1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰሜን ሸዋ ዞን ቀዎትና ሞላሌ ወረዳዎች በድሮን በተከፈተ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 6 2016

አንድ የአከባቢው ነዋሪ እንደሚሉት እሁዱ የቀዎት ወረዳው እኩለ ቀን የድሮን ጥቃት የተነጣጠረው በርግቢ በሚባል አከባቢ ት/ቤት ላይ ነው፡፡ቦታው ለኤፍራታ እና ግድም ወረዳ እጅግ ቅርብ ቦታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ትምህርት ቤት ላይ ተጥሎ ነው መምህራን ያለቁት፡፡ እለቱ እሁድ ቢሆንም እነሱ ገጠር ስለሆነ ቦታው በዚያው ነው የሚኖሩት” ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4fqNq
የኢትዮጵያ ጦር አማፂያን ሸምቀዉበታል የሚለዉን አካባቢ በተደጋጋሚ በድሮን ያጠቃል
ከተለያዩ ሰዉ አዉልባ የጦር አዉሮፕላኖች (ድሮን) አንዱ ዓይነትምስል Iranian Army Office/Zuma/picture alliance

ሰሜን ሸዋ ዞን ቀዎትና ሞላሌ ወረዳዎች በድሮን በተከፈተ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ

ባለፈው እሁድ ግንቦት 04 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በቀዎት ወረዳ እና ሞላሌ ወረዳዎች ተፈጸመ በተባለ የሰውአልባ  አዉሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደልና መቁሰላቸዉ ተነገረ።የሁለቱ አከባቢዎች ነዋሪዎች እንደሚሉት በታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ከአየር በተከፈተ ጥቃት 14 ሰዎች ተገድለዋል፡፡መንግስት ሥለጥቃቱ እስካሁን ያለው የለም፡፡

የቀዎት ወረዳ ተሬ ቀበሌው ጥቃት

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አንድ የአከባቢው ነዋሪ እንደሚሉት የባለፈው እሁዱ የቀዎት ወረዳው እኩለ ቀን የድሮን ጥቃት የተነጣጠረው በርግቢ በሚባል አከባቢ ት/ቤት ላይ ነው፡፡ “ቦታው ለኤፍራታ እና ግድም ወረዳ እጅግ ቅርብ ቦታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ትምህርት ቤት ላይ ተጥሎ ነው መምህራን ያለቁት፡፡ እለቱ እሁድ ቢሆንም እነሱ ገጠር ስለሆነ ቦታው በዚያው ነው የሚኖሩት” ብለዋል፡፡

ሌላው የአከባቢው ነዋሪ በአስተያየታቸው፤ “በድሮኑ ፋኖን ነው የማድነው ብልም ምንገስት ጭራሽ እነሱን እያገኘ ሳይሆን ንጹሃን ነው እየሞተ ያለው፡፡ ሰባት መምህራን ናቸው በዚህ ቀዎት ወረዳ ተሬ በሚባል ቀበሌ ባሉ ትምህርት ቤት ላይ እሁ በተጣለው የድሮን ጥቃት ያለቁት፡፡ መምህራኖቹ በዚያው የሚኖሩና የሚስተምሩ ናቸው” ብለዋል፡፡

የሞላሌ ወረዳ አዘዞ ቀበሌው ጥቃት

ከዚህ በተጨማሪ በዚሁ ተመሳሳይ ዞን በሞላሌ ወረዳ መዘዞ ተብላ በምትጠራው ከተማ አጠገብ በተጣለ ሌላው የድሮን ጥቃት የሰላማዊ ሰዎች ህይወትም ጭምር ያለፈበት አደጋ መድረሱን ከሳላ ድንጋይ አከባቢ አስተያየታቸውን የሰጡን የአከባቢው ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ “በዚያው በመዘዞ እሁድ መስለኛል ከአንድ ሶስት አራት ቀናት በፊት በዚያው መዘዞ ከተማ አጠገብ የሳር ጎጆ ላይ በተጣለው ድሮን ጥቃት ሶስት የፋኖ አባላት እና በመጠጥ ሽያጭ ላይ የተሰማራች አንድ ሴት ጨምሮ አራት ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች አልቀዋል” ብለዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የመንግስት ኃይላት ከአማራና ከኦሮሞ አማፂያን ጋር በተደጋጋሚ ይዋጋሉ
በሰሜን ሸዋ ዞን የመንግስት ኃይላትና አማፂያን ከሚያደርጉባቸዉ አካባቢዎች አንዱምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ምላሽ

ስለጥቃቱ መፈጸም በመንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡ ዶቼ ቬለ ለሰሜን ሸዋ ዞን ኮሚዩኒኬሽን እንዲሁም ለክልሉ እና ለፌዴራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናትም ደውሎ ተጨማሪ መረጃውን ለማግኘት ያደረገው ጥረትም ለዛሬ አልሰመረም፡፡ እንዲሁም መረጃዉን ከሶስተኛ ወገን ለማረጋገጥ ጥረት አድርገን መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን መረጃው እንዳላቸው አረጋግጠውልን የምርመራ ሂደቱ ግን ገና በጅምር ላይ ነው ብለዋል፡፡ ባለስልጣኑ “ክስተቱ ገና የቅርብ ቀን ስለሆነ በመረጃ አሰባሰብ ሂደት ላይ ነን፡፡ በቂ መረጃ ስኖረንና ምጃውም ትክክል መሆኑን ብሎም ማን ላይ ያነጣጠረ ነበር የምለውን ከለየን በኋላ ይፋ እናደርጋለን” ሲሉም ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት መጨረሻ ከሃምሌ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል የተስፋፋውን ግጭት ተከትሎ ተደጋግሞ የተከሰተውን የአየር ላይ (የድሮን) ጥቃት በርካታ የመብት ድርጅቶች ሲያወግዙ መንግስት ግን ከዚህ በፊት በሰጠው አስተያየት የጥቃቱ ኢላማ በክልሉ በህገወጥ መንገድ ታጥቆ በመንቀሳቀስ ጉዳት ያደርሳሉ ያሏቸው ላይ ብቻ እንደሚነጣጥር ደጋግሞ ማስረዳቱ ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ