1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰላምን እንዴት ይመጣን?፤ የመከላከያ ሚኒስትሩ ቃለ ምልልስ፤ የፓትሪያርኩ አስተያየት

ዓርብ፣ የካቲት 29 2016

ለህዝባችንን ማዘን፤ ህብረተሰቡን መርዳት፤ እርስ በእርስ መተዛዘን፤ የተሻለውና አማራጭ የሌለው የአማራና የትግራይ ህዝብ ብቻ ተነጋግረው ችግሮቻቸውን መፍታት ነው፤ ለእምነት አባቶች ክብር የሌላቸው ባለስልጣናት ናቸው የበዙት፤ ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት በእርስ በርስ ጦርነት ማንም አሸናፊ አይሆንም። እናም የሰላም መፍትሔው አካል እራሳቸው ጠቅላዩ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4dJcw
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማምስል AMANUEL SILESHI AFP via Getty Images

ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሰላምን እንዴት ይመጣ ይሆን? 

በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የተለያዩ አካላት ጥሪ ሲያቀርቡ ይሰማል። ሆኖም በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሰላም እጦቱ ተባብሶ ቀጥሏል። ሰላም እንዲሰፍን ከሚጠይቁት አንዱ የሆነው መንግሥት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ ኃይላት ጋር ውጊያ ገጥሟል። በሂደቱም ሲቪሉ ማኅበረሰብ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እና የሚፈጸመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አሳሳቢ መሆኑን በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ተቋማት በተደጋጋሚ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጠረው የደህንነት ስጋት የኅብረተሰቡን ከቦታ ቦታ የመንገቀሳቀስ ፍላጎት ከመገደብ አልፎ የረድኤት ድርጅቶችን ስጋት ላይ በመጣሉ ሦስት ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች እንዲወጡ ማስገደዱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የሚታየውን የጸጥታ ስጋት ለማስወገድ ምን መደረግ ይኖርበት ይሆን?   በሚለዉ ጥያቄ ስር የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ሰፋ ያሉ መልሶችን ተለዋዉጠዋል። 

አብዲ ጃፋር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ ሰላም ለማምጣት ቀላሉ ነገር መሪ የሚለውን መስማት ብቻ ነው። መሪ የሚለዉን መስማት፤ ለሌላው አካል መጠቀሚያ ላለመሆን ነቅተን መስራት፤ ባንዳነት ከውስጣችን ማውጣት፤ ለህዝባችንን ማዘን፤ ህብረተሰቡን መርዳት፤ እርስ በእርስ መተዛዘን፤ ከዛ ፈጣሪ እራሱ ሰላሙን ያወርድልናል ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

ሸምስ መሀመድ እንዲህ ይላሉ በአስተያየታቸዉ። ይህ ሁሉ ምስቅልቅል የመጣው፤ በመንግስት እምቢተኝነት ነው።  ቀደም ባለው መግለጫቸው የአሁኑን ጫጫታ እናውቀዋለን፤ አዲስ አይደለም በሚል እዚህ አደረሱት። የአሁኑም መግለጫቸው ሁሉ፤ ከአንድ የሀገር መሪ የማይጠበቅ፤ አታሸንፉንም የሚል መፈክር ነው። ጠቅላዩ ግን ትልቁን  የሀገሪቷን ተቋም መከላከያን ያለአግባብ ዋጋ እያስከፈሉት መሆኑን ያውቁ ይሆን ? ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት በእርስ በርስ ጦርነት ማንም አሸናፊ አይሆንም። እናም ይላሉ እናም የሰላም መፍትሔው አካል እራሳቸው ጠቅላዩ ናቸው። አሁንም አልረፈደም ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ኤፍራታ ጌዛይ በበኩላቸዉ፤ ሰላም በቀላሉ መምጣት የሚችለው በመንግሥት በኩል ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ፍትሃዊ ህግ ሲኖር ብቻ ነው። ልክ እናንተ እንደምትኖሩበት ጀርመን ማለት ነው። ለምሳሌ ጀርመን ውስጥ ችግር ሳይኖር ቀሮቶ አይደለም እኮ።  ለዛውም ጥርሱን ያገጠጠ የዘረኝነት ችግር ነዉ ያለዉ። ግን ይላሉ፤ ግን ህጋቸው አድሏዊ ስላልሆነ እብዱም ጤነኛውም ሁሉም ህግን ፈርቶ ሳይወድ በግዱ ህጉን አክብሮ ፀጥ ለጥ ብሎ ይኖራል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን በአራት ነጥብ ቋጭተዋል። ፋንታሁን አወቀ፤ ለሰላም ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ይላሉ። ሰላም በአንድ ወገን ብቻ አይመጣም ሁሉም ወገኖች ለሰላም ሆደ ሰፊ መሆን አለባቸው። በተለይ ደግሞ ለህዝብ ነዉ ብለዉ የሚታገሉ ወገኖች በጠብ መንጃ አሸንፋለሁ በለው ከማሰብ ወጥተዉ፤ በሰላም ማሸነፍም አለ። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ዛሬም ነገም ሰላም አስፈላጊ ነዉ፤ ሲሉ በአራት ነጥብ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ቃለ ምልልስ

የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር
የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለአንድ መንግስታዊ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በትግርኛ በሰጡት ቃለ ምልልስ «አወዛጋቢ ቦታዎች»ባሏቸው እና ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች የሚገኙ  ከፌደራል መንግስት ውጭ የሆኑ ታጣቂዎችን ለማስወጣት እየሰራ ነው፤ በጦርነቱ የተፈናቀሉትንም  ወደቀዬአቸው ለመመለስ የፌደራሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነዉ ብለዋል። ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ እስካሁን በተያዘለት ግዜ ባይሳካም፥ ጥረቶች መቀጠላቸውን አንስተዋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ፤ በኤርትራ ሰራዊት የተያዙ ቀሪ አካባቢዎችን ለመለየት እና መፍትሔ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑም ገልፀዋል።

አበበ ዘለቀ የተባሉ ፤ በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ አሉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ፤ በአፍ ይጠፉ፤ ለዘላቂ ችግር የማይነጋ እየመሠለን የምንሰጠው የማደናገሪያ መፍትሄ ተብዬ ሀገሪቷን እንደ አሻሮ እያመሣት ነው። የአማራና የትግራይ ህዝብ በቅንነት ቢወያዩ ሊፈቱት የሚችሉትን ችግር እየቆሰቆሱ፤ ዳር ሆኖ መግለጫ መስጠት እሳት መሞቅና እሳት መንካት ያላቸውን ትኩሳት ያለመረዳት ያህል ነው። በአማራና ትግራይ ህዝብ መካከል ከእንግዲህ ምንም አይነት የሚባክን ጥይትም ሆነ የሠው ህይወት አይኖርም። እያጋጩ ማስታረቅ ዘመን ያለፈበት ፖለቲካ ለማንም አይበጅም። የሠው ልጅ ከፈጣሪ የተሠጠውን በህይወት የመኖር መብት ማንም ሊነጥቀው አይገባም። የምንባለው ኢትዮጵያ ለኛ ሳትበቃን ቀርታ ሣይሆን እኛ ለሀገራችን የሚበቃ አስተሳሰብ በማጣታችን ነው። ፈጣሪ ሀገራችንና ህዝባችን ይጠበቅ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ዳዊት ትግራይ የተባሉ በበኩላቸዉ፤ ምንም የሚያወዛግብ ስፍራ የለም። አማራጩ አንድና አንድነው፤ የአገራችን ሰላምና መረጋጋት ካስፈለገ፤ ያለምንም ማቅማማት፤ መሠረታዊ የትግራይ ግዝአቶች በአግባቡ፤ መመለስና በወረራ የገቡትን ማስወጣት፤ የግድነው። በመከላኪያ ጀርባ ታዝሎ የገባው ሻዕቢያም፤ በአስቸኳይ፤ ከግዝአታችን መውጣት አለበት። ከአንድ ሚልዮን በላይ ነዋሪ አፈናቅለህ ምን አይነት ሰላም ይመጣል? ተፈናቃዩስ ሰላም ይሰጣል ወይ ? በየመጠለያው ላይ ያለዉ የባርነት ሕይወት እየመራ ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል። ዛዉ ቤራዉ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ የተሻለው እና አማራጭ የሌለው የአማራና የትግራይ ህዝብ ብቻ ተነጋግረው ችግሮቻቸውን መፍታት ነው ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤታ ክርስትያን የፓትሪያርክ አስተያየት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤታ ክርስትያን ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤታ ክርስትያን ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤታ ክርስትያን ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ «ያለንበት ዘመን ለእግዚአብሔር ክብርን የነሣ፤ ከፍቅርና ከአንድነት የራቀ፣ ራስ ወዳድነትና በቃኝ አለማለት የወረረው፤ በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ የተዋጠ ትውልድ የታየበት ዘመን ነው» ብለዋል ። አክለውም «የዘመናችን ትውልድ ከተግባር ይልቅ አስመሳይ ሆኖ መታየትን፣ ከቅድስና ይልቅ ነውረ ኃጢአትን፤ ከትሕትና ይልቅ ትዕቢትን የተለማመደ፣ ለሃይማኖትም ሆነ ለማኅበረ - ሰብ ጤናማ ህላዌ ያልተመቸ ትውልድ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው» በማለት አዝማሚያው አደገኛ እንደሆነ ገልፀዋል ።

ሱልጣን ጀማል እንደዚህ ለሰማያዊ ህይወታቸው ያደሩ አባቶችን ሳይ በኢትዮዽያ ተስፋ አረጋለሁ። ይላሉ። ሰዎች ምን ይላሉ የሚል የፌስቡክ መለያ ያላቸዉ መልስ አዎ እውነት ነው ይላሉ አዎ እዉነት ነዉ። እያየነው ነው። ለእምነት አባቶች ክብር የሌላቸው ባለስልጣናት ናቸው የበዙት፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። ኮሎናኒ ያቢሊ የተባሉ አስተያየት ሰጭ፤ አዲሱ ትውልድ ቴክኖሎጂን መከተሉ በዚህ ደረጃ ሊያስወቅሰው አይችልም። በግለሰብ ደረጃ ስህተት ሊሠራና ሊነገርም ይችላል፤ እንደ ትውልድ በጅምላ መጨፍለቅ ግን ጥቅም አያስገኝም፤ ሲሉ ትችት አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።  በማኅባራዊ መገናኛ ትስስር ገጻችን አስተያየቶቻችሁን አስቀምጡልን እያልን ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመቻ ማዕቀፉn በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ