1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ታኅሣሥ 20 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 20 2012

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ዘንድሮ ዋንጫውን ከሦስት ዐሥርተ ዓመት ወዲህ በእጁ ሊያስገባ ዳር ዳር እያለ ነው። ቀጣዩን ተስተካካይ ጨዋታ የሚያሸንፍ ከኾነ ሊቨርፑል ከተከታዩ ላይስተር ሲቲ የሚራራቀው በ16 ነጥቦች ይኾናል ማለት ነው።  ጀርመናዊው አሰልጣኝ ግን ለመደሰት ገና ነን ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3VW1v
Club World Cup - Final - Liverpool v Flamengo | Pokalsieger
ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ዘንድሮ ዋንጫውን ከሦስት ዐሥርተ ዓመት ወዲህ በእጁ ሊያስገባ ዳር ዳር እያለ ነው። ቀጣዩን ተስተካካይ ጨዋታ የሚያሸንፍ ከኾነ ሊቨርፑል ከተከታዩ ላይስተር ሲቲ የሚራራቀው በ16 ነጥቦች ይኾናል ማለት ነው።  ጀርመናዊው አሰልጣኝ ግን ለመደሰት ገና ነን ብለዋል። በበዓላት ሰሞን ረፍት ላይ በሚገኘው ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን በአዲስ አሰላለፍ ለመመለስ ዝግጅት ላይ መኾኑ ተነግሯል። የረዥም ጊዜ የብሔራዊ ቡድኑ ተከላካይ ጄሮም ቦዋቴንግ የውድድር ዘመኑ ኹለተኛ አጋማሽ ሲጀምር ከባየር ሙይንሽን ጋር መቆየቱ አለየለትም።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ዳግም ድል ቀንቶት ወደ ዋንጫ የሚያደርገውን ግስጋሴ አፋጥኗል። ትናንት ከዎልቨርሀምፕተን ጋር ባደረገው ጨዋታ1 ለ0 ያሸነፈው ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረውም ቢኾን ከተከታዩ ላይስተር ሲቲ በ13 ነጥብ ርቆ በአንደኛነት እንደሰፈረ ነው። 20 ጨዋታዎችን ያከናወነው ላይስተር ሲቲ 42 ነጥብ አለው።

Club World Cup - Final - Liverpool v Flamengo | Tor
ምስል AFP/M. Abumunes

ሊቨርፑል ቀደም ሲል ላይስተር ሲቲን በሜዳው 4 ለ0 ያሸነፈበት ድንቅ ብቃቱ ትናንት በሜዳው አንፊልድ ዎልቭስ ላይ ሲኾን በጠባብ ልዩነት ወደ ማሸነፉ ተቀይሯል። ዎልቨርሀምፕተን 30 ነጥብ ይዞ የሚገኘው 7ኛ ደረጃ ላይ ነው። ማንቸስተር ሲቲ ሼፊልድ ዩናይትድን  ትናንት 2 ለ0 አሸንፎ ሦስተኛ ደረጃውን አስጠብቋል። ከላይስተር ሲቲ የሚበለጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው።

ሊቨርፑሎች የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ በእጃቸው ያስገቡት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1990 ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በፕሬሚየር ሊጉ ዋነኛ ተፎካካሪ ቢኾኑም፤ ላለፉት 30 ዓመታት ዋንጫው ርቋቸው ቆይቷል። አኹን ከየትኛውም ቡድን በተሻለ ዋንጫውን ለመውሰድ የተቃረቡ ቢኾንም፤ ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ግን ውድድሩ ገና ባለማለቁ ገና ካኹኑ ወደ ፌሽታ አንገባም ብለዋል።

በነገራችን ላይ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕን የፈረንሳዩ ፓሪ ሴንጄርሜን  ቡድን ከሊቨርፑል ነጥሎ ሊወስዳቸው ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል። ለ ዲስስፖርት የተሰኘው የድረገጽ ጋዜጣ እንደዘገበው ከኾነ፦ በገና ሰሞን ዬርገን ክሎፕ ከፈረንሳዩ ቡድን የስልክ ጥሪ ደርሷቸዋል። በጥሪውም ሊቨርፑልን ትተው ወደ ፓሪ ሴንጄርሜን እንዲያቀኑ ተጠይቀዋል። ጀርመናዊው አሰልጣኝ ግን በሊቨርፑል ቆይታቸው ደስተኛ እንደኾኑ በመግለጥ ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል። ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሊቨርፑል አሰልጣኝ ኾነው ለመቆየት ውል መፈረማቸው ቀደም ሲል ተዘግቧል።

ትናንት በተደረጉ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ቸልሲ አርሰናልን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ በርንሌይን 2 ለ0 ድል አድርጓል። 35 እና 31 ነጥብ ያላቸው ቸልሲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በተከታታይ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። 

Fußball Bundesliga | Jerome Boateng, Bayern München
ምስል picture-alliance/dpa/Sven Simon/Frank Hoermann

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የኋላ መስመር ተከላካይ ጄሮም ቦዋቴንግ በባየር ሙይንሽን የመቆየት ዕድሉ ጥያቄ አጭሯል። አዲሱ የባየር ሙይንሽን አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ኪከር ከተሰኘው የድረገጽ ጋዜጣ ጋር ዛሬ ባደረጉት ቃለመጠይቅ አዲስ የቀኝ ተከላካይ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። የ31 ዓመቱ ተከላካይ ጄሮም ቦዋቴንግን በተመለከተ ተጠይቀው «በቡድኑ ውስጥ መቆየት የእሱ ውሳኔ ነው» ብለዋል።

ከገና እና አዲስ ዓመት ረፍት በኋላ በሚጀምረው የቡንደስሊጋ ግጥሚያ ጄሮም ቦዋቴንግ ቦታ ይኖረው እንደኾን ተጠይቀው የመለሱት በገደምዳሜ ነው። «ከእሱ ጋር ሁልጊዜም ችግሮችን በግልጽ ነው የምንነጋገረው። ሳይሰለፍ ሲቀር ብዙም ቁብም አይሰጠውም፤ ይቀበልሃል። ከቮልፍስቡርግ ጋር ስንጫወት ተቀይሮ እንደገባ ብዙም ሳይቆይ  ለባየርን ለመጫወት ብቃት እንዳለው አሳይቷል። ግን ውሳኔው የራሱ ነው። ጄሮም ስለ ወደፊት ዕድሉ ራሱ መወሰን ይገባዋል» ሲሉ ተናግረዋል።   

የኦስትሪያው የግራ ተከላካይ ዳቪድ አላባ በባየርኑ አሰልጣኝ ዐይን የመሀል ተከላካይ ነው። «እያሻሻለ የመጣው ነገር የተከላካዮች ዋና ያስብለዋል» ብለዋል። «በእሱ በጣም ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም ኳስ ለማስጣል እና ኳሷን ይዞ ጨዋታ ለመመስረት የሚያሳየው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። ስለኾነም እዚህ ቦታ ላይ የእሱ መኖር ወሳን ነው» ሲሉ በተከላካይ መስመር ሊያጡት የማይፈልጉ ተጨዋች መኾኑን ገልጠዋል። ከ27 ዓመቱ ተከላካይ ከጄሮም ቦዋቴንግ በተለየ መልኩ አወድሰውታል።

Äthiopien | Judo mit Dr. Tsegahe Degneh
ምስል privat

ለረዥም ጊዜ የቀኝ መስመር ተከላካይ ኾኖ ላገለገለው የ24 ዓመቱ ጀርመናዊ ተከላካይ ዮሹዋ ኪሚሽም ምልከታቸው ለየት ያለ ነው። «እዚህ ቦታ ላይ ከዚህ ቀደም ተጫውቷል ወደፊትም ለብሔራዊ ቡድኑ ይጫወታል። የአማካይ ተከላካይ መስመር ላይም ላቅ ያለ ብቃት አለው። ጨዋታን ማንበብ ይችላል፤ ከኳስ ጋርም ኾነ ወደ ኳስ በመሄድ እንቅስቃሴው ጥሩ ነው» በማለትም ዮሹዋ ኪሚሽን አድንቀውታል።

በጀርመን ሃገር ያለውን የስፖርት ልምድ ለኢትዮጵያ በሚጠቅም ሁኔታ ለማዳበር የሚያስችል ስልጠና በአዲስ አበባ ሰሞኑን ተሰጥቷል። የስፖርት ሕግ ምን መምሰል እንዳለበት፣ ዘርፉን በምን መልኩ ማዘመን እንደሚቻል፣ ትምህርትና ስፖርት እንዴት መተሳሰር እንዳለባቸው፣ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልን እንደምን ማስቀረት እንደሚቻልና ስፖርትን እንዴት የሃገር ኢኮኖሚ ማሳደጊያ ማድረግ ይቻላል በሚል ነው። በጀርመን ሀገር ለ30 ዓመታት የኖሩት ዶክተር ጸጋየ ደግነህ ስልጠናውን ባለፈው ሳምንት ለስፖርት ቤተሰቦች ሰጥተዋል። የአዲስ አበባው ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ በስልጠናው ቦታ ተገኝቶ ቀጣዩን ዘገባ ልኮልናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ