ስፖርት፤ መስከረም 26 ቀን፣ 2012 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 07.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

ስፖርት፤ መስከረም 26 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

በዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ቡድን ከካታር የአየር ሁኔታ ጋር ሊስማማ በሚችል የአየር ጠባይ ውድድሩን ቢያካሂድ የበለጠ ውጤት ሊገኝ ይችል እንደነበረ ተገለጠ። የኢትዮጵያ ቡድን ከዓለም አምስተኛ ከአፍሪቃ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:02

ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ቡድን ከካታር የአየር ሁኔታ ጋር ሊስማማ በሚችል የአየር ጠባይ ልምምዱን ቢያካሂድ የበለጠ ውጤት ሊገኝ ይችል እንደነበረ ተገለጠ። የኢትዮጵያ ቡድን ከዓለም አምስተኛ ከአፍሪቃ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው። ከዶሃው ውድድር ውጤት በኋላ በአትሌቶች እና የስልጠና ኹኔታ ላይ የተነሱ ነጥቦች አነጋጋሪ ኾነዋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን ዘንድሮ በሰባተኛ ዙር ጨዋታው ሽንፈት ቀምሷል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል የማታ ማታ ድል ተጎናጽፎ አሁንም ድረስ የሚረታው እንደጠፋ አስመስክሯል።  

ለአንድ ሳምንት ያህል የዘለቀው የዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ትናንት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ብዛት ከአፍሪቃ ሁለተኛ ከዓለም የአምስተኛ ደረጃን አግኝታለች። በዶሃው ውድድር ዩናይትድ ስቴትስ 14 የወርቅ፤ 11 የብር እና 4 የነሐስ በጥቅሉ 29 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የአንደኛ ደረጃን አግኝታለች። ጎረቤት ኬንያ 5 የወርቅ፤ 2 የብር እንዲሁም 4 የነሐስ በጥቅሉ 11 ሜዳሊያዎችን አግኝታ ሁለተኛ መኾን ችላለች። ጃማይካ በ12፤ ቻይና በ9 የሦስተኛ እና የአራተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። 2  የወርቅ፤ 5 የብር  እንዲሁም 1 የነሐስ በጥቅሉ 8 ሜዳሊያ ያገኘችው ኢትዮጵያ በዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ብሪታንያ እና ጀርመንን በልጣ የአምስተኛ ደረጃን ይዛለች። በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት አዘጋጅ እና አቅራቢ ጋዜጠኛ ምሥጋናው ታደሰ ኢትዮጵያ ውጤቷ ከዚህም የተሻለ ይኾን ነበር ብሏል። 

በዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ለኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን ሌሊሳ ደሲሳ እና ሞስነት ገረመው ወርቅ እና ብር ሲያስገኙ፤ ሙክታር እድሪስ በ5000 ሜትር ወርቅ እንዲሁም ሰለሞን ባረጋ የብር ሜዳሊያ አስገኝተዋል። በ10,000 ሜትር ወንዶች ዮሚፍ ቀጄልቻ፤ በተመሳሳይ ርቀት በሴቶች ለተሰንበት ግደይ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ኾነዋል። ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳሊያዎች ያገኘችው በ1500 ሜትር የሴቶች ውድድር በጉዳፍ ጸጋዬ ነሐስ እና በለሜቻ ግርማ የ3000 ሜትር መሰናክል ውድድሮች ነው። ለሜሳ በዓለም አቀፍ መድረክ በመሰናክል ውድድር ላይ በርቀቱ ያስመዘገበው ውጤት በልዩ ተመዝግቦለታል። በተለይ ውድድሩን እጅግ በጠበበ ኹኔታ ለጥቂት ተቀድሞም ቢኾን በሁለተኛነት ያጠናቀቀበት ቁርጠኝነት በርካቶችን አስደምሟል።

እግር ኳስ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ውጤቶች አስደማሚ ነበሩ። ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር የገጠመው ላይፕሲሽ ከሽንፈት ለጥቂት ተርፏል። አጓጊ በነበረው የቅዳሜው ግጥሚያ 67ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ኬቪን ፎላንድ ለሌቨርኩሰን የመጀመሪያዋን ግብ ከመረብ በማሳረፍ ደጋፊዎችን አስፈነደቀ። ኾኖም ብዙም ሳይቆይ በ79ኛው ደቂቃ ላይ ክሪስቶፈር ንኩንኩ ለላይፕሲሽ አቻ የምታደርገውን ግብ በማስቆጠር ቡድኑንን ከሽንፈት ታድጓል።  እንዲያም ኾኖ ግን ላይፕሲሽ ከነበረበት የ2ኛ ደረጃ ወደ አራት ዝቅ ብሏል። ሦስተኛ ደረጃ ከሚገኘው ባየር ሙይንሽን እና አራተኛ ከኾነው ፍራይቡርግ ጋር እኩል 14 ነጥብ ይዞ ላይፕሲሽ በግብ ክፍያ ደረጃው አምስተኛ ነው።

ከባየር ሙይንሽን በስተቀር ባየር ሌቨርኩሰንም ኾነ ላይፕሲሽ ሁለቱም ለሻምፒዮንስ ሊግ ተጫውተው ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ሌቨርኩሰኑ ባለፈው ሳምንት በሻምፒዮንስ ሊግ በጁቬንቱስ 3 ለ0 ሲሸነፍ፤ ላይፕሲሽም በፈረንሳዩ ኦሎምፒክ ሊዮን የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። በሻምፒዮንስ ሊጉ የእንግሊዙ ቶትንሀምን 7 ለ2 ጉድ ያደረገው ባየር ሙይንሽን በቡንደስ ሊጋው በተራው በሆፈንሀይም ጉድ ኾኗል።  ዘንድሮ ባየር ሙይንሽን የመጀመሪያ ሽንፈቱን በሆፈንሀይም 2ለ 1 ቀምሷል። በድል ጎዳና የሚገሰግሰው ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ ትናንት አውስቡርግን በሰፋ ልዩነት 5 ለ1 አሸንፎ ነጥቡን 16 በማድረስ በደረጃ ሰንጠረዡ የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል። በጀርመን ቡንደስሊጋ የደረጃ ሰንጠረዡ ልዩነት ከመሪው ሞይንሽን ግላድባኅ እስከ 10ኛ ደረጃ የሚገኘው ሔርታ ቤርሊን የስድስት ብቻ ነው።

በአንጻሩ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የመሪው ሊቨርፑል እና ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ የነጥብ ልዩነት ስምንት ነው። ማንቸስተር ሲቲ ትናንት በዎልቨርሀምፕተን 2 ለ0 መሸነፉ ለመሪው ሊቨርፑል ሲሳይ ነው የኾነለት። ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት ባለቀ ሰአት ባገኘው ፍጹም ቅጣት ምት ላይስተር ሲቲን 2 ለ1 አሸንፎ ዘንድሮ በስምንቱም ተከታታይ ጨዋታዎች ለአንድም ጊዜ ሳይበገር ወይንም ነጥብ ሳይጥል መዝለቅ ችሏል። በዚህም ነጥቡን 24 አድርሶታል። በጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ የሚመራው ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊጉም ድል ቀንቶታል። ሬድ ቡል ሳልዝቡርግን 4 ለ3 ነው ያሸነፈው። ቸልሲ ሳውዝሀምፕተንን 4 ለ1 ሲያሸንፍ፤ አርሰናል በርመስን 1 ለ0 አሸንፏል። ማንቸስተር ዩናይትድ በኒውካስትል ዩናይትድ የ1 ለ0 ሽንፈት ደርሶበታል። ፈተና የበዛበት ቶትንሀም በብራዮተን 3 ለ0 ተበራይቷል። በደረጃ ሰንጠረዡ ማንቸስተር ሲቲ 16፤ አርሰናል 15 ነጥብ ይዘው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ናቸው። ላይስተር ሲቲ፤ ቸልሲ እና ክሪስታል ፓላስ 14 ነጥብ ይዘው ከ4ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች