ስጋት በእየሩሳሌም | ዓለም | DW | 28.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ስጋት በእየሩሳሌም

በእስራኤል የአይሁዳውያን ምኩራብ ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ እየሩሳሌም የግጭት ስጋት ውስጥ ተዘፍቃለች። የዶይቼ ቬሌ ወኪል የሆነችው ታኒያ ክራመር በዘገባዋ ለአንዳንዶች አሁን በከተማዋ የሚታየው ስጋት ሁለተኛውን ህዝባዊ አመጽ ወይም ኢንቲፋዳ ያስታውሳል ትላለች።እሸቴ በቀለ ዘገባውን እንዲህ አሰናድቶታል።


በምዕራባዊ እየሩሳሌም ሁሉም ነገር እንደ ወትሮው ነው። ቢሆንም ባለፈው ሳምንት በአይሁዳውያን ምኩራብ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ በከተማዋ ውጥረት ነግሷል። እስራኤላዊው የእየሩሳሌም ነዋሪ ጊልበርት ግላንዝ ይህ ውጥረት ከሚሰማቸው አንዱ ነው። ግላንዝ መሳሪያ ታጥቋል፤ልጆቹን ትምህርት ቤት ካደረሰ በኋላ ቅጥሩ በአግባቡ መዘጋቱን ያረጋግጣል። እሱና ቤተሰቦቹ ሰዎች ወደ ሚበዙበት አካባቢ በምሽት መሄድ አቁመዋል። ባለፈው ሳምንት በፍልስጤም ታጣቂዎች በአይሁዳውያን ምኩራብ ላይ በፈጸሙት ጥቃት አራት ራቢዎችና አንድ ፖሊስ ከተገደሉ በኋላ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ይመስል ነበር። ከዚያ ቀደም ብሎ የከተማ ባቡር በመጠበቅ ላይ ባሉ መንገደኞች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሶስት እስራኤላውያን ሞተዋል። በቀኝ አክራሪ አይሁዳዊ ይሁዳ ግሊክ ላይ የግድያ ሙከራ ከተደረገ በኋላ ደግሞ ወደ አል አቅሳ መስጊድ መግባት ተከልክሎ ነበር።


ከአመታት በፊት በከተማዋ የተፈጠሩ ተመሳሳይ ሁኔታዎችን የሚያስታውሰው ጊልበርት ግላንዝ አሁን ያለው የእየሩሳሌም የጸጥታ ሁኔታ ስጋት ፈጥሮበታል። ''ችግሩ መቼ ጥቃት እንደሚፈጸም አታውቅም። በአንድ የሚታወቅ ፖለቲካዊ ቡድን ታቅዶ የሚፈጸምም አይደለም። ማንም ሊሆን ይችላል-በየትኛው ቦታም ሊሆን ይችላል። ''
ጊልበርት ግላንዝ መንግስት እና የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ዙሪያቸውን የታጠሩት ትምህርት ቤቶች በድጋሚ እንዲታጠሩ ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥርም እንዲደረግ ይፈልጋል። ያለፈውን ሳምንት ጥቃት በ'እየሩሳሌም ላይ የታወጀ ጦርነት' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በከተማዋ ህግና ስርዓት መልሶ ለማስፈን ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ ቃል ገብተው ነበር። እናም የከተማዋ የጸጥታ ቁጥጥር ከፍ እንዲል ተደረገ። ተጠባባቂ የጸጥታ ሃይሎችም መሳሪያ እንዲታጠቁ ተፈቀደላቸው።
ወጣቷ እስራኤላዊት እናት ኪናሬት ሚልግሩም ግን የጸጥታ ቁጥጥሩን ማጥበቅ የሚፈይደው ነገር የለም ብላ ታምናለች።
''የምዕራብ እየሩሳሌም ነዋሪዎች በምስራቁ የከተማዋ ክፍል የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ያሉበትን ሁኔታ አያውቁም ብዬ አስባለሁ። ሁኔታው እንዲሁ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ይሰማኛል። ሙሉ ዜግነት ሊሰጣቸውና ባለሙሉ መብት ሊሆኑ ይገባል ብዬ አስባለሁ። ያ ለሁሉም የተሻለ ይሆናል። አሁን ያለው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነው። እናም ቢቆጡ አልፈርድባቸውም። ይህ ደግሞ ልጆቼን ከማን እንደምጠብቃቸው ስለማላውቅ ለእነሱን ከሚመጣው አደጋ መጠበቅ አስቸጋሪ ሆኖብኛል።''
በምዕራባዊ እየሩሳሌም ምግብ ቤቶችና ሱቆች የተለመደ ስራቸውን ቢከውኑም ከተማዋ ከወትሮው በባሰ ለሁለት ተከፍላለች። በእስራኤላውያንና ፍልስጤማውያን መካከል በተፈጠረው ውጥረት ውስጥ በእየሩሳሌም ከተማ ሃር ኑፍ መንደር የሚገኘው የአይሁዳውያን ምኩራብና የአል አቅሳ መስጊድ ቦታ አላቸው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ቀኝ ዘመም አክራሪ ይሁዳውያን 'የጽዮን ተራራ' ተብሎ የሚታወቀውን የእምነቱ ቅዱስ ስፍራ መጎብኘትና መጸለይ እንዲፈቀድላቸው ይወተውታሉ። ለፍልስጤማውያን በእስልማና ሶስተኛው ቅዱስ ስፍራ በሆነው የአል-አቅሳ መስጊድ እንደፈለጉ መጎብኘት አለመቻል በተለይም የአርብ ጸሎት መከልከል ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም።


የሁለት ልጆች አባት የሆነው ፍልስጤማዊ ከማል አቡ ሰላም በሲልዋን መንደር ከሚገኘው ቤቱ ሆኖ የአል-አቅሳ መስጊድን መመልከት ይችላል። ይሁዳ ግሊክን ለመግደል ሙከራ አድርጓል የተባለው ፍልስጤማዊ በእስራኤል የጸጥታ ሰራተኞች ከሚኖርበት የቤተሰቦቹ ቤት በጥይት የተገደለው ከዚሁ የሲልዋን መንደር ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በመንደሩ ያለውን ሁኔታ እንደተቀየረ አቡ ሰላም ይናገራል። ''በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ አለ። ሰዎች የመታጎር ስሜት ይሰማቸዋል። ወደ አል-አቅሳ መስጊድ ለጸሎት መሄድ አንችልም። ብንሄድ እንኳ በእስራኤል ጦር እንሰደባለን፤እንዋረዳለን። ድንጋይ ወርውሬ ሰዎችን መጉዳት አልፈልግም። ቢሆንም ሰዎች እጅግ ተማረዋል።'' ወጣቱ ፍልስጤማዊ በምዕራባዊ እየሩሳሌም ሚገኙ ኩባንያዎች በጽዳት ሰራተኝነት ያገለግል ነበር። አሁን ግን በጽንፈኛ አይሁዳውያን ጥቃት ይደርስብኛል ብሎ በመስጋቱ ስራውን አቁሟል።ይህ ግን የአቡ ሰላም እጣ ፈንታ ብቻ አይደለም። በርካታ ፍልስጤማውያን ለስራም ሆነ ለገበያ ወደ ምዕራባዊ እየሩሳሌም መሄድ የከተማ ባቡር መጠቀምም አቁመዋል። ካሁን ቀደምም ቢሆን በምስራቃዊ እና ምዕራባዊ እየሩሳሌም መካከል ጠንካራ ግንኙነት አልነበረም። አሁን ግን በእየሩሳሌም የሚኖሩ እስራኤላውያንና ፍልስጤማውያን በከፋ ደረጃ ተከፋፍለዋል።

ታንያ ክራመር / እሸቴ በቀለ
ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic