በተሽከርካሪዎች ለተጨናነቀችው አዲስ አበባ መፍትሄ ፍለጋ
ሰኞ፣ መስከረም 13 2017
የሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚፈጥረው የኢኮኖሚ ጠቀሜታው በርካታ ነው የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ መሪድ ቱሉ፤ በተለይም ከከተሞች እድገት ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የትራንስፖርት መጨናነቅ አስቀድሞ ሊሰሩ የሚገቡ ልዩ የመሰረተ ልማት ትኩረት የሚያሻቸው ነው ይላሉ፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በተለያዩ ጊዜያት አዲስ አበባ ውስጥ ለሚፈጠረው የመንገዶች በትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ በርካታ እልባቶችን ስያፈላልግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በአንድ ወቅት የኮድ - 2 የግል ተሸከርካሪዎች በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ የሚል ውጥን በበርካቶች ቅሬታ ባነሳበት ከተማዋ አሁን ደግሞ ከሰሞኑ ከትምህርት መከፈት ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የትራፊክ መጨናነቆችን ለመቀነስ የተወሰኑ የከተማዋ መስመሮች ለብዙሀን ትራንስፖርት አግልግሎት ብቻ ክፍት እንዲሆኑ በሚል ውሳኔ ብቅ ብሎ ነበር።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ያማረረው የትራንስፖርት አገልግሎት
ይሁንና ቢሮው ወዲያው ይህንንም ውሳኔ ሽሮ ባወጣው መግለጫ እቅዱ ከባለድርሻ አካለት ጋር ውይይት እስከሚደረግበት ድረስ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ባለበት ይቀጥላል ብሏል።
ትራንስፖርት ቢሮው ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ 14 መስመሮችን ይፋ በማድረግ ለብዙሃን ትራንስፖርት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ተለይተዋል ነበር ያለው።
የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ መሪድ ይህ የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ በርግጥ በተለያዩ አገራት ተመሳሳይ ልምድ በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ “እንደዚህ አይነት ፖሊሲዎች በተለይም ትራፊክ ፍሰቱ በሚጨናነቅበት ገቢራዊ የሚሆንባቸው እንደ ቻይና ያሉ አገራት አሉ” ብለዋል፡፡የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር
ይህን መሰል ውሳኔ ግን ከሌሎች አገራት በቀጥታ ቀድቶ ከመምጣት ይልቅ የኛን አገር ተጨባጭ እውነታ ከግንዛቤ ማምታት እንደሚያስፈልግም ባለሙያው ስመክሩ፤ “በኛ አገር ሁኔታ ችግሩ መኪና መዝቶ ሳይሆን የመሰረተ ልማት ውስንነት ነው ያለው፡፡ ከዚህች ያለችው መኪና ውስጥ እንቅስቃሴ የተወሰኑትን መንቀሳቀስ መገደብ ሌላ ችግር ይዞም የሚመታ ነው የሚመስለው፡፡ በመሆኑም አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎችን መፈለግ እና መሰረተ ልማት ላይ አተኩሮ መስራት ዘላቂ እልባት ሊያመጣ ይችላል” የሚል ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ላይ ግጭት ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ በሚመስል መልኩ ከፍተኛ የህዝብ ብዛትና የትራንስፖርት መጨናነቅ ጎልቶ ይስተዋላል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ