1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰሜን ሸዋ ታጣቂዎች በእምነት ቦታ ላይ የተፈፀመ እገታና ግድያ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 22 2015

ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ ከተማ የልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን ዲያቆንን ገድለው ሌሎች 11 አገልጋዮችን ደግሞ አገቱ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሰላሌ አገረስብከት እንደገለጸው በዞኑ ስምንት ወረዳዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ቤተክርስትያናት በችግር ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቁመዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4Ivmz
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ሰሜን ሸዋ ዞን በርካታ ቤተክርስትያናት በፀጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቁመዋል

«ታጣቂዎች በኩዩ ወረዳ የገርባጉራቻ ከተማውን በጫፍ ገብተው ነው ልደታ ማሪያም በምትባል ቤተክርስቲያን ቅዳሜ ሌሊት ለእሑድ አጥቢያ አንድ ሰው ገድለው የደብሩ አስተዳደርን ጨምሮ 11 ሰዎችን ደግሞ አግተው እንደወሰዱዋቸው የሰማነው፡፡»

ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ በገርባጉራቻ ከተማ በምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልደታ ማሪያም ደብር ላይ ታጣቂዎች አደረሱት ስለተባለው ግድያ እና እገታ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የአከባቢው ነዋሪ የሰጡን አስተያየት ነው፡፡

ሌላው በዕለቱ ተረኛ ያልነበሩ የደብሩ አገልጋይም ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጸ ጠይቀውን መሰል ድርጊት ለገርባጉራቻ ከተማ የመጀመሪያው ቢሆንም ድርጊቱ በአከባቢው እየተለመደ የመጣ ነው ብለዋል፡፡ «አንድ ዲያቆም በዕለቱ ሲገደል፤ የደብሩ አስተዳደርን ጨምሮ 11 አገልጋዮች ከሦስት ጥበቃ ጋር ተወስደዋል፡፡»

አስተያየት ሰጪው የታጣቂዎቹን ማንነት አልገለጹም፡፡ ከዚህ አስቀድሞ በሌሎች ደብራት በተፈጸሙ ተመሳሳይ የእገታ ተግባራት በታጣቂዎች ገንዘብ መጠየቅ አዲስ ነገር ባይሆንም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በሰፊው መሰል ትኩረት ውስጥ እየገቡ መምጣታቸው ግን ጉዳዩን ከዚያም በላይ ያደርጓል ባይም ናቸው፡፡ «መወሰዳቸውን እንጂ የወሳጆችንም ሆነ የተወሰዱበትን ስፍራ አናውቅም፡፡ በትንሽ ደመወዝ ለሃይማኖታቸው የቆሙና የሚያገለግሉ አገልጋዮች ላይ መሰል የእገታ ተግባር መፈጸም ግን ገንዘብን ብቻ ፍለጋ አይመስለንም፡፡»

የሰሜን ሸዋ ሰላሌ አገረ ስብከት ሥራ አስከያጅ ሊቀ-ስዩማን ሽፈራሁ በበኩላቸው ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት፤ በቅዳሜ የገብረጉራቻ ልደታ ማሪያም የቤተክርስቲያን ግድያ እና እገታ የታገቱትን ሰዎች ለማስለቀቅ ከፀጥታ ኃይላት ጋር እየተሠራ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በዕለቱ ከግድያውና እገታው ሌላ በቤተክርስቲያን ላይ ግን ምንም አይነት ጥቃት አለመድረሱንም ነግረውናል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስከያጅ በአስተያየታቸው በአገረ ስብከቱ መሰል ተግባራት በአብያተ-ቤተክርስቲያናት ሲፈጸም የመጀመሪያው እንዳልሆነም ነው ያነሱት፡፡ ከዚህ ቀደምም በዞኑ በቤተክርስቲያን ላይ በተደጋጋሚ ተፈጽሟል ያሉትን መሰል ተግባራት ለጠቅላይ ቤተክነት ማሳወቃቸውንም አስገንዝበዋል፡፡ በዞኑ 8 ወረዳዎች ውስጥ ውስን የከተማ አከባቢዎች በስተቀር በቁጥር በርካታ በሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ሃይማኖታዊ አገልግሎት መስጠት መቆሙንም አክለው ተናግረዋል፡፡

የጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የገብረጉራቻ ልደታ ማሪያም ቤተክርስቲያን ጥቃትን ጨምሮ በሃይማኖቱ በተደጋጋሚ በእምነት ስፍራ ላይ ይፈጸማል ስለተባለው የታጣቂዎች ጥቃት ለመጠየቅ ለኩዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ይልማ ደውለን ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸው ምላሽ ሳይሰጡን ቀርተዋል፡፡ ለኃላፊው የጽሁፍ መልእክትም በመላክ በተደጋጋሚ ብንደውልላቸውም ምላሽ አልሰጡንም፡፡ ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮም ደውለን ለዛሬ አልተሳካልንም፡፡
 

ሥዩም ጌቱ 

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሠ