1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

ለምንድነው ዓለም የሱዳንን የእርስ በእርስ ጦርነት ችላ ያለው?

ቅዳሜ፣ ሰኔ 15 2016

ሱዳን ውስጥ በጦርነት ጊዜ የሚፈጸሙ አረመኔያዊ ድርጊቶች ዝርዝር በርክተዋል፣ እጅግ እየበዛም በመሄድ ላይ ነው። ምንም እንኳን የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ ቢያቀርብም የእርዳታና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት በሀገሪቱ ሁኔታዎች አልተሻሻሉም።

https://p.dw.com/p/4hNCZ
ፎቶ ከማኅደር፤ አልፋሽር ከተማ
ባለፈው ዓመት በጥቃት የወደመው ዳርፉር ግዛት የአል ፋሽር የገበያ ስፍራ ፎቶ ከማኅደር፤ አልፋሽር ከተማምስል AFP

የሱዳን ጦርነት

የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች በከባድ መሳሪያ ተደብድበዋል፤፤ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል፤ መንገዶች በአስከሬን ተሞክተዋል፤ እርዳታ ማድረስ አልተቻለም፤ ስልታዊ የሆነ ጾታዊ ጥቃት እና ሌሎች የጦር ወንጀሎች እየተፈጸሙ ነው። ሱዳን ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነቱ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ከተጀመረ አንስቶም ወደ 16 ሺህ ገደማ ሰዎች ተገድለዋል።

ከዚህም ሌላ የሱዳን ጦርነት በዓለም የከፋ የተባለውን የመፈናቀል ቀውስ አስከትሏል። 10 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ ለደህንነቱ ሲል ከየመኖሪያ አካባቢው ለመፈናቀል ተዳርጓል። ከሳምንት በፊት የተመድየስደተኞች ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ከሀገራቸው ከተፈናቀሉት ሱዳናውያን 70 በመቶው ለመኖር የሚታገሉት ጭራሽ የርሃብ አደጋ ባለባቸው አካባቢዎች ነው።  

ምንም እንኳን የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ ቢያቀርብም የእርዳታና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት በሀገሪቱ ሁኔታዎች አልተሻሻሉም።

ጦርነቱ እንዴት ተጀመረ?

ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር አንስቶ ሁለቱ የሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች ማለትም የሱዳን ወታደራዊ ኃይል በምሕጻሩ SAF እንዲሁም ፈጥኖ ደራሽ በምሕጻሩ RSF እየተዋጉ ነው። እነዚህን ኃይሎች ነፍጥ ወደማንሳት ያደረሳቸው የሀገሪቱን ሥልጣን በመጋራት ሂደት አለመስማማታቸው መሆኑ ተደጋግሞ ይገለጻል። በጀነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው ወደ 200 ሺህ የሚገመት ሠራዊት ያሉት የሱዳን ጦር እንደሀገሪቱ መደበኛ ጦር ኃይል የሚቆጠር ነው። በአንጻሩ በጀነራል መሀምዳን ዳጋሎ ሥር የሆነውና ከ70 እስከ መቶ ሺህ ተዋጊዎች እንዳሉት የሚነገርለት ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ደግሞ እንደሽምቅ ተዋጊ ያለ መሆኑ ይነገራል።

በቅርቡ ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በተለይ በሱዳን ምዕራባዊ ክፍል ዳርፉር ግዛት ይዞታውን እያጠናከረ በመሄድ ላይ ነው። ሚያዚያ ወር ውስጥ ስልታዊ ጠቀሜታ እንዳላት የሚነርላት ሚሊት ከተማን ተቆጣጥሯል፤ አሁን ደግሞ ወደ1,5 ሚሊየን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችውን ኤል ፋሸር ከተማን በከበባ ውስጥ ከቷል። ዳርፉር በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ከሚኖሩት አንዱ አዳም ሮጃል ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገረው እነዚህን የሚዋጉ ኃይሎች ሕዝቡ እንደጀግና አይመለከታቸውም። እንደውም ለራሳቸው ፍላጎት የሚፋለሙ በማለት ይተቻቸዋል። በዚህ መሀል ግን ለችግርና ለመከራ የተዳረገው የሱዳን ሕዝብ መሆኑን በመቆርቆር ይገልጻል። «ሕዝቡ ያለውን ነገር ሁሉ አጥቷል። ይህ ቀውስ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ቃላት ሊገልጹት አይችሉም።» ባይ ነው አዳም ሮጃል።

የተመድ አምባሳደር ወቀሳ፤ «ይቅር የማይባል ዝምታ»

ምንም እንኳን ሱዳንውስጥ ጥቃቱ ተጠናክሮ ቢቀጥልም፤ በርካታ የሰብአዊ መብቶች እና የረድኤት ድርጅቶች እንደሚሉት፤ የቀረው ዓለም ይህን ግጭት ችላ ብሎታል። ባለፈው ሚያዝያ ወር ጦርነቱ የተቀሰቀሰበት አንደኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ዓለም አቀፍ የለጋሾች ጉባኤ ተካሂዶ 2,1 ቢሊየን ዶላር ለሱዳን የሰብአዊ ርዳታ ቃል ተገብቶ ነበር። ሆኖም ግን በቀጣዩ ወር ማለቂያ በተጻፈ ደብዳቤ የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ አባላት ቃል ከተገባው ያገኙት 16 በመቶውን ብቻ መሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን አመልክተዋል።

የሱዳን ቀውስ ችላ መባሉን በይፋ ከተቹት መካከልም በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ለኒዮርክ ታይምስ በግልጽ «ይቅር የማይባለው ዝምታ በሱዳን ላይ» በሚል አስተያየታቸውን ጽፈዋል። «የእርስ በእርስ ጦርነት ሱዳንን የእውን ሲኦል አድርጓታል» ያሉት አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፤ ምንም እንኳን የእርዳታ ድርጅቶች የሀገሪቱ ሰብአዊ ቀውስ በዓለም ከሚታዩት የከፉ ሁኔታዎች አንዱ እንደሆነ ቢገልጹም ለሱዳን ሕዝብ የተሰጠው ትኩረት እና እርዳታ ግን በጣም ትንሽ ነው በማለት ወቅሰዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ አልፋሽር
በሱዳን ዳርፉር አልፋሽር የተፈናቀሉ ሱዳናውያን መጠለያ ፎቶ ከማኅደር፤ አልፋሽር ምስል AFP

ለምንድነው ለሱዳን ትኩረት ያልተሰጠው?

ባለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ሜሊሳ ፍሌሚንግ ይህን ጥያቄ በይፋ የጠየቁበትን ጽሑፍ አውጥተዋል። እሳቸው ባቀረቡት የሙግት ነጥብ፤ እንደውም ሰዎች በጥቃቶች የሰለባዎች ቁጥር የመጨመሩ ዜና ቀልባቸውን የሚስበው ይመስላል ነው ያሉት። እንዲህ ያለው የተጎጅዎችን ቁጥር የመስማቱ አባዜም በተለያዩ ችግሮች ማለትም ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ሰለባዎች አንስቶ እስከ ጋዛ እና ዩክሬን ጦርነት ሊሰፋ እንደሚችልም አመላክተዋል። እናም የሱዳን ግጭት ጉዳይም ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደማይችልም ሞግተዋል። ጄኔቫ የሚገኙት ገለልተኛ የሱዳን ጉዳይ ተንታኝ ሮማን ዲከርት እንዲህ ያለው ጥያቄ በአእምሯቸው ሲመላለስ እንደነበር ነው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት።  

«ማለቴ የሱዳንን ጉዳይ መመልከትና መተንነት ከጀመርኩ ወዲህ እንዲህ ካለው ጥያቄ ጋር ስታገል ነው የቆየሁት፤ ከ1997 ወዲህ ለረዥም ጊዜ ማለት ነው። እዚያ የነበረው ሁኔታ በጣም የተበላሸ ነበር፤ ከጦርነት ጋር እና በተለይም በአዋሳኝ አካባቢዎች አሰቃቂ ጦርነቶች እንደውም የዘር ፍጅት ሊባሉ የሚችሉ ነበሩ። እናም ዓለም በመሠረቱ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠውም።»

ለዚህ ደግሞ አንድ ወጥ መልስ ሊኖር እንደማይችል ነው ያመለከቱት ተመራማሪዋ። አንደኛው ምክንያት የሁኔታው ውስብስበት እንዳለ በሌላ በኩሉ ደግሞ የዘረኝነት ጉዳይም እንዳለ ነው ለማሳየት የሞከሩት። እሳቸው እንደሚሉትም በተለይ አፍሪቃና መሰል አካባቢዎች የሚኖር ጦርነት ያለመሰልጠን ውጤት እና የተለመደ ተደርጎ የመውሰድ አዝማሚያም ይታያል።

በአንጻሩ የሃገራት የውስጥ ችግር አንዱ ሀገር ከሌላው ጋር ከሚያደርገው ፍጥጫ ያነሰ ቀልብ ሊስብ እንደሚችል በማመልከት የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ምንም ያህል ሚሊዮኖችን ለከፋ አደጋ ቢዳርግም ትኩረት እንዲያጣ ሳያደርገው እንዳልቀረም የሚናገሩ አሉ።

ዲከርት ለምሳሌነት ያነሱት እሳቸው በሱዳን ጉዳይ ምርምር መሥራት በጀመሩበት ወቅት የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ጦርነት ውስጥ ነበረች። ያኔ ዳርፉር የከፋ ረሀብ እያሰጋት ቢሆንም ለዚህ ችግር ትኩረት የሰጠ አካል ግን አልነበረም። በወቅቱም አንዲት ጀርመናዊት ጋዜጠኛ ጉዳዩን ለማነጻጸር መሞከሯን ያስታውሳሉ።

«የመከራከሪያ ነጥቧም በዚያን ወቅት የዩጎዝላቪያ ጉዳይ የበለጠ ትኩረት አግኝቶ ነበር፤ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጧ በማከላዊ አውሮጳ በመሆኑ የሚል ነው። ሰዎቹ እንደኛ ባለወርቅማ ፀጉር፤ ሰማያዊ ዓይን ያላቸው፤ ቤቶቻቸው፤ ሥነ-ሕንጻቸው ሁሉ ከእኛ ጋር ይመሳሰላል። ይህ ደግሞ አሁን ከዩክሬን ሁኔታ ጋር መነጻጸር ይችላል። ስለዚህ ቅርብ እና ሰዎቹም  ለዚህ በቀላሉ ይበልጥ ቅርብ እንደሆኑ ማሰብ ይቻላል። በአንጻሩ ከሱዳን እጅግ በጣም ጥቂት ሥዕል ነው የሚመጣው። በእርግጥ ያ ተቀይሯል፤ ሆኖም ጋዜጠኛዋ እነዚያ ከሱዳን የሚመጡትን ፎቶዎች ልክ ከማርስ እንደመጡ ዓይነት ነው የሚታዩት፤ ሰዎቹም የተለዩ ናቸው። እናም ሰዎች በቀላሉ ከራሳቸው ጋር ሊያዛምዷቸው አይችሉም።»

ሌላው የሱዳንን ጉዳይ አስቸጋሪ ያደረገው የዓለም አቀፍ ተዋናዮች ጣልቃ ገብነት ነው ባይናቸው ዲከርት። ሳውድ አረቢያ እና ግብፅ የሱዳንን ጦር ኃይል በመደገፍ ሲታወቁ፤ አረብ ኤሜሬትስ ደግሞ የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አጋር ናት። በዚህ በኩል ደግሞ ምዕራባውያን ሃገራት በአጋሮቻቸው አማካኝነት ተቀናቃኞቹን በየፊናቸው ጠቃሚ ተጓዳኝ አድርገው መቁጠራቸው ለመፍትሄው መራቅ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ሸዋዬ ለገሠ/ካትሪን ሺር