1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

ሳይንሳዊ አመጋገብ ለተሻለ ውጤት

ረቡዕ፣ ግንቦት 3 2014

እግርኳሳችን ለውጤቱ አለማማር ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ዘመኑ የወለደው ቴክኖሎጂን አለመጠቀም እንደሆነ ይነገራል። ከነዚህም አንዱ በባለሞያ የተደገፈ የተንቀሳቃሽ ምስል ትንተና ይገኝበታል ይላል የስፖርት ጋዜዘኛና ተንታኝ መንሱር አብዱልቀኒ።

https://p.dw.com/p/4B88m
ምስል ISSOUF SANOGO/AFP

ሳይንሳዊ አመጋገብ ለተሻለ ውጤት

የአገራችን እግር ኳስ በዘርፈ ብዙ ችግሮች የተተበ እንደሆነ ትችቶች ይቀርቡበታል። ካሉት ችግሮች ውስጥ በክለቦችና በብሔራዊ ቡድኑ ጭምር ሳይንሳዊ የስፖርት አመጋገብ ያለመኖርና የተንቀሳቃሽ ምስል ትንተና አለመኖር ተጠቃሽ ናቸው። በዛሬው ዝግጅታችን በዚህ ርእሰ ጉዳይ ጥናታዊና ሞያዊ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉን ዶክተር ሞላ ደዩ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም ታዋቂውን የስፖርት ጋዜጠኛና ተንታኝ መንሱር አብዱልቀኒ እንግዳችን አድርገናቸዋል። 

“ኬሻ በእህል ይቆማል”፤ “ሰው የበላውን ይመስላል” የሚሉና ሌሎች በኅብረተሰባችን ዘንድ የሚዘወተሩ አባባሎች አሉ። እነዚህ አባባሎች ምግብ በሰውነታችን ግንባታ ያለውን ሚና ቀለል አድርገው የሚያስረዱ ናቸው። በተለይም እግር ኳሳችን ውጤታማ እንዳይሆን ካደረጉት አንዱ ለእንቅስቃሱው የሚመጥን ሳይንሳዊ አመጋገብ ያለመኖር እንደሆነ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሞላ ደዩ ይናገራሉ።

ዕውቁ የስፖርት ጋዜጠኛና ተንታኝ መንሱር አብዱል ቀኒ ዶክተር ሞላ ባሉት ሐሳብ ይስማማል። ሰሚ ቢያጣም በስፖርት ፕሮግራሞቹ ያለመሰልቸት እንደወተወተ በማከል ጭምር።
ዶክተር ሞላ የአርባ ምንጭ ከነማ እግር ኳስ ቡድን የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉ በተጠየቁበት ጊዜም ሳይንሳዊ የስፖርት አመጋገብ ተግባራዊ ለማድረግ ሞክረው እንደነበረ አጫውተውናል።

ባደጉ አገራት የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች ሳይንሳዊ የስፖርት አመጋገብ ለውጤት ከሚያደርሷቸው ተግባራት በዋነኝነት እንደሚጠቀስ የገለጸልን መንሱር እያንዳንዱ ተጫዋች እንደሚያፈሰው ጉልበትና እንደሚጠይቀው ፍጥነት መሰረት ተደርጎ ሳይንሳዊ የስፖርት አመጋገብ ተግባራዊ እንደሚደረግ አጫውቶናል።

ዶክተር ሞላ ከአንዲት የሆላንድ ተመራማሪ በጋራ በካሄዱት ጥናት ከ1 እስከ 5 ዓመት በሆናቸው ህጻናት አመጋገብን መሰረት ያደረገ ጥናት አካኺደው ህጻናቱ ብቃታቸው ከሆላንድ ህጻናት ጋ ተቀራራቢ ሊባል የሚችል ውጤት ማሳየቱን ገልጠውልናል። በአንጻሩ ከዛበላይ ባለ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ግን ብቃታቸው እያሽቆለቆለ እንደሚሄድ የጥናት ውጤቱ እንዳሳየ አብራርተዋል። ይህም በሀገሪቱ ህጻናትን የመንከባከብ ባህልን ሲያመለክት፤ ከዛ በኋላ ባለው እድሜ ግን አመጋገቡ ቀጣይነት እንደማይኖረው የሚያሳይ ነው ብሏል። ከእንደዚህ አይነት ማኅበረሰብ የወጣ የእግር ኳስ ተጫዋች በሳይንሳዊ አመጋገብ ስለማይደገፍ ውጤታማ እንደማይሆንም አክሏል።

ዶክተር ሞላ በ4 የኢትዮጵያ የስፖርት ቡድኖች ላይ ደማችን ውስጥ ስለሚኖሩ የደም ህዋሳት መጠንና በደማችን ስላሉ ኬሚካሎች ከእንቅስቃሴያችንና ብቃታችን አንጻር ጥናት አድርገዋል። ይህ ጥናት በእንግሊዝኛ (ኮለክቲቭ ብለድ ካውንትና ብለድ ኬሚስትሪ) ይባላል። ውጤቱ እንደሚያመለክተውም የስፖርተኞቹ በቀጥታ አመጋገባችው ሳይንሳዊ ከአለመሆኑ ጋ የሚያያዝ እንደሆነ ነግረውናል።

ሌላው እግርኳሳችን ለውጤቱ አለማማር ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ዘመኑ የወለደው ቴክኖሎጂን አለመጠቀም እንደሆነ ይነገራል። ከነዚህም አንዱ በባለሞያ የተደገፈ የተንቀሳቃሽ ምስል ትንተና ይገኝበታል ይላል የስፖርት ጋዜዘኛና ተንታኝ መንሱር አብዱልቀኒ።

በስፖርት ሳይንሳዊ አመጋገብና በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ ሳይንሳዊ ትንተና ላይ ያተኮረውን የዛሬው ዝግጅታችን በዚሁ አበቃ። 

Athiopien Fußballspiel | Äthiopien vs. Elfenbeinküste
ምስል DW/O. Tadele
Äthiopien Äthiopische Fußballnationalspielerin Eyerusalem Negash
ምስል Eyerusalem Negash


ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ