1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ ወለጋው ጥቃት በርካቶች መገደላቸው

ሰኞ፣ ሰኔ 13 2014

በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሊ ቀበሌ ሰኔ 11/2014ዓ.ም ደረሰ በተባለው ጥቃት በርካቶች ሲገደሉ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች አርጆ ወደ ተባለ ከተማና የተለያዩ ቦታዎች መፈናቀላቸውን ከጥቃቱ የተረፉት ለዶቼ ቬለ ተናገሩ። ባሳለፍነው ቅዳሜ ዕለት በደረሰው ጥቃት 108 ሰዎች መሞታቸውን ወደ ሌላ ወረዳ የሸሹ ነዋሪዎች አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/4Cwm9
Karte Äthiopien englisch

የምዕራብ ወለጋው ጥቃት

በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሊ ቀበሌ ሰኔ 11/2014ዓ.ም ደረሰ በተባለው ጥቃት በርካቶች ሲገደሉ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች አርጆ ወደ ተባለ ከተማና የተለያዩ ቦታዎች መፈናቀላቸውን ከጥቃቱ የተረፉት ለዶቼ ቬለ ተናገሩ። ባሳለፍነው ቅዳሜ ዕለት በደረሰው ጥቃት 108 ሰዎች መሞታቸውን  ወደ ሌላ ወረዳ የሸሹ  ነዋሪዎች አመልክተዋል። አርጆ በምትባል ቦታ በፈደራል እንደተወሰዱ የተናገሩት ሌላው ነዋሪ  ደግሞ በጅምላ የተቀበሩትን ጨምሮ 97 ሰዎችን በተለያዩ ቦታ አይቻለሁ ብለዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥቃቱ በሲቪሎች ላይ የደረሰ መሆኑን በማመልከት አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። ከምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደርና ከክልሉ መንግሥት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ከትናንት በስተያ ቅዳሜ ጠዋት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሊ ቀበሌ ውስጥ የደረሰው ጥቃት በንጹሀን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።፡ ከቶሊ ቀበሌ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማሳከም በሆስፒታል እንደሚገኙ የነገሩን አንድ ነዋሪ ትናንት የፌዴራል ጸጥታ ኃይሎች ወደ ስፍራው ገብተዋል ብለዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎችን ወደ ሆስፒታል ሲያመላልሱ እንደነበርም ገልጸዋል። ቶሊ በተባለች ቀበሌ በአንድ ቦታዎች በጅምላ የተቀበሩትን ሰዎች ጨምሮ ከ90 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉንና በስፍራው ማየታቸውን ለዶይቼቬለ ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱ ወቅት ሲሸሹ ጠፍተው የቀሩ ሰዎችም እንዳሉም አብራርተዋል፡፡

ቅዳሜ ጠዋት ከሦስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት በጊምቢ ወረዳ ቶሊ ቀበሌ ከፍተኛ ተኩስ እንደነበረ የተናገሩት ሌላው በጊምቢ ከተማ እንደሚገኙ የነገሩት ነዋሪም ከአንድ ቤተሰብ ከ9 እስከ 12 ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንደሚገኙ አመልክተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችም መቃጠላቸውን ነዋሪው ተናግረዋል። ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ወደ አርጆ ከተማ የተጠለሉ ሲሆን በከተማው ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚገኙ ሌላው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ አብራርተዋል። በአካባቢያቸው ተከስቶ በነበረው ጥቃት በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንም አክለዋል። የኢትዮጵያ ሰአብዊ መብቶች ኮሚሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ በተጠቀሰው ስፍራ በሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በአካባቢው ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት በመኖሩ  ለነዋሪዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው አሳስቧል። ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ዛሬ ጠዋት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ባስተላለፉት መልዕክት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እየተፈጸመ ያለውን የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት እንደማይታገሱ አመልክተዋል። ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላምና ደህንነት የመመለስ ተግባር ቅደሚያ የሚሰጠው እንደሆነም አክለዋል። በምዕራብ ወለጋ እና የተለያዩ ዞኖች ከዚህ ቀደምም በደረሱት ተመሳሳይ ጥቃቶች  የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉና ንብረት መውደሙ ሲዘገብ ቆይቷል።

ነጋሳ ደሳለኝ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ