1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መተማ ዮሐንስ፦ ዉጊያ ጋብ ብሏል፣ ዉጥረቱ ግን አልረገበም

ረቡዕ፣ ነሐሴ 29 2016

አንድ የመተማ ዮሐንስ ነዋሪ«ዛሬ በከተማዋ የተኩስ ድምፅ ባይሰማም፣ በትናንትናው የተኩስ ልውውጥ የ2 ሰዎች ሕይወት አልፏል፣ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል»ብለዋል፡፡በከተማዋ ከሰኞ ጀምሮ እንቅስቃሴዎች እንደሌሉም ተናግረዋል። ሌላ አስተያየት ሰጭ የፋኖ ታጣቂዎች በመተማ ወረዳ የሺንፋ ከተማን ያለምንም ተኩስ ትናንት ማምሻውን እንደተቆጣጠሯትም አስረድተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4kH06
Äthiopien l Metema in der Amhara Region
ምስል Alemnew Mekonnen

«በምዕራብ ጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት ይካሄዳል» ነዋሪዎች

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ትናንት በአንዳንድ ከተሞች በመከላከያና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ሲካሄድ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል፣ የፋኖ ታጣቂዎች ትናንት ምዕራብ ጎንደር ዞን የምትገኘውን የሽንፋን ከተማ መቆጣጠራቸው ተነግሯል፡፡ ትናንት በመተማ ከተማ ዮሐንስ  በነበረው ውጊያ በሰዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን እንድ የዓይን እማኝ ገልጠዋል፣

ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በመተማ ዮሐንስ አካባቢ በፋኖና በመንግስት ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ሲካሄዱ ሰንብተዋል፣ ሰኞ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ገብተው ከወጡ በኋላ ትናንትና እንደገና ውጊያ በከተማዋ እንደነበር ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ አንድ የከተማዋ ነዋሪ አስተያየት ሰጪ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ደግሞ ዛሬ በከተማዋ የተኩስ ድምፅ ባይሰማም፣ በትናንትናው የተኩስ ልውውጥ የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል፣ ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል ብለዋል ፡፡ በመተማ ዮሐንስ  ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴዎች እንደሌሉም አስተያየት ሰጪው ገልጸዋል፡፡ ከሱዳን የጠረፍ ከተማ ገላባት ወደ ኢትዮጵያ የጠረፍ ከተማ መተማ ዮሐንስ የነበረው የትራንስፖርት እንቅስቃሴም መዘጋቱን ተናግረዋል፡፡ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው የአማራ ክልል ጦርነት ማብቂያው የት ነው?

“በትናንትናው ተኩስ ሁለት ሰዎች ሞተዋል፣ በሁለቱም ቀብር ላይ ተገኝቻለሁ፣ አራት ያክል የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም አሉ፣ በከተማዋ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም ” ብለዋል፡፡በገንዳ ውሀና በመተማ ዮሐንስ መካከል ላይ በምትገኘው “ኮኪት” በተባለችው አነስተኛ ከተማም የተኩስ ልውውጦች ሰሞኑን እንደነበሩ አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡

ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የምትገኘው የሺንፋ ከተማ አካባቢ
ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የምትገኘው የሺንፋ ከተማ አካባቢምስል DW/Alemenew Mekonnen

በመተማ ወረዳ የሺንፋ ከተማን ደግሞ የፋኖ ታጣቂዎች ያለምንም ተኩስ ትናንት ማምሻውን እንደተቆጣጠሯትና ከባንክ አገልግሎት ውጪ ሌሎች እንቅስቃሴዎች በተለመደው መልኩ መቀጠላቸውን አስረድተዋል፡፡ግጭት የወለደው ቀውስ በአማራ ክልል

እንደ አስተያት ሰጪው የፋኖ ታጣቂዎች ትናንት አመሻሽ 12 ሰዓት አካባቢ ያለምንም ተኩስ ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ጠቁመው ሁሉም የከተማ ውስጥ እንቅስቃሴዎች አልተስተጓጎሉም ነው ያሉት፣ ዛሬም የፋኖ ኃይሎች  በከተማው ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ አስረድተዋል፡፡ ከተማውም ሰላም እንደሆነ ነው አስተያየት ሰጪ የተናገሩት፡፡ “ ባንኮችን እኛ እስክንነግራችሁ እንዳትከፍቱ” መባሉንም አክለዋል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዛሬ 7 ሰኣት ድረስ ከተማዋ በፋኖ ታጣቂዎች ስር እንደነበረችም የከተማዋ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡ የሽንፋ ከተማ በመተማ ወረዳ ስር የምትገኝ ሲሆን ከገንዳ ውሀ ወደ ቋራ ወረዳ በሚወስደው መንገድ አማካይ ስፍራ ላይ ትገኛለች፡፡

በዞኑ ማዕከል ገንዳ ውሀ (ሸኽዲ) ዙሪያ ትናንት በተለያዩ አቅጣጫዎች የተኩስ ድምፅ ሲሰማ እንደነበር አንድ አስተያየት ሰጪ ጠቁመው ዛሬ ስጋቶች ቢኖርም በከተማዋ የተረጋጋ ሁኔታ በመጠኑ እንደሚታይ ገልጠዋል፡፡ትናንት ሁሉም የመንግስትና የግል ተቋማት ዝግ ሆነው ቢውሉም ዛሬ የተወሰነ እንቅስቃሴ በገንዳ ውሀ ከተማ እንደሚታይ ጠቅሰዋል፣ ትናንት ከባድ መሳሪያ ከገንዳ ውሀ ወደ ውጪ ሲተኮስ ውሏል፣ ዛሬ ጠዋት እንቅስቃሴዎች አልነበሩም ቀስ በቀስ ግን የከተማ ውስጥ እንቅስቃሴን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ብዙም ባይሆን እደነበሩ ገልጠዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ላይ የሚገኘው የመተማ ከተማ
ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ላይ የሚገኘው የመተማ ከተማ ምስል Alemenew Mekonnen/DW

ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪም ዛሬ ብዙም ተኩስ ድምጽ እንደማይሰማ ግን የፋኖ ተዋጊዎች በቅርብ እርቀት እንዳሉ ተናግረዋል፡፡በአማራ ክልል እገታና ግድደያ ነዋሪውን አማርሯል፡፡

ሱዳን ትሪቡዩን የተባለው የሱዳን ጋዜጣ ባለፈው ሰኞ ባወጣው ዘገባ “የፋኖ ታጣቂዎች የመተማን ከተማ በመቆጣጠራቸው ሁለቱን አገሮች የሚያዋስነውን ደንበር ሱዳን ዘግታለች” ብሏል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ከክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ ከምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደርና ከመተማ ወረዳ የስራ ኃላፊዎች ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ስልክ መነሳት ባለመቻሉ አልተሳካም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ