በሶማሌ እና ኦሮሚያ ድንበር ውጥረት ሰፍኗል | ኢትዮጵያ | DW | 14.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

በሶማሌ እና ኦሮሚያ ድንበር ውጥረት ሰፍኗል

በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰው ግጭት ጋብ ቢልም በቦታዎቹ ላይ አሁንም ውጥረት እንደሰፈነ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ገለጹ፡፡ ከዚህ ቀደም በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ በኦሮሚያ ስር እንዲተዳደሩ የተደረጉ ቀበሌዎች ወደ ሶማሌ ክልል እንዲጠቃለሉ ተወስኗል በሚል ነዋሪዎቹ ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡ 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:53
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:53 ደቂቃ

የአምስት ቀበሌዎች ይገባኛል ተቃውሞ አስነስቷል

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሚገኙ የባቢሌ እና ጉርሱም ወረዳዎች ሰሞኑን መረጋጋት ርቋቸዋል፡፡ ተመሳሳይ ስም ካላቸው የሶማሌ ክልል ተጎራባች ወረዳዎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ ሰንብተዋል፡፡ መነሾው ደግሞ አወዛጋቢውን የሁለቱን ክልል ድንበር ለመከለል እየተደረገ ያለ ጥረት ነው፡፡ 

ባለፈው ሐሙስ በባቢሌ የጀመረው ተቃውሞ እና ግጭት ወደ ጉርሱም ተሻግሯል፡፡ ግጭቱ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ጋብ ቢልም በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት መስፈኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የባቢሌ ከተማ ነዋሪ በወረዳው ገጠር ቀበሌዎች የተነሳው ግጭት እንዴት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ቀበሌዎቹ በ1996 በኦሮሚያ እና ሶማሌ አወዛጋቢ ቦታዎች በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ የተካተቱ ነበሩ ይላሉ፡፡  

“ያው በድንበር ላይ በተመለከተ በሶማሌ እና አሮሞ መካከል ሰላም አልነበረም፡፡ ሐሙስ ዕለት ቀን የሶማሌ እና የኦሮሞ ኮሚቴ እነዚህ ኮሚቴዎች በህዝበ ውሳኔ ጋር ያሉት ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች ቦታውን እነርሱ ስለሚያውቁት እነርሱ ነው የሚወስኑት ተብሎ እስከ 30 ሽማግሌዎች ከየቀበሌው ተሰበሰቡ፡፡ ከእነርሱ ተቀምጠው እየተወያዩበት ነበር፡፡ ወደ ቦታውም ሄደው እያዩ ነበር፡፡ በህዝበ ውሳኔው የተወሰነው ቦታ ትንሽ ራቅ ይላል፡፡ ኦዳ ዳከታ ይባላል፡፡ በዚያ ያለው ህዝብ ኦሮሚያ መሬት ላይ ተቀምጦ የእኛ ነው መሬቱ ብለው የኦሮሞ ሰዎች እና ወደ እዚያ የሚሄዱ እስከ አራት የኦሮሞ መኪናዎችን ወጥተው በድንጋይ ሰባበሩት፡፡ ከዚያ በኋላ [ሽማግሌዎቹን] ሲያባርሯቸው ወደ ከተማ ተመለሱ” ሲሉ ስለ ሀሙሱ ክስተት ያብራራሉ፡፡

በወቅቱ በነበረው ግጭት የተፈነከቱ ሰዎች እንደነበሩ ገልጸው ከዚያ የከፋ ጉዳት አለመድረሱን ግን ተናግረዋል፡፡ ነዋሪው በጠቀሱት ዕለት በአዲስ አበባ ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ በባቢሌ እና ሐረር መካከል ባሉ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጥ የታከለበት ከፍተኛ ግጭት እንዳለ ለዜጎቹ በላከው መልዕክት አስጠንቅቆ ነበር፡፡ ከሐረር ጅጅጋ የሚወስደው አውራ ጎዳና መዘጋቱንም አሳውቋል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጉዳዩን አስተባብለዋል፡፡ ኤምባሲው በነጋታው ባወጣው ተመሳሳይ መልዕክት አውራ ጎዳናው ክፍት መሆኑን ነገር ግን ዜጎቹ በየአካባቢያቸው የሚሆነውን በንቃት እንዲከታተሉ አሳስቧል፡፡ 

ኤምባሲው ተጨማሪ መልዕክቱን በላከበት ባለፈው ዓርብ ዕለት በባቢሌ አቅራቢያ የሚገኙ የጉርሱም ነዋሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው እንደነበር ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ከዓርብ ጀምሮ እስከዛሬ የቀጠለው ተቃውሞ ዋና ምክንያት የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች የተፈራረሙት ስምምነት እንደሆነ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከተማው ነዋሪ ያስረዳሉ፡፡

“በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል በነበረው ስምምነት ላይ በተፈራረሙት መልኩ የቆሬ ቀበሌ እና በዚያው ስር የሚካተቱ አምስት ንዑስ ቀበሌዎች አንድ ላይ ለሶማሌ ክልል ለአስተዳደራዊ አመቺ በሚሆን መልኩ እንዲሰጥ ተብሎ ነው፡፡ ያ ነገር እንግዲህ ሲሰጥ ከዚያ ተነስቶ የጉርሱም ህዝብም የራሱን ተቃውሞ አሰምቷል፡፡ ተቃውሟችንን ካሰማን በኋላ ሽማግሌዎችን ሰብስበን ዛሬ ወደ አዲስ አበባ አቶ ለማ መገርሳን እንዲገናኙ ወደ አዲስ አበባ ልከናል፡፡ ይህንን የህዝብ ተቃውሞ አሰምተው እንደሚቀየር ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡

የሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያደረጉትን ስምምነት ቅጂ ተመልክቻለሁ የሚሉት እኚሁ ነዋሪ ለሶማሌ ይሰጡ የተባሉት አምስት ቀበሌዎች ተብሎ በደፈናው ይጠቀስ እንጂ ዝርዝራቸው አለመስፈሩን ያስረዳሉ፡፡ እርሳቸውን ጨምሮ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ያለው ጥርጣሬ አሁን በኦሮሚያ ስር ያሉት ኩልምዬ፣ ኖልዬ፣ ወረ ጉዬ፣ ወረ አሊ እና በከካ የተባሉ ቀበሌዎች ለሶማሌ ተሰጥተዋል የሚል ነው፡፡ በ1996ቱ ህዝበ ውሳኔ ወደ ኦሮሚያ እንደተጠቃለሉ የሚነገርላቸው እነዚህ አወዛጋቢ ቦታዎች በሶማሌ ክልል ስር እንዲሆኑ ለመወሰኑ አንዱ ማሳያ የክልሉ ልዩ ኃይል ሰሞኑን አካባቢውን መቆጣጠሩ ነው ይላሉ፡፡ ስሜ አይገለጽ ያሉ ሌላ የጉርሱም ነዋሪ በአካባቢው ያለውን ሁኔ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ 

“ህዝቡ እምቢ አለ፡፡ ‘እኛ ክልል አራት ሆነን አሁን ወደ ክልል አምስት በግድ መመለስ አንፈልግም፤ እኛ ኦሮሞ ነን’ ብሎ ህዝቡ አልፈልግም አለ፡፡ ክልል አምስት ደግሞ ልዩ ኃይል አምጥቶ ቆሬ ከተማ እና አካባቢ ላይ አስቀመጡ፡፡ አሁን እዚያ አምስቱ ቀበሌ ውስጥ ችግር አለ” ይላሉ ነዋሪው፡፡ 

የአምስቱ ቀበሌዎች ነዋሪዎች የሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆኑም ወረጉሜ በሚባለው ጎሳ ስር ያሉ የኦሮሞ ህዝብ አካል እንደሆኑ የጉርሱም ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ጥያቄያቸውም “አንዱን ህዝብ አትከፋፍሉት” የሚል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ኃላፊዎችን አስተያየት ለማካተት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ በሶማሌ ክልል በኩል ግን ችግሩ ከተፈጠረባቸው ቦታዎች አንዱ ነው የተባለውን የባቢሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሃመድ ጌሌን አግኝተን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ “ባቢሌ ሰላም ነው” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic