1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሙስና

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ15 ሚሊየን ብር በላይ በመመዝበር የተጠረጠሩ እየተያዙ ነው

ሰኞ፣ ግንቦት 19 2016

ጉዳዩም ከባለሙያዎችና የግንባታ ተቋራጮች እስከ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንደሚመዘዝ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ “ አብዛኛው ምዝበራ የተፈጸመው በኮሌጁ ያልተሠራን ሥራ እንደተሠራ በማስመሰልና የክፍያ ወጪ በማድረግ ነው።አስቀድሞ በተጠርጣሪዎቹ ተመዝብሯል ከተባለው 15 ሚሊየን ብር ሌላ ተጨማሪ 20 ሚሊየን ብር ከሙሰኞች መንጋጋ ለማዳን ተችሏል»ብለዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4gKhZ
አቶ ዘውዴ ባልቻ የደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ የሥነ ምግባርና ጸረሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር
አቶ ዘውዴ ባልቻ የደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ የሥነ ምግባርና ጸረሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምስል privat

በቡልቂ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ግንባታ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መዝብረዋል የተባሉ እየተያዙ ነው

 በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ15 ሚሊየን ብር በላይ መዝብረዋል በሚል የተጠረጠሩ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚሊየን የሚቆጠር ብር መዝብረዋል የተባሉ ባለሙያዎች ፣ የግንባታ ተቋራጮች እና የሥራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ይገኛሉ ፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ የሚገኙት በክልሉ ጎፋ ዞን ከሚገኘው የቡልቂ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ግንባታ ጋር በተያያዘ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ መዝብረዋል በሚል ነው ፡፡በኮሌጁ ባልተገባ ክፍያ ሊወጣ ነበር የተባለ ተጨማሪ 20 ሚሊየን ብር ከሙሰኞች መንጋጋ  አትርፊያለሁ ሲል የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል  ፡፡

ምዝበራው እንዴት ተካሄደ ?
የሙስና ተግባሩ ተፈጽሟል የተባለው  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በሚገኘው የቡልቂ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ውስጥ ነው ፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን  በኮሌጁ ተፈጸመ ያለው ምዝበራ ሠንሰለቱ ረጅም ፣ ተዋናዮቹም የበዙ ናቸው ይላሉ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ የሥነ ምግባርና ጸረሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘውዴ ባልቻ ፡፡አሳሳቢ ደረጃ የደረሰው የመንግሥትና ህዝብ ሀብት ምዝበራ
ጉዳዩም ከባለሙያዎችና የግንባታ ተቋራጮች እስከ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንደሚመዘዝ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ “ አብዛኛው ምዝበራ የተፈጸመው በኮሌጁ ያልተሠራን ሥራ  እንደተሠራ በማስመሰልና የክፍያ ወጪ በማድረግ ነው ፡፡  አስቀድሞ በተጠርጣሪዎቹ ተመዝብሯል ከተባለው 15 ሚሊየን ብር ሌላ በተጨማሪነት ሊከፈል የተዘጋጀ ነበር የተባለ 20 ሚሊየን ብር ከሙሰኞች መንጋጋ ለማዳን ተችሏል “ ብለዋል ፡፡

የወላይታ ሶዶ ከተማ
የወላይታ ሶዶ ከተማ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በሕግ ተጠያቂነት

በኮሌጁ ተፈጽሟል ከተባለው ምዝበራ ጋር በተያያዘ የህግ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ዳይሬክተሩ አቶ ዘዉዴ ተናግረዋል ፡፡ እስከአሁን ድረስ 16 ተጠርጣሪዎች የእሥር ማዘዣ እንደወጣባቸው የጠቀሱት አቶ ዘውዴ “  ከእነኝህም መካከል እስከአሁን 6ቱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ፡፡ የተቀሩት በህግ እየታደኑ ይገኛሉ ፡፡ የተያዙትና በህግ ከሚጠየቁት መካከል ምክትል የቢሮ ሃላፊዎች ፣ ዳይሬክተሮች ፣ ባለሙዎችና የግንባታ ተቋራጮች ይገኙበታል “ ብለዋል ፡፡የሜቴክ ሹማምንት ምዝበራ

አቶ አለማየሁ ባውዴ የደቡብ ኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ተጠሪ
አቶ አለማየሁ ባውዴ የደቡብ ኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ተጠሪምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ፈተና ሆኖ የቀጠለው ሙስና 

ዶቼ ቬለ በቡልቂ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ተፈጽሟል በተባለው የሙስና ድርጊት ከክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥራ ሃላፊዎች ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡  ያም ሆኖ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዴ ሙስና አሁንም የክልሉ ዋነኛ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል ፡፡ “ እኛ ብልፅግናዎች ሌብነትን እንጸየፋለን ብቻ ሥላልን የሚቆም ጉዳይ አይደለም “ ያሉት አቶ አለማየሁ “ በሁሉም የአስተዳደር እርከኖቻችን አሁንም ተግዳሮት ብለን ከለየናቸው አንዱ ሙስና ነው ፡፡  በክልላችን አሁንም ሥርቆት አለ ፣ ብልሹ አሠራር አለ ፡፡  በዚህ መንገድ ነው የምንበለጽገው ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሁንም በዚህ አጀንዳቸው ቀጥለዋል ፡፡ በቀጣይ ግን ይህን መታገል አለብን ፡፡ ቆራጥ የሆነ ሥረዓትም መዘርጋት ይጠበቅብናል  “ ብለዋል፡፡


ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ 
እሸቴ በቀለ