በረራና ብርቱ ፍርሃት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 08.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በረራና ብርቱ ፍርሃት

ሰው ለምን በአይሮፕላን መብረርን ይፈራል? በእንግሊዝኛ «አቪፎቢያ» ወይም «ኤይሮፎቢያ» የሚባለው ለምን ያድርበታል? ከሚነቀሳቀስበት የብስ ራቅ ባለና አንዳች ሊቆጣጠረው ፣ ሊይዘው- ሊጨብጠው በማይችልበት ሁኔታ ስለሚገኝ? ሰው በሠራው የሥነ ቴክኒክ

ውጤት መመካት አይቻልም ብሎ ስለሚያስብ ? ወይስ ባጭሩ ሞትን በመፍራት?! ስለበረራ ፣ የበራሪዎችን ፍርሃት እንዲሁም ሥጋቱን ለመቀነስ አንድ የሥነ ልቡና ምሁር በሚሰጡት እጭር ምክር ላይ ነው የዛሬው ሳይንስና ሕብረተሰብ የሚያተኩረው።

የሰው የዘመናት ህልምም ሆነ ምኞት በሥነ ቴክኒክ ዕድገት ተደግፎ አየሩን ሰንጥቆ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአንዱ ክፍለ ዓለም ወደሌላው በተወሰኑ ሰዓቶች ልዩነት ከተፍ የሚልበት አጋጣሚ ከተመቻቸ ቢያንስ 112 ዓመት ገደማ አልፏል። ኦርቪልና ዊልበር ራይት የተባሉ ወንድማማች በሰሜን ካሮላይና ኪቲ ሖክ ላይ የሙከራ በረራን ማሳካት ከቻሉበት ጊዜ አንስቶ ዓለም በፍጥነት ነው ፣ አይሮፕላንን ለህዝብ ማመላለሻ እንዲሁም ለጦር አገልግሎት እንዲውል ያበቃው። አሁን የሚታሰበው የበረራ ፍጥነትን፣ ከድምፅ ፍጥነት በላይ 4 እጥፍ ያህል ከፍ በማድረግ ፤ ለምሳሌ ያህል ከለንደን ሲድኒ -አውስትሬሊያ፤ አንድ የሕዝብ ማመላለሻ አይሮፕንን አሁን የሚወስድበትን ከ 23 ሰዓት የማያንስ ጊዜ፤ በሰዓት 22,000 ኪሎሜትር በመክነፍ፣ በ 2 ሳዓት ውስጥ እንዲገባ ማብቃት--- የሚለው ነው። «ቦይንግ» ሆነ «ኤርቡስ» ፤ በአሁኑ ጊዜ የሕዝብ ማመላለሻ አይሮፕላኖቻቸው፤ በሴኮንድ 299,4552 ሜትር እንጂ ከዚያ ባነሰ ፍጥነት አይደለም የሚጓዙት። ወደፊት ከድምጽ በ 4 እጥፍ ፍጥነት የሚከንፉ የሕዝብ ማመላላሻ አይሮፕላኖች ለመሥራት የታሰበው ፣ የብሪታንሪንያና የፈረንሳይ ንብረት የነበረው «ኮንኮርድ ሱፐርሶኒክ» የሕዝብ ማመላለሻ አይሮፕላን እ ጎ አ በ 2003 የበረራ አገልግሎቱን ከእነአካቴው ካቆመ ወዲህ ነው። ስለሆነም ሲቭሎችን ወደ ሕዋ ለአጭር ጊዜ ጉብኝት ለማመላለስ ትኩረት በማድረግ ፤ በ «ሰር» ሪቸርድ ብራንሰን የተቋቋመው Virgin Galactic የተባለው ድርጅት «ኮንከርድ»ን በመተካት ለመሥራት መነሣሣቱ አልቀረም ። የሕዋው ልዩ መንኮራኩር፤ ትንሽ ለወጥ ተደርጎ «ሱፐር ጄት » እንዲሆን ማብቃት አይገድም ፣ ብራንሰን እንደሚሉት። ታዲያ ሕዋን ሰንጥቆ ካንድ ክፍለ ዓለም ወደሌላው በፍጥነት ለመብረር ፣ መርኀ ግብሩ ከ 15 እስከ 20 ዓመት እንደሚወስድ ነው የተገለጠው።

«ቨርጂን ጋላክቲክ» ከከባቢ አየር እርከን በማለፍ፤ አንዳች የአየር ግፊት በሌለበት ባዶ የሕዋ ክፍል በስበት ኃይል በመክነፍ ነው በልዩ ቀዘፋ ወደ ሕዋ ከመውረዱ በፊት በረራውን ማካሄድ የሚሻው። ይህን የበረራ ዘዴ በመጠቀም ፤ ከለንደን ሲድኒ በ 2 ሰዓትም ሆነ በአንድ ሰዓት ከ 45 ደቂቃ ውስጥ መግባት እንደማያዳግትም ነው የዚህ ኩባንያ ባለቤቶች የሚገልጹት። «ቨርጂን ጋላክቲክ» ለአጭር ጊዜ ግብኝት የሕዋ ቱሪስቶች ለመሆን ከሚሹ 640 ያህል ቱጃር ግለሰቦች 80 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡ ታውቋል።

የሕዝብ ማመላለሻ ዘመናዊ አይሮፕላኖች እስካሁን ባላቸው ፍጥነትና ከዚያም እጅግ በላቀ ሁኔታ ለመንገደኞች አግልግሎት እንዲሰጡ ሲታሰብ፤ በሥነ ቴክኒክ ፤ ደኅንነትን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ ፤ በእነዚህና በመሳሰሉት ምንጊዜም መሻሻል እንዲደረግ በመጣር መሆኑ የሚታበል አይደለም። ይሁንና የማንኛውንም ሰብአዊ ፍጡር ሰብአዊ ሥጋት አንዳንዴም ብርቱ ፍርሃት ራሱ ግለሰቡ እንጂ ማንም ሊያስወግደው አይችልም። አይሮፕላን በኅይለኛ ወጀብ ሳቢያ ወደላይ ወደታች ወደጎን የመናወጥ ሁኔታ ሲያጋጥመው መሥጋትም ሆነ መፍራት ፍጹም የተለመደ ሰብአዊ ባሕርይ ነው። ከዚያ አልፎ በአካልና በመንፈስ የሚያስጨንቅ ፤ ቀልብ የሚነሣ ሁኔታ ሲፈጠር ግን ፍርሃቱ ብርቱ ወይም አደገኛ ሊባል ይችላል። ከብርቱ ሥጋትም ሆነ ፍርሃት የተነሣ ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሁኔታዎች ሊከሠቱ ይችላሉ። ለምሳሌ ይህል፤ የልብ ትርታ ማየል ፣ ቁና -ቁና መተንፈስ፤ መንቀጥቀጥ፣

መዝለፍለፍ፣ እንዲሁም ላብ በላብ መሆን፣ የብርቱ ፍርሃት ነጽብራቆች ሊሆኑ ይችላሉ። ራስን መቆጣጠር ፍጹም ሲያቅትም ፤ በየት ልውጣ ብሎ መሸበር፣ ሽንትና የመሳሰለውን መቆጣጠር አለመቻል፤ ማስታወክና የመሳሰለ ሁሉ የዚህ የብርቱ ፍርሃትም ሆነ ሥጋት ምልክቶች ናቸው።

ስለበረራ ፤ ከተነሣ ፤ ፍርሃት የሚያርዳቸውና በአይሮፕላን ለመሣፈር ፍጹም የማይሞክሩ ሰዎች ስለመኖራቸው እንሰማለን። እ ጎ እ በ 2010 በደቡብ አፍሪቃ በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ሥርዓት ለመዝፈን ሲጋበዝ ለቀቀው እንጂ ከዚያ በፊት ፣ በበረራ ፍርሃት የተነሣ፣ ወደ አውሮፓ ለዘፈን ሲመጣ እንኳ በመርከብ ነበረ የተጓዘው፤ ታዋቂው አፍሪቃዊ አሜሪካዊ አሜሪካዊ የ ሪዝም ና ብሉስ አቀንቃኝ ሮበርት ሲልቨስተር ኬሊ --ባጭሩ R . Kelly ! ከታወቁት ዜማዎቹም አንዱ እ ጎ አ በ 1997 ያቀረበው I Believe I can fly የተሰኘው ነው።

በዚህ በጀርመን ሀገር ፤ በቅርቡ ፣ «ጀርማን ዊንግስ» በተባለው የሕዝብ ማመላለሻ አይሮፕላን ያልተለመደ ዓይነት የአይሮፕላን አደጋ ፣ ማለትም በረዳት አብራሪው እኩይ ተግባር በጠቅላላ የ 150 ሰዎች ሕይወትን ከተቀጠፈ ወዲህ ፣ «የበረራ ፍርሃት የለብንም የሚሉ ወገኖችን ጭምር ድንጋጤ ውስጥ መክተቱ ሲነገር ይሰማል። አዘውትረው በአይሮፕላን ከሚጓዙትና መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል ሁለት ግለሰቦች የሚሉትን እናስደምጣችሁ---

«ብዙ ሺ ማይሎች አቋርጬ በአይሮፕላን በርሬአለሁ። የበረራ ፍርሃት የለብኝም። አንድ ትንሽ የሚያስስብ ጉዳይ ቢኖር፤ (አሁን አድገውልኛል እንጂ) የ ሁለቱ ልጆቼ ጉዳይ ነው። በትምህርት ልውውጥ ወቅት ብዙ ጉዳዮችን ፈጽመዋል። ይህ በቅርብ የተፈጸመው ጉዳይ ዘግናኝ ሆኖብኛል። »

ሌላ አንድ የዘውትር የበረራ ተገልጋይ ይህን ነበረ ያሉት።

«ብዙ ጊዜ፤ በአይሮፕላን የምጓዝ ሰው ነኝ። የቅርቡ አደጋ ከደረሰ በኋላም ቢሆን፤ በ «ጀርመንዊንግስ » በርሬአለሁ። ቀደም ባለው ጊዜ አንድ የታዘብኩት ነገር ቢኖር፣ አይሮፕላኑ ሲነሣና ሲያርፍ በተሰማ የተለመደ ድምፅ፤ የቴክኒክ ብልሽት ይሆን ወይ? በማለት የተደናገጥኩበት ቅፅበት ነበረ። በተረፈ ምንም የሚያሳስብ አይደለም። የተለመደ ነው። እርግጥ የወዲያኛው ሰሞኑ ሁኔታ፤ በተለየ መልኩ አስደንጋጭ ነበር።»

ሁኔታው እንደተባለው ፤ የበረራ ፍርሃት የሚባል ነገር በአጠገቤም አያልፍም የሚለውን ሁሉ ነው ያስደነገጠውና ፤ ጊዜ ትንሽ የድርጊቱን አስከፊነት እስኪያስረሳ ድረስ ፣ ከሞላጎደል ሁሉንም በአእምሮው እንዲያስብ እንዲያሰላስል የገፋፋው። በብሪታንያ አየር መንገድ (ብሪትሽ ኤይርዌይስ) ባለፉት 25 ዓመታት ለአብራሪዎች እንዲሁም ለተለያዩ ባለሙያዎችና የአይሮፕላን ተሣፋሪዎች የበራራ ፍርሃትን ስለማስወገድ ፣ ---በራስ ተማምኖ መብረር(Flying with Confidence) በሚል ርእሰ ኮርስ የሚሰጡት ዶ/ር ኬይት ስቶል፣

« የሆነ የአይሮፕላን አደጋ ከደረሰ በኋላ ሰዎች ሥጋታቸው ጨምሮ መወያየታቸው፤ የተለመደና ትክክለኛም ስሜት ነው » ይላሉ።

ስለበረራ ብርቱ ስጋትም ፤ ፍርሃትም ላላቸው ሰዎች የስነ ልቡናው ባለሙያ ዶ/ር ኬይት ስቶል፤

«አትሥጉ፤ ሁሉም ነገር አስተማማኝ » ነው የሚሉት ማበረታቻ ቃልም ሆነ ማጽናኛ እንደማይበጅ ነው የገለጡት።

«መቶ በመቶ፤ አስተማማኝ ሁኔታ የትም አይገኝም። አደጋ ከየት እንደሚመጣ ማንም አስቀድሞ ማወቅ አይችልም። አውቶሞቢሎች ከሚሽረከሩበት ጎዳና ዳር፤ መስመራቸውን ጠብቀው የሚጓዙ የእግር መንገደኞች፤ በቴክኒክ እክልም ሆነ በሰው ሠራሽ ሰበብ ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳርግ አደጋ ያጋጥመናል ብለው አያስቡም፤ ግን የሚያጋጥምበት ሁኔታ መኖሩ የታወቀ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፣ 1,200ሰዎች በአኤሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከዚያ በተለየ ሁኔታ ቤት ውስጥ ዳቦ በሚያሞቅ የኤሌክትሪክ መሳሪያ ሳቢያና በመሳሰለው በዛ ያሉ ሰዎች እንደሚሞቱ የሚያስብ የለም።

Richard Branson Vorstellung seines Raumschiffes

በረራ ለእኛ ለሰዎች ከተፈጥሮ ባህርያችን ጋር የሚያያዝ አይደለም። የአብዛኞቹ አእዋፍ አንጎል ከበረራ ልምድና ሕይወት ጋር የተዛመደ ነው። ይህን ግን የሰው አእምሮ አይገነዘበውም፤ ይላሉ ፣ ዶ/ር ኬይት ስቶል!

ስለበረራ የተለያዩ ድምጻውያን የተለያዩ እንጉርጉሮዎች ያሰማሉ ፣ ጀርመናዊው ራይንሃርድ ማይ ግን፣ እ ጎ አ በ 1974 ፣ ስለአንድ አይሮፕላን ማረፊያ ላይ ቆሞ የአይሮፕላኖችን ተንኮብኩቦ መነሣት የሚያደንቅን ሰው ስሜት በመግለጽ ይህን Über den Wolken ከደመናው በላይ የተሰኘውን ጀርመንኛ ተወዳጅ ዜማ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

« ከደመና በላይ ሲበሩ፤ ያለው ነጻነት ወሰን የሌለው ነው ፤ ፍርሃትዎና ሐዘንዎ ሁሉ ታምቆ፣ ተደብቆ ይቀራል፤ ትልቅና ፣ እጅግ ጠቃሚ መስሎ የሚታየን ሁሉ፣ ከመቅጽበት ኢምንትና ትርጉም የለሽ ይሆናል--» ይላል።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic