በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው ውዝግብ እና የፖለቲከኞች አስተያየት
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 7 2016የህወሓት ውዝግብ፡ የፖለቲከኞች አስተያየት
ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ጋር ወደ መካረር በመግባት ሂደቶቹ ወደ ግጭት እንዳያመሩ በጥንቃቄ ልያዝ እንደሚገባ ፖለቲከኞች አሳሰቡ፡፡
የክልሉን ፖለቲካዊ ሁናቴ በቅርበት የምከታተሉ ፖለቲከኞቹ እንዳሉት የሌላው ዙር ግጭት የመቀስቀሻ ምልክት እየሆነ የመጣው የህወሓት እና የብሔራዊ ምርቻ ቦርድ ውዝግብም ብሆን በሰከነ ውይይት እልባት እንዲፈለግለት ነው የተጠየቀው፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የህወሃት ውዝግብ
የቀድሞ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ርዕሰመስተዳድርና የህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፍተኛ አመራር እና የአሁኑ የተቃዋሚው ዓረና ትግራይ አመራር ፖለቲከኛ ገብሩ አስራት በወቅታዊው የህወሓት ውዝግብ ስጋት ከገባቸው ናቸው፡፡ አቶ ገብሩ አሁናዊውን ውዝግብ ምናልባትም የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዳግም የሚያጨልም ብለውታል፡፡
“ከዚህ በፊትም በፖለቲካ እልባት ልበጅለት የሚገባውን ጉዳይ ፖለቲካውን በማጦዝ ወደ ጦርነት የገቡት ሁለቱም አካላት (የፌዴራል መንግስት እና ህወሓት) ሁለቱም ወገኖች አሁንም የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለመተግበር ቁርጠንነቱ አላቸው ወይ” በማለት ይጠይቃሉ፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት አገሪቱ ያላትን የህግ መርህዎችን መጠበቅ ነው ያሉት ፖለቲከኛው አሁን የተጀመረው አካሄድ ወደ ግጭት የሚወስድ ከሆነ አደገኛ ነው ሲሉ ገልጸውታልም፡፡
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ከፍተኛ አመራር ፖለቲከኛ መስፍን ደሳለኝ በበኩላቸው ምናልባት እንደከዚህ ቀደሙ ባይከፋም ነገሮች ከከረሩ ጉዳቶች ሊደርሱ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
“ምናልባት ጉዳቱ እንደከዚህ ቀደሙ ባከፋም አለመግባባቱ ወደ ግጭት ልወስድ ይችላል” ሲሉ ግምታቸውን ያስቀመጡት ሌላው ፖሊቲከኛ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር መስፍን ደሳለኝ፤ በተለይም በፓርቲው አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል “የስልታን ፍላጎት የሚጫጫን ሽኩቻ” ሲሉ ሃሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ፖለቲከኛ መስፍን በአመራሮቹ አሁንም ብሆን ግጭት የሚያስቀር የትኛውም የሰላም እልባት ብፈለግ ሲሉ መክረዋል፡፡
የምርጫ ቦርዱ መከራከሪያ ነጥብ
በቅርቡ ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው አሁን ባስቸኳይ አደርጋለሁ ያለውን ጠቅላላ ጉባኤ እውቅና ነፍጎት ጉባኤውን ከ21 ቀናት በኋላ እንዲያደርግ ብጠይቅም ፓርቲው ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ አደርጋለሁ ያለውን ጉባኤ ማስጠንቀቂያውን ጥሶ ለማካሄድ መወሰኑ ተነግሯል፡፡ እንደ ፖለቲከኛ ገብሩ አስራት ህወሓት ይህን የምርጫ ቦርዱን ውሳኔ ማክበር ነበረበት፡፡
“ፓርቲዎች ጉባኤ ከማካሄዳቸው ከ21 ቀናት በፊት ማሳወቅ አለባቸው የሚለው ህግ በምርቻ ቦርዱ ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሰራ ነው” ያሉት ፖለቲከኛ ገብሩ ሌሎች ችግሮችም ካሉ መፍትሄው ድርድር ሊሆን ይገባ ነበር የሚል ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
አቶ ገብሩ በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው ልዩነትም ይህ ነው ይላሉ፡፡ “በሁለቱ ቡድን መካከል ያለው ልዩነት በተለይመም በእነ አቶ ጌታቸው በኩል ወደ ጦርነቱ ያስገባን ምንድነው የሚለውን ነጥብ ከመሰረቱ እንገምግም ሲሉ ሌላው ቡድን አመራሮቻችን በስብሷል የሚል ሃሳብ እያነሳ ነው” የሚል ይገኝበታል ነው ያሉት፡፡
ስለጉባኤው የፌዴራል መንግስት አስተያየት
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ህወሓት ዛሬ ከሰዓቱን ጉባኤውን መጀመሩን ተከትሎ የህወሓት ድርጊት የትግራይ ህዝብ ያገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደመንጠቅ ሲል ኮንኗል፡፡
የኮሚኒኬሽን አገልግሎት እንዳመለከተው ህወሓት በፕሪቶሪያ የተገባውን የአገሪቱን ህግ የማክበር መርህን መጣሱ ወደ ጥፋት የሚወስድ ነው ብሎታልም።
«የህወሓት ከሽብርተኝነት መሰረዝ መልካም ጅምር ነው» የህወሃት ባለሥልጣን
ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ህወሓት ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው አቅጣጫ ህጋዊ ሰውነቱን ካላገኘ መንግስት የመሆን እድል ስለማይኖረው ወደ ተለመደው ግጭት ሊያስገባ እንደሚችል አስጠንቅቀው አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ