“ቀለበታማ የፀሐይ ግርዶሽ″ በኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 18.06.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

“ቀለበታማ የፀሐይ ግርዶሽ" በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ድጋሚ የሚታየውና የቀለበት ቅርፅ ስላለው "ቀለበታማ" የሚል ስያሜ የተሰጠው የፀሐይ ግርዶሽ ከ18 ዓመታት የተከሰተ መሆኑን ለዶይቼ ቨለ "DW" የገለፁት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ፤ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የሚኖረው ደግሞ ከ146 ዓመታት በኋላ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:45

ግርዶሹን ያለመከላከያ ማየት አደጋ አለዉ

የፀሐይ ግርዶሽ ጨረቃ በፀሐይና በመሬት መካከል በመሆን ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ተጋርዳ ብርሃን መስጠት የማትችልበት ሁኔታ ሲኖር ወይም ጨለማ ስትሆን የሚፈጠር ክስተት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ድጋሚ የሚታየውና የቀለበት ቅርፅ ስላለው "ቀለበታማ" የሚል ስያሜ የተሰጠው የፀሐይ ግርዶሽ ከ18 ዓመታት የተከሰተ መሆኑን ለዶይቼ ቨለ "DW" የገለፁት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ፤ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የሚኖረው ደግሞ ከ146 ዓመታት በኋላ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡የፊታችን ዕሁድ ሰኔ 14,2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ በድጋሚ የሚታየው “ቀለበታማ የፀሐይ ግርዶሽ ከኮንጎ ተነስቶ፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክኝ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንን፣ ኢትዮጵያንና ኤርትራን አዳርሶ፣ ወደ መካከለኛው ምስራቅ በመሻገር የመንን፣ ሳውድ አረቢያና ፣ኦማንን ካካለለ በኋላ ወደ እስያ ሀገራት በመዝለቅ በደቡብ ፓኪስታን፣ በሰሜናዊ የህንድ ግዛትና ቻይና ውስጥ ከተከሰተ በኋላ ፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ እንሚያበቃም ይጠበቃል:: ከምዕራብ እስከ ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚታየው የፀሐይ ግርዶሹ ከጠዋቱ 12፡45 እስከ ቀኑ 6፡33 የሚቆይ ሲሆን ከረፋዱ 3፡40 ደግሞ ለ38 ሴኮንዶች ጨለማ እንደሚሆንም ከዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ግርዶሹ ከወለጋ ተነስቶ ከፊል ጎጃምን እንጅባራ፣ ግሽ አባይና ሌሎችንም አካባቢዎች የሚያዳርስ ሲሆን ጎንደር ደብረታቦር፣ ወሎ አላማጣ ፣መቀሌ በአዲስ አበባ እና ሌሎችም ስፍራዎች ለተወሰኑ ጊዜያት በጨለማ እንደሚዋጡም ነው የገለፁት፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ሰሎሞን በላይ እንዳሉት ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች የዓለም ሀገራት በተለየ መልኩ ላልይበላ ላይ ድቅድቅ ያለ ጨለማ ይሆናል፡፡ ላልይበላ በፀሃይ  አቀማመጥና ባላት ልዩ ተፈጥሮአዊ የመሬት ገፅታ ምክንያት የቀለበት ግርዶሹ ሙሉ ለሙሉ በአካባቢው እንደሚታይም ታውቋል:: ይህንንም ዓለማቀፉ የሥነ ፈለክ ማህበር የምርምር ቡድን ሳይንቲስቶች ጭምር አስቀድመው በጥናት በማረጋገጣቸው በርካታ ተመራማሪዎችና ቱሪስቶች ታሪካዊ ክስተቱን ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ  የመምጣት ዕቅድ ስለነበራቸው የዝግጅት አስተባባሪ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር፡፡ይሁን እንጂ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የጉዞ እገዳ ምክንያት ውጥናቸው ቢስተጓጎልም መንግሥት ዓለም በጉጉት የሚጠብቀውን ይህንን በረጅም ዓመታት የሚታይ ክስተት የአገሪቱን ገፅታ ለማስተዋወቅ በልዩ ዝግጅት እንደሚያከብረው ለዶይቼ ቨለ "DW" አስታውቀዋል:: በተባበሩት መንግሥታት ጥንታዊ የቅርስ መስህብነት ዕውቅና በተሰጣትና የበርካታ ሳይንቲስቶችንና ቱሪስቶችን ቀልብ በምትስበው ላልይበላ በሂደትም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በምሥራቅ አፍሪቃ የመጀመሪያውን የህዋ ስፔስ ቱሪዝም የማስፋፋት ስራ እንደሚጀመርም ዶክተር ሰለሞን ይፋ አድርገዋል::

ኢትዮጵያን ለስነ ፈለክ ምርምርና ለስፔስ ቱሪዝም የምናስተዋውቅበትን እንዲሁም የሀገሪቱ ስም በዓለም ዙሪያ ጎልቶ የሚወሳበትን ይኽ ዓይነቱን የተፈጥሮ ታሪካዊ ክስተት የእኛ ትውልድ ከረጅም ዓመታት በኋላ ለማየት በመታደሉ እድለኛ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ ለአጭር ሰዓታት የሚከሰተውን ይህን ሁነት ምንም ዓይነት መደናገጥ ሳያሳይ ጤናውን በማይጎዳ መልኩ በጥንቃቄ ሊከታተለው እንደሚገባም መክረዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለስነ ፈለክ ምርምርና ለስፔስ ቱሪዝም በምናስተዋውቅበት በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ጠንካራ የፀሃይ ጨረር /ራድዬሽን/ ከባድ የጤና ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑም ማንኛውም ሰው ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሹን ክስተት ያለ መከላከያ መነፅር ማለትም /ቪወር/ በባዶ ዓይን መመልከት እንደማይኖርበትም ማሳሰቢያ ተላልፏል:: ፎቶ ካሜራ የሚያነሱ ሰዎችም ቢሆኑ ለካሜራው ልዩ መከላከያ መጠቀም እንደሚገባቸው በማሳሰብ የቀለበት ግርዶሹ በጣም ደምቆ በሚታይባቸው ክልሎች ከወዲሁ የጨረር መከላከያ መነፅሮች እየተከፋፈሉ መሆኑን ዳይሬክተሩ ለዶይቼ ቨለ ጨምረው ገልፀዋል::

ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችና ሀገር ጎብኝዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የመጪውን ዕሁድ ታሪካዊ ክስተት ለመታደም ባይችሉም ኢንስቲትዩቱ ከፌዴራል እና ከአማራ ክልል መንግሥት እንዲሁም ከኮማንድ ፖስት ጋር በመነጋገር በላልይበላ በልዩ ሁኔታ ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ክስተቱ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ለምርምር የሚያተጋ የዓለም የህዋ ተመራማሪዎችን ለበለጠ ጥናት የሚጋብዝ እንዲሁም ለዘርፉ ገቢ የሚያመጣና የኢኮኖሚ ምንጭ ሊሆን ስለሚችል አቅም በሚፈቅደው መንገድ በሄሊኮፕተር እና በድሮውን ካሜራ ይህንን ታሪክ ክስተት በጥንቀቄ በመቅረጽ ለቀጣዩ ትውልድ ለጥናትና ምርምር ማስቀረት እንደሚኖርበትም ነው የተገለፀው፡፡ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ በኢትዮጵያ ከ 15ተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በየምዕተ ዓመቱ ሲከሰት መኖሩን ልዩ ልዩ የታሪክ ድርሳናት ላይ የሰፈሩ መረጃዎች መጠቆማቸውን የገለፁት ዶክተር ሰለሞን ለአብነትም በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት በወንጀል ጥፋት የሞት ብይን የተፈረደበት አንድ ሰው ውሳኔው ከመፅናቱ አስቀድሞ በአገሪቱ የፀሐይ ግርዶሽ መከሰቱን ተከትሎ ፍርዱ እንደተነሳለት የሚገልፅ ታሪክ መኖሩንም ጨምረው አስረድተዋል::


እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ 


 

Audios and videos on the topic