1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰሎሞን ይትባረክ የፓሪሱ «ሬስቶራንት ምኒልክ» ባለቤት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 17 2016

አቶ ሰሎሞን የምግብ ቤታቸው መታወቅና የደንበኞች ቁጥር መጨመር ቢያስደስታቸውም ሥራ እንደጀመሩ ግን እጅግ የሚያሳስባቸው ነገር ነበር ።በተለይ ፈረንሳውያንም ሆኑ ሌሎች የውጭ ዜጎች ምናልባት ምግቡ ባይስማማቸው ችግር ያስከትልብኛል የሚል ስጋት ነበራቸው። ሆኖም እስካሁን ግን መጥፎ ነገር አልሰሙም ።

https://p.dw.com/p/4e9Ng
Menelik Restaurant in Paris | Eigentümer Solomon Yitbarek
ምስል Hirut Melesse/DW

አቶ ሰሎሞን ይትባረክ የፓሪሱ «ሬስቶራንት ምኒልክ» ባለቤት

አቶ ሰሎሞን ይትባረክ ይባላሉ።ከሀገራቸው ከኢትዮጵያ ከወጡ ግማሽ ምዕተ ዓመት ተቆጥሯል። 17 ዓመት እስራኤል፤ ፈረንሳይ ደግሞ 33 ዓመት ኖረዋል።አሁን በሚኖሩባት በፈረንሳይ ታዋቂ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት አላቸው። ፈረንሳይ ከመምጣታቸው በፊት እስራኤል ኖረዋል። በፈረንሳይ በምግብ ቤታቸው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንን በመርዳትም ይታወቃሉ። 
ከኢትዮጵያ ሳይወጡ ከአባታቸው ጋር ይነግዱ ነበር። በእስራኤል ደግሞ በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ ሰርተዋል።


እስራኤል የተዋወቁዋቸውን ፈረንሳዊት ካገቡ በኋላ የዛሬ 33 ዓመት ከቤተሰባቸው ጋር ወደ ፈረንሳይሄዱ። ከጥቂት ዓመታት በኋላም በፓሪስ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት ከፈቱ። «ሬስቶራንት ምኒልክ» የተባለው ምግብ ቤታቸው ሥራ ከጀመረ ዘንድሮ 27 ዓመት ሆነው። አንዱ ከአንዱ እየሰማ ፣የሚያውቋቸው ሰዎች ምግብ ቤቱን እያስተዋውቁ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የደንበኞቻቸው ቁጥር ከፍ ማለት ጀመረ። በተለይ ግን በምግብ ቤታቸው አካባቢ ትኖር የነበረች አንዲት ፈረንሳዊት ዘፋኝ ለርሳቸውም ምግብ ቤትም ሆነ በፓሪስ ለሚገኙ ሌሎች የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶች መታወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ።

 አጼ ኃይለ ስላሴ ከእውቁ የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሻርል ደጎል ጋር የተነሱት ፎቶግራፍ በፓሪሱ «ሬስቶራንት ምኒልክ»
አጼ ኃይለ ስላሴ ከእውቁ የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሻርል ደጎል ጋር የተነሱት ፎቶግራፍ በፓሪሱ «ሬስቶራንት ምኒልክ»ምስል Hirut Melesse/DW


ምግብ ቤቱ እየታወቀ ሲሄድ እርሳቸውን ጨምሮ አራት የነበረው የምግብ ቤቱ ሠራተኞች ቁጥርም ወደ ሰባት ስምንት አደግሞ ነበር ። አቶ ሰሎሞን የምግብ ቤታቸው መታወቅና የደንበኞች ቁጥር መጨመር ቢያስደስታቸውም ሥራ እንደጀመሩ ግን እጅግ የሚያሳስባቸው ነገር ነበር ።በተለይ ፈረንሳውያንም ሆኑ ሌሎች የውጭ ዜጎች ምናልባት ምግቡ ባይስማማቸው ችግር ያስከትልብኛል የሚል ስጋት ነበራቸው። ሆኖም እስካሁን ግን መጥፎ ነገር አልሰሙም ።


እርሳቸው ምግብ ቤቱን ሲያስተዳድሩ ባለቤታቸው ደግሞ በሂሳብ ሥራ ያግዙዋቸዋል። እስከ ኮሮና ድረስ ሥራው በጥሩ ሁኔታ ነበር የቀጠለው። በኮሮና ምክንያት የምግብ ቤቶች መዘጋት ከዚያም በፈረንሳይ አብዛኛው ሠራተኛ ከቤት መሥራት መጀመሩ በገበያቸው ላይ ተጽእኖ አሳደረ። ሥራው ፈታኝ ቢሆንም አቶ ሰሎሞን ግን ተስፋ ባለመቁረጥ በጽናት በመቀጠል አሁን ለሚገኙበት ደረጃ መድረስ መቻላቸውን ይናገራሉ። የአቶ ሰሎሞን እድሜ  68 ቢሆንም አሁንም ጠንካራ ሠራተኛ መሆናቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ይመሰክሩላቸዋል። ከዚህ ሌላ ለሀገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ባለ አቅማቸው በመርዳትም ይታወቃሉ። ይህን ከሚመሰክሩት አንዷ ከዛሬ 28 ዓመት አንስቶ የምታውቃቸው የፓሪስ ነዋሪ ሀና ውብሸት ናት።ያኔ አዲስ የነበረችው ሀና የመኖሪያ ፈቃድዋ እስኪስተካከል በሚል ለጊዜው በምግብ ቤታቸው መሥራት ጀምራ 7 ዓመት እዚያው ቆይታለች።

ፓሪስ የሚኖሩት አቶ ሰፈፈ ገብሬ ከአቶ ሰሎሞን ጋር የሚተዋወቁት የራሳቸውን ምግብ ቤት ሳይከፍቱ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ነበር። እርሳቸው እንደሚሉት አቶ ሰሎሞን ምግብ ቤታቸውን ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን በምግብ ሥራው የሚሳተፉና ከምንም በላይ የተመጋቢዎቻቸውን ስሜት ማወቅ የሚፈልጉ ናቸው ።     
ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት አቶ ሰሎሞን የአራት የልጅ ልጆችም አያት ናቸው። ልጆቻቸው እንዲያርፉ ቢፈልጉም እርሳቸው ግን ከሥራው መራቅ አልፈቀዱም።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ