1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ አርሲ ዞን የዶዶላ የንጹሃን ግድያ

ረቡዕ፣ መጋቢት 18 2016

ለደህንነታቸው ስባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የአከባቢው ነዋሪ በአከባቢው በተከታታይ ይፈጸማል ያሉት መሰል ጥቃት በሰኞ እለትም የአገልጋዮችን ህይወት ከነቤተሰብ አጥፍቷል፡፡ “የተገደሉት ምዕመናን ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/4eCTx
የከተማይቱ ባለሥልጣናት ለግድያዉ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ተጠያቂ አድርገዋል
ምዕራብ አርሲ ዶዶላ ዉስጥ በሰዉ እጅ የተገደሉት ሁለት የኃይማኖት አባቶችና አምስት ቤተሰቦቻቸዉ ናቸዉምስል picture-alliance/Panther Media/F. Salimi

በምዕራብ አርሲ ዞን የዶዶላ የንጹሃን ግድያ


በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ ባለፈዉ ሰኞ አመሻሽ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት በትንሽ ግምት 7 ሰዎች መግደላቸዉ ተነግሯል።የአካባቢዉ ነዋሪዎች እንዳሉት በጥቃቱ የተገደሉት  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች እና ቤተሰቦቻቸው ናቸዉ።ሟቾቹ ትናንት በዶዶላ ከተማ መቀበራቸዉን ምዕመናን እና ባለስልጣን አስታዉቀዋል።ጥቃቱ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በተከታታይ በገጠር ቀበሌያትም መፈጸሙ ነው የተጠቆመው፡፡


በአከባቢው የተባባሰው የምዕመናን ግድያ

በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በዶዶላ ደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክስቲያን አገልጋይ የነበሩ ሁለት አገልጋዮች ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በታጠቁ አካላት መገደላቸውን ምንጮች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ ለደህንነታቸው ስባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የአከባቢው ነዋሪ በአከባቢው በተከታታይ ይፈጸማል ያሉት መሰል ጥቃት በሰኞ እለትም የአገልጋዮችን ህይወት ከነቤተሰብ አጥፍቷል፡፡ “የተገደሉት ምዕመናን ናቸው፡፡ ግድያውም ቤተክርስቲያን፣ በአገልጋዮቿ እና ምእመናን ላይ ያነጣጠረ ነው የሚመስለው፤ ሌላ ላይ ስታይ አይስተዋልም፡፡ በተረፈ አፈና ሰው ማገት በአከባቢው የተለመደ ነገር ሆኗል” ነው ያሉት፡፡

ዶይቼ ቬለ ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊዎች እንዲሁም ለዞን ሀገረስብከት በተደጋጋሚ ብደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡ በቤተክርስቲያኗ የማህበረሰ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት እንደዘገበው ግን በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት የዶዶላ ደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሁለት አገልጋዮች ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው ጋር ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት መገደላቸውን አሳውቋል፡፡
ግድያው ሰኞ ምሽት መፈጸሙንም በመግለጽ የተገደሉት አገልጋዮቹ አንድ የቤተክርስቲያኑ መሪጌታ እና ዲያቆን ከነመላው ቤተሰቦቻቸው ባጠቃላይም ሰባት ሰዎች በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን አመልክቷል፡፡

ያላቧራው የንጹሃን ግድያ

በዚህ አከባቢ ተደጋጋሚ እና የማያቋርጥ ግድያ በቤተክርስቲያን ምእመናት እና አገልጋዮችላይ ይፈጸማል የሚሉት የምእራብ አርሲው ዶዶላ አስተያየት ሰጪ ከመስከረም ወዲህ እንኳ 80 የሚሆኑ ንጹሃን በታጣቁ አካላት መገደላቸውን ጠቁመዋል፡፡ “ዛሬ ነገ ምን እንሰማ ይሆን በሚል ከባድ ስጋት ውስጥ ነን፡፡ የጸጽታ አካላቱም ስሯሯጡ እንመለከታለን፡፡ ችግሩ ግን ስር የሰደደ ነው፡፡ ከመስከረም ወዲህ እንኳ በሁለቱ አርሲዎች የተገደሉት ምእመናን ከ80 በላይ ናቸው” ብለዋል፡፡

የባለስልጣን አስተያየት

ስለግድያ ድርጊቱ ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት የዶዶላ ከተማ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አማን ዳቤ በእለቱ ቤተክርስቲን ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጥቃት አለመኖሩን አስረድተው፤ በቤተክስቲያኑ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ምዕመናን ግን በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ በግፍ መገደላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከተገደሉት ሰባት የሁለት ቤተሰቦች አባላት ህጻናትም ጭምር እንደምገኙም ተናግረዋል፡፡ “እውነት ነው በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ላረጋግጥልህ የምፈልገው ግን ለጊዜው በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም፡፡ በእለቱ ሰባት ሰዎች ስገደሉ ህጻናት እና ወጣቶችም ይገኙበታል፡፡ ጥቃቱ በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ከምሽቱ 3 ሰኣት ከ10 ደቂቃ ገደማ ነው፡፡ ጥቃቱን የፈጸመው ኦነግ ሸነ ነው፡፡ በተጨማሪም አብሮት ይሰራል የተባለው የጠላት ኃይል የእነዚህ ንጹሃን ሰዎች ቤት መርቶ እንደወሰዳቸው ጥቆማ አለ እየተጣራ ነው፡፡ ንጹሃኑ ላይ የተወሰደው ጥቃት ተቀባይነት የሌለውና ሰብዓዊ መብትን የሚጋፋ ነው፡፡ እንደ መንግስት እና የከተማው አስተዳደር የምናወግዘው መሆኑን እያረጋገጥን፤ ድርጊቱ የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር የወጠነ ከመሆኑም በላይ የከተማውን መልካም ስም እና የህዝቦች አንድነት ለመሸርሸር የተደረገ ሴራ አድርገን ነው የምንወስደው” ብለዋል፡፡

ይወሰዳል የተባለው እርምጃ

ከተገደሉት ንጹሃን ውስጥመምህራን፣ የሃይማኖት አባቶች እና ህጻናት ይገኛሉ ያሉን ኃላፊው፤ መንግስት የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ የተለያዩ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡ “እንደ መንግስት የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የህግ የበላይነትን የማስጠበቅ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ጠንካራ ክትትልም እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከክልሉ መንግስት ጀምሮ በዚህ ላይ የተጠናከረ ስራ እየተሰራ ከችግሩ መፈጠር ጋር ትስስር አላቸው ተብለው የተጠረጠሩትን በህግ ጥላ ስር የማዋሉ ተግባር እየተከናወነ ነው” ብለዋል፡፡

የዶዶላ ከተማ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ አማን ሰኞ በከተማው የተገደሉትን ሰባት ንጹሃን ስርዓተ ቀብራቸው በትናንትናው እለት በከተማው ነዋሪ ስርዓተ ቀብራቸው መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ ከከተማው በተጨማሪ በዶዶላ ወረዳ የገጠር ቀበሌዎችም ተመሳሳይ ጥቃቶች ተፈጽመው የሰዎች ህይወት ማለፉን በመግለጽ ዝርዝሩን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከዚህ በፊት በአርሲ እና ምዕራብ አርሲ ዞኖች በምዕመኖቿ ላይ ተደጋጋሚ የግድያ እና አፈና ጥቃቶች መፈጸማቸውን መግለጿ ይታወሳል፡፡ በቅርቡ እንኳ ህዳር ወር ውስጥ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ 36 ምእመኗ መገደላቸውን ገልጻ ድርጊቱን ማውገዟ አይዘነጋም፡፡  

መንግስት ለመሰል ጥቃቶች እራሱን የኦሮሞ ነጸጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራውን ሸነ ያለውን የታጠቀ ቡድን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ታጣቂ ቡድኑ በፊናው መሰል የንጹሃን ዜጎች ጥቃት ላይ እጁ እንደሌለበት ስገልጽ ይስተዋላል፡፡የአሁኑን ጥቃት በተመለከተ ግን ከሁሉም ወገን በይፋ የተባለ ነገር የለም፡፡

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ