ ሐይል ጋር ግንኙነት የለም ማለታቸው ይታወሳል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ