ሱዳን፦ የጦር ኃይል አዛዧ ላይ የተቃጣው የድሮን ጥቃት መዘዝ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 27 2016የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ላይ በዚህ ሳምንት የተቃጣው የድሮን ጥቃት ብርቱ መዘዝ አስከትሏል ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎችን ያፈናቀለው፤ በዐሥር ሺዎችን የገደለው የሱዳን የርስ በርስ ግጭትም ማብቂያ ያለው አይመስልም ። ከሰሞኑ ስዊትዘርላንድ ውስጥ ጦር ሠራዊቱን እና ባላንጣው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ለማደራደር የነበረው ሐሳብ በድሮኑ ጥቃት ሰበብ ለጊዜው የመከነ ይመስላል ። ጄኔራሉ እስከ መጨረሻው የደም ጠብታችን በጦርነቱ እንገፋበታለን ሲሉ ዝተዋል ።
የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን በዚሁ ሳምንት ወታደራዊ ጦር ሠፈር ውስጥ በነበረ የምረቃ ሥነስርዓት ላይ ከተሰነዘረባቸው የድሮን ጥቃት ለጥቂት ተርፈዋል ። ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የድሮን ጥቃት የተቃጣባቸው ከፖርት ሱዳን 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ገባይት ከተማ ውስጥ ነው ። ጄኔራሉ ምሥራቅ ሱዳን ውስጥ በሚገኘው ጦር ሠፈር 5 ሰዎችን ከገደለው የሰው አልባ ጢያራ (ድሮን) ጥቃት ለጥቂት የተረፉት ባለፈው ረቡዕ ነበር ። ይህ ጥቃት የተሰነዘረው የሱዳን ጦር ሠራዊት ከአማፂው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) አንጃ ጋ ስዊዘርላንድ ውስጥ በሰላም ድርድር ለመሳተፍ ፈቃደኝነቱን በገለጠ ማግስት ነው ። ድርድሩ ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ነበር ። ጊባይት ጦር ሠፈር ውስጥ ከድሮን ጥቃት ሙከራው ከሰዓታት በኋላ አብደል ፋታህ ኧል-ቡርሃን ለተመራዊቂ ወታደሮቻቸው ንግግር ባሰሙበት ወቅት ግን ከእንግዲህ ከማንም ጋ ለድርድር እንደማይቀመጡ ዐሳውቀዋል ።
«ሱዳናውያንን በየቦታው ሲያሸብሩ የከረሙትን አማፂያን ድራሻቸውን ማጥፋት አለብን ። ወታደሮቻችን ክብር ይገባችኋል ። በእየ ቦታው ላለው ሕዝባችንም፦ እንደማናፈገፍግ፤ እጅ እንደማንሰጥ፤ ማንም ይሁን ማን ከየትኛውም አካል ጋ እንደማንደራደር በእናንተ በኩል መልእክት ማስተላለፍ እንሻለን ። አንዳችም የሚያስፈራን ነገር የለም ። ሰው አልባ አውሮፕላኖችንም ይሁኑ ሌላ የሚያስፈራን ነገር የለም ። ከተጻፈልን ቀን ውጪ አንሞትም ። የማንም ሰው እጣ ፈንታ በተወሰነለት ቀን ይመጣል ። ለዚያም ነው አንገታችንን ቀና አድርገን የምንንቀሳቀሰው፤ በኩራት የምንዋጋውም ። እጅ አንሰጥም ።»
የሱዳን ከፍተኛ ጦር አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እሳቸው ታድመውበት በነበረው የጦር ሠራዊት የምረቃ ስነስርዓት ላይ ከተሰዘረው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት አንዳችም ጉዳት ሳይደርስባቸው መውጣታቸውን የጦር ሠራዊቱ ቃል አቀባዩ ረቡዕ ዕለት አረጋግጠዋል ። አምስት ሰዎችን የገደለው ጥቃት የተሰነዘረው በፈጥኖ ደራሽ ኃይል ቡድኑ ነው ተብሏል ። ቡድኑ ግን በጥቃቱ እጄ የለበትም ሲል አስተባብሏል ።
ሱዳን በሀገሪቱ ጦር ሠራዊት እና ከመደበኛው ጦር ውጪ በሚንቀሳቀሰው ብርቱው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) መካከል በሚደረግ የእርስ በርስ ጦርነት ከአንድ ዓመት በላይ ፍዳዋን ስትበላ ቆይታለች ። ቡድኑ በአንድ ወቅት በሱዳን መንግስት ቁጥጥር ስር የነበረ ቢሆንም፤ በጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ግን ተቃቅሮ ተለያይቷል ።
በሱዳኑ የርስ በርስ ግጭት ሳቢያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሱዳን ንጹሐን ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተገድለዋል ። ግድያ እና መፈናቀሉ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚያከትም አይመስልም ። በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በአማጺያኑ መካከል ከሰሞኑ ይደረጋል ተብሎ የታቀደው ድርድር ግን ለጊዜው የማይታሰብ መሆኑን ጄኔራሉ እዛው በምረቃው ሥነስርዓት ወቅት ይፋ አድርገዋል ።
«እነዚያ ሰዎች እስካሉ ድረስ ውጊያችን ይቀጥላል፣ ጦርነታችንም ይቀጥላል። ሱዳን ለሴራ፤ እጅግ ለብርቱ ሴራ በተጋለጠችበት ወቅት እንደመጣችሁ ልነግራችሁ እወዳለሁ ። እናም እኛ ከእናንተ ጋ ሆነን ይህን ሴራ እንዲያከትም የማድረግ አቅሙ አለን ። ይህንን ጠላት እንደመስሰዋለን ። ዛሬ ማታ፤ ነገ እና ከነገ በስትያ እንደመስሳቸዋለን ። ያን አድርገን ደግሞ እናጠፋቸዋለን ።»
ምንም እንኳን የሱዳን ተፋላሚዎች ለድርድር እንዲቀመጡ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪው ቢበረታም፤ ጄኔራሉ ግን ከምንም በላይ በቅድሚያ የሱዳንን ሕዝብ እና ጦር ሠራዊቱን ማክበር ያሻል ብለዋል ። የመንግስት እና ጦር ሠራዊቱን ጥረት እና መስዋዕትነትም ዕውቅና መስጠት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
«ድርድር እንዳለ ሁላችንም ሰምተናል። ድርድሩን እንቀበላለን ብለናል፤ ግን እነማን ናቸው ድርድሩን የሚጠሩት? የሚጠሩትስ እነማንን ነው? ሠራዊቱ ብቻ አይደለምውጊያ ላይ ያለው ። ዜጎችም እየተዋደቁ ነው ። የሰላም ንቅናቄው እየተዋጋ ነው ። መላው የሱዳን ሕዝብ እየተዋጋ ነው ። ለዚያም ነው ድርድር ካለ እነዚህን ሰዎች እና አስተያየታቸውን ማጤን የሚያሻው ። ድርድር ካለ ለሱዳን መንግስት ዕውቅና ይሰጣል ተብሎ ይታሰባል ። እናም ይህ መንግሥት ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል ። በዚያ መሠረት መደራደር እንችላለን ።»
በድርድሩ ግንባር ቀደም የሆኑ ሃገራት ማለትም ሣዑዲ ዓረቢያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ከሱዳን መንግሥት ጋ ቀርበው እንዲወያዩ ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጠዋል ። በዚህም አለ በዚያ ግን በጦርነቱ ድል እስክንጎናጸፍ ድረስ በውጊያው እንገፋበታለን ሲሉ ዝተዋል ። የርስ በርስ ጦርነት እና ተከታታይ ድርቅ የመታት ሱዳን የመከራ ድግስ መሪር ጽዋዋ ግን ተጠምቆ ያለቀም አይመስልም ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ