1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን ለተቃውሞ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈፃሚን ጠራች

ቅዳሜ፣ ግንቦት 22 2012

የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ቅዳሜ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚን ጠርቶ ከአል-ቀዳሪፍ ከተማ አቅራቢያ ተፈጸመ በተባለ ጥቃት ላይ ተቃውሞውን ገለጸ። ሱዳን ለተቃውሞ ጉዳይ ፈፃሚውን ለመጥራት ያበቃት ባለፈው ማክሰኞ ታጣቂዎች ፈፅመውታል የተባለ ጥቃት ነው። በጥቃቱ ወታደሮች እና ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል

https://p.dw.com/p/3d2n8
Karte Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre EN

የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚን ጠርቶ ባለፈው ማክሰኞ ከአል-ቀዳሪፍ ከተማ አቅራቢያ ተፈጸመ በተባለ ጥቃት ላይ ተቃውሞውን ገለጸ። ከኢትዮጵያ ድንበር የተሻገሩ ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉ ታጣቂዎች ፈፅመውታል በተባለው ጥቃት የሱዳን ጦር አባላት እና ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫን ጠቅሶ ሬውተርስ ዘግቧል። የሱዳን ዜና ወኪል እንደዘገበው ጥቃቱ የተፈጸመው ከአል-ቀዳሪፍ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ ነው። 

የሱዳን ጦር ቃል-አቀባይ ኢትዮጵያ ለታጣቂዎቹ ድጋፍ አድርጋለች ሲሉ ወንጅለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን በይፋ ማብራሪያም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም።  

የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሕፃናትን ጨምሮ የአገሪቱ ጦር አባላት እና ሱዳናውያን ዜጎች ተገድለዋል ቢልም ዝርዝር ማብራሪያ ሳይሰጥ ቀርቷል። በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ሽፈራው ጃርሶ ባለፈው ሳምንት የሥራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳለው ጥቃቱ የተፈጸመው ኻርቱም የኢትዮጵያ እና የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚሳተፉበት እና በድንበር ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ስብሰባ ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ሳለች ነው።

የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ምኒስትር ደመቀ መኮንን እና የሱዳን  የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኦማር በሽር ማኒስ የተሳተፉበት የዚሁ ስብሰባ የመጀመሪያ ዙር ከግንቦት 8 እስከ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ ተካሒዶ ነበር።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት በአዲስ አበባ "በሁለቱ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች በየጊዜው የሚያጋጥሙ የጸጥታና የደህንነት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ እና የሁለቱን አገሮች የድንበር ጉዳይ በተመለከተ" ውይይት መደረጉን ገልጿል።

"ውይይቱ በሁለቱ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፤ ሕገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣ አፈናና የመሳሰሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን በጋራ ለመከላከልና መፍትሄ ለመሻት የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል" ብሏል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን የድንበር አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ግጭቶች የተለመዱ ናቸው። ሁለቱ አገሮች በይገባኛል የሚወዛገቡባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ በርካታ ውይይቶች እና ስብሰባዎች ቢያደርጉም ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት አልቻሉም። አሁን በድንበር አካባቢ የተፈጠረው ኹኔታ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል እና አስተዳደር ጉዳይ በሚያደርጉት ድርድር ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር አስግቷል።

እሸቴ በቀለ