በስኳር ህመም ላይ የሚደረገው ምርምር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 15.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በስኳር ህመም ላይ የሚደረገው ምርምር

በኢትዮጵያ የታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ከመጣባቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መካከል የስኳር ህመም ይጠቀሳል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በሀገሪቱ በከተሞች አካባቢ ለስኳር በሽታ ያለው ተጋላጭነት ከፍ ያለ ነው። በበሽታው ላይ ምርምር ያደረጉ የጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህር በገጠር አካባቢዎች ያለው የስኳር በሽታ በከተሞች ካለው የተለየ መሆኑን ደርሰውበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:44

የገጠሩ የስኳር ህመም ከከተማው እንደሚለይ ጥናቱ ጠቁሟል

በህክምና ዘርፍ ከተሰማሩ 36ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል። ላለፉት 26 ዓመታት ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው የሰሩት በስኳር ህመም ላይ ነው። መቀመጫቸውን ጎንደር ዩኒቨርስቲ አድርገው በበሽታው የተጠቁ ህመምተኞችን በከተማም ወደ ገጠር አካባቢዎችም ወጣ እያሉ ሲያክሙ ቆይተዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን በበሽታው ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ምርምሮችንም በየጊዜው ማካሄዳቸውን አላቋረጡም። በእነዚህ ዓመታት በከተማም፣ በገጠርም የስኳር በሽተኞች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ታዝበዋል። 

ዶ/ር ሽታዬ አለሙ ይባላሉ። በጎንደር ዩኒቨርስቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር ናቸው። በስኳር በሽታ ህሙማን ላይ ለዓመታት ባደረጉት ክትትል በከተማ እና በገጠር በዛ ብለው የሚታዩ የበሽታው ዓይነቶች የተለያዩ መሆናቸውን ተገንዝበዋል። “አይነት አንድ” የተሰኘው የስኳር በሽታ ባልተለመደ መልኩ በገጠር አካባቢዎች ከፍ ብሎ እንደሚታይም ምርምራቸው አመላክቷቸዋል። 

Karte Verbreitung von Diabetes 2014 ENGLISCH

“ያሉንን በሽተኞች በደንብ ስንከፍላቸው ከተማው ላይ ከ100 በሽተኛ 73፣ 74 ከመቶው ዓይነት ሁለት የቀረው ደግሞ 23፣ 24 በመቶው አይነት አንድ [ያላቸው ናቸው]። ገጠር ውስጥ ደግሞ ይገለበጣል። ወደ 77 ከመቶው አይነት አንድ፤ ሌላው ወደ 20፣ 23 ከመቶው ደግሞ አይነት ሁለት [ያላቸው ናቸው] ።ይሄ ደግሞ በዓለም ውስጥ ከሚታየው ስርጭት የተለየ ነው። በዓለም ውስጥ ስኳር ሲባል 80 እጁ አይነት ሁለት፣ 20 እጁ አይነት አንድ ነው።

እንግዲህ እኛ ከተማ የምናየው ‘አይነት ሁለት’ ለምን ገጠር ውስጥ ይሄን ያህል ዝቅ አለ ብለን ስንጠይቅ አንዱ የስኳር ህመም ምክንያት ዕድሜ ስለሆነ ሰዎች ረጅም ዕድሜ ላይኖራቸው፣ ረዥም ዓመት ላይኖሩ ይችላሉ። ሰው ዕድሜው በገፋቁጥር የስኳር በሽታ ስለሚይዘው [ማለት ነው]። ሁለተኛው ደግሞ ያው ውፍረት የለም። የአመጋገቡ ዘዴ ለስኳር ህመም የሚያጋልጥ አይደለም። አልኮል ብዙ አይጠጣም። ሰዎች እስከ ዕለሞታቸው ድረስ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። ለእንቅስቃሴ ብለው ሳያደርጉም የአኗኗር ዘይቤያቸው ብዙ እንቅስቃሴ ያለበት፣ ሰውነት የማያስወፍር ቀጥነው ዕድሜያቸውን የሚገፉበት፣ ምናልባትም ደግሞ በገጠር ውስጥ ጭንቀት (setress) ገጠር ውስጥ ላይኖር ይችላል። እነኚህ ጥያቄዎቻችን ናቸው አልተመለሱም። እንግዲህ የምናየው እንደዚህ ነው” ብለዋል ዶ/ር ሽታዬ።

“አይነት አንድ” የተሰኘው የስኳር ህመም አይነት በአብዛኛው በወጣትነት የዕድሜ ክልል እና ከዚያ በታች ባሉ አዳጊዎች እና ህጻናት ላይ የሚከሰት መሆኑን አዲስ አበባ በሚገኘው ግሸን ፋርማሲ የተዘጋጀ የህክምና መረጃ ይጠቁማል። ይህ አይነት የስኳር ህመም የሚከሰተውም ቆሽት የተሰኘው የሰውነታችን ክፍል የሚያመርተው ኢንሱሊን የተባለው ተፈላጊ ጥንረ ቅመም በጣም አነስተኛ ሲሆን አሊያም ከቶውኑ ማምረት ሲያቆም እንደሆነ የህክምና መረጃው ያሳያል።

“አይነት ሁለት” የተሰኘው የስኳር ህመም አብዛኛውን ጊዜ ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰት መሆኑን የሚገልጸው የህክምና መረጃው በብዙሃኑ ዘንድም ይበልጥ የሚታወቀውም ይሄኛው አይነት በሽታ ነው ይላል። ዶ/ር ሽታዬ በህሙማኖቻቸው ላይ የተመለከቱት የ“አይነት አንድ” የስኳር ህመም በህክምና መጽሐፍት ላይ ከተጠቀሰው የራቀ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህም ለተጨማሪ ምርምር እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ።  

“መጽሐፉ የሚለው ምንድነው? ‘አይነት አንድ’ ስኳር በሽታ የሚበዛው ከአራት እስከ ሰባት ዓመት እና ከ10 እስከ 14 ዓመት በትንንሽ ህጻናት እና በጉርምስና ዕድሜ ባሉ ልጆች ላይ ነው። እኛ ግን ይሄንን በሽታ ገጠር ገበሬ፣ ድሃ አርሶ አደር ላይ እናየዋለን። እና የምናይባቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ ከ25 እስከ 30 ዕድሜ ያሉ፣ ከሴት ይልቅ ብዙዎቹ ወንዶች ሆነው ሳለ ልክ በመጽሐፉ ላይ እንደተጻፈው ‘አይነት አንድ’ ናቸው። ያለ ኢንሱሊን አይሻላቸውም፣ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ሁልጊዜ ኢንሱሊን መውሰድ አለባቸው ግን ዕድሜያቸው የዘገየ ነው። እንደ መጽሐፉ ከ4 እስከ 7 ወይም ከ10 እስከ 14 ሳይሆን ዘግይቶ ነው የሚታየው። 

ይህ አይነት አካሄድ ቀድሞም የታየ ነው። እኛ አዲስ አይደለም ያየነው። እኛ ስናይ ግን ጥያቄዎች ጠየቅን። ለምን ይሄ እንዲህ ሆነ? ራሱን የመጽሐፉን አይነት ስኳር ከሆነ ምን አዘገየው ለመምጣት? ካልሆነ ደግሞ ምናልባት ይህ የስኳር ህመም  ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ወይ? የምግብ እጥረት አምጥቶት ይሆን ወይ? ወይስ ሌላ የተለየ የስኳር ህመም ነው? ሶስተኛ አይነት፣ አራተኛ አይነት የስኳር ህመም ነው ወይ? የሚል ነገር ነው ያየነው” ይላሉ ዶ/ር ሽታዬ። 

ሶስት ዓመት የወሰደው እና ወደ መገባደጃው ላይ እንደደረሰ የተነገረለት ይህ ጥናት የስኳር ህመም እና የምግብ እጥረት ባላቸው ተዛምዶ ላይ ምን አመላከተ? ዶ/ር ሽታዬ ማብራሪያ አላቸው። “ያመላከተን ሁለት ነገር ነው። አንደኛ የዓለም ጤና ድርጅት በ1985 ዓ. ም. የስኳር ህመምን ሲከፋፍል ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዘ ብሎ አንድ ክፍል ሰጥቶት ነበር። በኋላ በ1999 ምንም ዓነት በቂ ምክንያት ሳይኖረው ከዚያ መካከል አወጣው።  ‘ድሮም እንደው ለብቻው ክፍል የሰጠነው ብዙ ጥሩ መረጃ ሳይኖረን ነው’ ብለው አውጥተው እንደገና ክፍፍሉን ከልሰውታል። እኛ ከዚያ ተነስተን ነው ‘አይ! ባትከልሱት ይሻላል። ምክንያቱም እኛ ጋር ያለው ለየት ያለ ስለሆነ ከምግብ እጥረት ጋር ሳይያዝ አይቀርም’ ብለን የምንናገረው።

ከዚህ በፊት ሌላም ጥናት አድርገናል።  ከዚህ በፊት የሰዎችን የልጅነት አመጋገብ እና በቂ ምግብ አላቸው፣ የላቸውም የሚያሰን አንዳንድ ምርመራዎች አድርገን ስኳር በሽተኞቻችን በምግብ በጣም የተጎዱ እንደሆነ እና በልጅነታቸው የምግብ እጥረት እንደነበረባቸው [ደርሰንበታል]። ምናልባትም እናቶቻቸውም የምግብ እጥረት ሳይኖርባቸው አይቀርም የሚል ውሳኔ ላይ እንድንደርስ አድርጎናል።  ይህን ከዚህ ቀደም አሳትነመዋል። እና በዚህ ምክንያት ነው የተነሳሳነው” ሲሉ ለምርምራቸው ምክንያት የሆነውን መነሻ ያስረዳሉ።   

በቀጣዩ ስድስት ወር ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የእነ ዶ/ር ሽታዬ ጥናት “አይነት አንድ” የተሰኘው የስኳር ህመም አይነት የሚይዛቸው ሰዎች የተለየ ዘር መል (gene) አላቸው ወይ? የሚለውን ጥያቄም ይፈትሻል። ጥናቱ እንዲዘገይ ያደረገውም ይሄው የዘረ መል ፍተሻ እንደሆነ ዶ/ር ሽታዬ ይናገራሉ። የምርምር ውጤታቸው ተጠናቅቆ ለህትመት ሲበቃ በኢትዮጵያ “እየተስፋፋ መጥቷል” ለሚሉት የስኳር ህመም የመፍትሄ ሀሳቦችን ይጠቁማል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። በኢትዮጵያ የስኳር ህመምተኞች ቁጥር እያሻቀበ የመጣበትን ምክንያት የተጠየቁት ተመራማሪዋ በገጠር እና በከተማ ከፍለው ምላሽ ይሰጣሉ።

“በገጠር አካባቢ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣበት ምክንያት ሁለት ነው። አንደኛው የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ሁለተኛ እንግዲህ የህክምናው ተደራሽነቱ ፣ ህክምናው መታወቁ፣ ሰው ወደ ህክምና መምጣቱ እየጨመረ መጥቷል። [በገጠር የበዛው] ‘አይነት አንድ’ ስለሆነ ይሄኛው አይነት በሌላ ውጪያዊ ምክንያት ብዙ አይቸገርም። ያ የሚሆንበት ብዙ ምክንያት የለውም። ሌላው ግን በከተማ ውስጥ ግን አመጋገባችን ትክክል አይደለም። ከአልኮል ጋር ሰው ያለው ግንኙነት በጣም ትክክል አይደለም። መንቀሳቀስ የሚባል ነገር የለም፤ ለትንሹም፣ ለትልቁም የምንጠቀመው መኪና ነው። ሰው ጭንቀት የተሞላበት (stressful) የአኗኗር ዘይቤ ነው የሚኖረው። በዚያ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥሩ በጣም እያደገ ነው። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ነው እያደገ የመጣው፤ አስፈሪ ነው” ሲሉ ዶ/ር ሽታዬ አጽንኦት ይሰጣሉ። 

 የጎንደር ዩኒቨርስቲዋ ዶ/ር ሽታዬ በስኳር ህመም ላይ ከሚያደርጉት ምርምር በላቀ አበርክቷቸው ይበልጥ የሚነሳው ህክምናውን ለህሙማን እንዲዳረስ ያደረጉት ጥረት ነው። በዩኒቨርስቲው ሆስፒታል የሚሰጠውን ህክምና በተለያየ ምክንያት ማግኘት ላልቻሉ ህሙማን የዛሬ 25 ዓመት ግድም አንድ እቅድ ይነድፋሉ።  እቅዱ “ህሙማኑ ወደ ሆስፒታል ካልመጡ ሆስፒታሉ ወደ ህሙማኑ ይሄዳል” በሚል እሳቤ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ከ25 እስከ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባሉ አካባቢዎች ህክምናውን ማዳረስ ነበር። ለዚህም ደባርቅ፣ ዳባት፣ አይከል፣  ቆላ ድባ እና ጠዳ የተሰኙ አካባቢዎችን መርጠው ወደ ስራ ገብተዋል። 

በአምስት አካባቢዎች የተጀመረው የስኳር በሽታ ህክምናን የማዳረስ ጥረት ዛሬ 10 ቦታዎችን የሚሸፍን ሆኗል። ቀድሞ ጤና ጣቢያ የነበረባቸውን አንዳንዶቹ አካባቢዎች ዛሬ ሙሉ ሆስፒታል ተገንብቶላቸዋል። ዶ/ር ሽታዬ በየጊዜው ህክምና የሚሰጣቸው በአጠቃላይ ከ8,500 እስከ 10 ሺህ ህሙማን እንዳሉ ናገራሉ። በየወሩ ለስኳር ህመምተኞች መድኃኒት በማድረስ የተጀመረው የዶ/ር ሽታዬ እንቅስቃሴ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አካትቶ በርካታ ህሙማን ህክምና እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል። 

በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆነ በሽታዎች ትኩረት ተነፍጎአቸው መቆየቱን የሚናገሩት ዶ/ር ሽታዬ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል ይህን ለማሻሻል ሙከራዎች እንዳሉ ይገልጻሉ። በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውም ግንዛቤ ከፍ እያለ መምጣቱን ያስረዳሉ። እንዲያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ “የስኳር ህመም አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲሉ ያስጠንቅቃሉ።

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ  

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic