1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ርዕደ መሬት እና ሳይንሳዊ እውነታዎቹ

ረቡዕ፣ መስከረም 29 2017

የአሜሪካ የጅኦሎጅካል ሰርቬይ መረጃ እንደሚያሳየው ርዕደ መሬት የሚፈጠረው የምድር ንጣፎች ወይም «ቴክቶኒክ ፕሌትስ» በሚሰኙት ጠርዝ ላይ ነው።እነዚህ የምድር ቅርፊቶች የተደራረቡ እና ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን እርስ በእርስ የሚጋጩበት ጊዜ አለ።

https://p.dw.com/p/4NW22
Türkei Erdbeben, Zerstörung in Kahramanmaras
ምስል Nir Elias/REUTERS

እንስስት ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት እንግዳ ባህሪ ያሳያሉ


በቅርቡ በቱርክ እና በሶርያ በተከሰተው ርዕደ መሬት  ከ36 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉ እየተነገረ ነው።  ለመሆኑ ይህንን መሰሉን አውዳሚ ርዕደ መሬት መከላከል፣ መተንበይ እና ጉዳቱን መቀነስ ይቻላልን?እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎቸን ለመመለስ የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በርዕደ መሬት እና ሳይንሳዊ እውነታዎቹ ላይ በማተኮር የተሰናዳ ነው። 
የአሜሪካ የጅኦሎጅካል ሰርቬይ መረጃ እንደሚያሳየው ርዕደ መሬት የሚፈጠረው ከምድር  በታች በሚገኙ አለታማ  ቁሶች ግጭት ነው።ይህ ግጭት የሚፈጠረው የምድር ንጣፎች ወይም «ቴክቶኒክ ፕሌትስ» በሚሰኙት ጠርዝ ላይ ነው። እነዚህ የምድር ቅርፊቶች  የተደራረቡ እና ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን እርስ በእርስ የሚተሻሹበት እና የሚጋጩበት ጊዜ አለ።ይህ ድንተኛ ግጭት የሚፈጥረው ንዝረት እና ሞገድም ምድርን በመሰንጠቅ  ርዕደ መሬት እንደፈጠር ያደርጋል። 
በዚህ ሁኔታ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ/ም በቱርክ እና በሶርያ የተከሰተው አስከፊ ርዕደ መሬት በርካቶች ጉዳት ሲደርስባቸው ከ36 ሺህ በላይ ሰዎችንም ህይወት ነጥቋል። በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 የተለካው ይህ ክስተት ከተሞቹንም ወደ ፍርስራሽነት ቀይሯል

Erdbeben in der Türkei - Kahramanmaras
ምስል Bulent Kilic/AFP

።ይህንን መሰሉን ተፈጥሯዊ ክስተት መከላከል የሚያስችል ሳይንሳዊ መላ ይኖር እንደሁ በባህርዳር ዩንቨርሲቲ መምህር እና የስነ-ምድር  ተመራማሪ የሆኑትን ዶክተር ምንያህል ተፈሪን ጠይቀናቸው አና እንዲህ አሉን። 
«ርዕደ መሬትን መከላከል አይቻልም።መከላከል ሳይሆን የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ህብረተሰቡን ከአካባቢው ማንሳት እና ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ነው እንጅ ፤የተፈጥሮ ክስተት ስለሆነ መግታት አንችልም።»በማለት ገልፀዋል።
ነገር ግን መቼ እንደሚከሰት ትክክለኛ ጊዜ መናገር ባይቻልም ርዕደ መሬት ከመድረሱ በፊት የመሬትን የላይኛውን የአካል ክፍል እንቅስቃሴ በመመልከት ቅድመ ትንበያ ማድረግ እንደሚቻል ተመራማሪው ያስረዳሉ።
«መተንበይ ይቻላል።ለምሳሌ የጃፓኑ የ2011 ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት ተተንብዮ ነበረ። በ30 ዓመት ውስጥ ይከሰታል ብለው ሳይንቲስቶች የፊዚክስ ባለሙያዎች ተንብየው ነበር።ያንን ትንበያ ባደረጉ በዓመቱ ነው የተከሰተው።ምክንያቱም የሚተነበየው የመሬትን የላይኛውን አካል እንቅስቃሴ በማየት ነው።» 
ርዕደ መሬት ከተፈጥሯዊ በተጨማሪ በሰው ሰራሽ መንገድ በግንባታ፣ በማዕድን ቁፋሮ እና በአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ ሊከሰት ይችላል። በዓለም ላይ  አነስተኛ ርዕደ መሬት በየትኛውም ቦታ የሚከሰት ሲሆን፤ ፍሎሪዳ እና ሰሜን ዳኮታ አነስተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ያለባቸው የአሜሪካ ግዛቶች ናቸው።አንታርክቲካ ከየትኛውም አህጉር ትንሹ ርዕደ መሬት የሚከሰትበት አህጉር ነው። አብዛኛው አውዳሚ ርዕደ መሬት የሚከሰተው ደግሞ በፓስፊክ አካባቢ ነው።ይህ የሆነበት ምክንያትም የመሬት ንጣፍ /ፕሌቶች/ በአብዛኛው የሚንቀሳቀሱት በዚሁ አካባቢ በመሆኑ ነው።በቅርቡ ርዕደ መሬት የተከሰተባቸው ቱርክ እና ሶርያም በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ናቸው።ባለሙያወቹ እንደሚሉትም የሰሞኑ ክስተት  የአረቢያን የመሬት ንጣፍ  /ፕሌት/ ወደ ሰሜን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከምስራቅ አናቶሊያ የመሬት ንጣፍ /ፕሌት/ ጋር በመጋጨቱ የተፈጠረ  ነው። በኢትዮጵያም የሰምጥ ሸለቆ አካባቢ ለዚህ ክስተት የተጋለጠ መሆኑን ተመራማሪው ይገልፃሉ።
«ክረስት» የሚባለው የመሬት የላይኛው ክፍል «ማንትል»በሚባለው የታችኛው የመሬት ክፍል ላይ እንደሚንቀሳቀስ የሚገለፁት ባለሙያው።

Innerer Aufbau der Erde
ምስል Wikipedia

በዚህ መሰሉ እንቅስቃሴ  በሚፈጠር ግጭት እና ንዝረትም በተለዬ ሁኔታ በርዕደ መሬት የሚጠቁ ሌሎች ሀገራት መኖራቸውንም ያስረዳሉ።
ይህንን የመሬት ውስጣዊ እንቅስቃሴም ከሰዎች ይልቅ እንስሳት ቀድመው እንደሚረዱት ባለሙያው ገልጸዋል።እንደ ውሻ ፣አሳ፣ አዕዋፍ ፣ተሳቢ እንስሳት እና ነፍሳትን የመሳሰሉ እንስሳት አውዳሚ  ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት እንግዳ ባህሪ እንደሚያሳዩ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ይህንንም እንደ ጃፓን እና አሜሪካ ያሉ ሀገራት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እንደሚጠቀሙበት ተመራማሪው አስረድተዋል። 
በሌላ በኩል ዋናው ርዕደ መሬት ከመከሰቱ  በፊት እና በኋላ   ቅድመ እና ድህረ ርዕደ መሬቶች ይከሰታሉ። የመጀመሪያው ቅድመ ርዕደ መሬት ከዋናው ጋር በተመሳሳይ ቦታ የሚከሰት ቢሆንም አነስተኛ ስለሆነ ፤ይህንን ክስተት ርዕደ መሬት መሆኑን ሊቃውንት እንኳ መናገር አይችሉም።ሌላው ድህረ ርዕደ መሬት ወይም / After shocks/ ሲሆን፤ ዋናው ርዕደ መሬት /Mainshocks/ በኋላ የሚከሰት እና በሬክተር  ስኬል ሲለካ ከዋናው ያነሰ ነው።ነገር ግን ባለሙያው እንደሚሉት የበለጠ ጉዳት የሚያደርስ ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ድህረ ርዕደ መሬት ለሳምንታት፣ለወራት ወይም ለዓመታት ሊቀጥል ይችላል።በሰሞኑ በቱርክ-ሶሪያ አዋሳኝ አካባቢ ከተከሰተው ርዕደ መሬት በኋላም ከ 100 ጊዜ በላይ ተከስቷል ።በተለምዶ የድህረ ርዕደ መሬት መጠን  ከመጀመሪያው ክስተት በአንድ ዲግሪ ያነሰ ሲሆን፤ የሰሞኑ  ግን መጀመሪያው  7.8  ከተመዘገበ በኋላ የተከሰተው 7.5 ማግኒቲዩድ  ያለው በመሆኑ ከተለመደው  ጠንከር ያለ ነው።
 

Erdbeben in der Türkei - Kahramanmaras
ምስል Bulent Kilic/AFP

የብሪቲታኒያ  የጂኦሎጂካል ሰርቬይ  ተመራማሪ ሮጀር ሙሶን ለDW እንደገለፁት አንዳንድ ጊዜ ጊዜ ከዋናው  የሚበልጥ የድህረ ርዕደ መሬትም ሊያጋጥም ይችላል። ስለዚህ እንደ  ባለሙያ፣ ምድር በምትሰጠን አዳዲስ ነገር ለመደነቅ  ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን አለብን። በማለት ሳይንስ ያልደረሰባቸው እውነታዎች መኖራቸውን ገልፀዋል። ሙሶን አክለውም ክስተቱ በምስራቅ አናቶሊያን የመሬት ንጣፍ /ፕሌት / እንደተከሰተ በተሻለ ሊገለጽ ይችላል ብለዋል። 
ከዚህ በተጨማሪም ዋናው ርዕደ መሬት አነስተኛ፣  መካከለኛ እና ከፍተኛ በመባል በሶስት ሊከፈል ይችላል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከፍተኛ የሚባለው ርዕደ መሬት በጎርጎሪያኑ 1960 ዓ/ም በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ችሊ የተከሰተው ሲሆን 9 ነጥብ 5 ሬክተር ስኬል ነበር።ሌላው በሬክተር ስኬል 9 የተመዘገበው በ2011 ዓ/ም በጃፓን የተከሰተው ርዕደ መሬት ሲሆን፤  ይህም መነሻው የባህር ዳርቻ በመሆኑ ተከታታይ ሱናሚዎችን በማስከተል በአካባቢው በሚገኝ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።በቅርቡ በቱርክ እና ሶርያ የተከሰተው ደግሞ 7 ነጥብ 8 ቢሆንም የከፋ ጉዳት የታየበት ነው።ለዚህም የህንፃዎቹ ጥንካሬ እና ችግሩ የተከሰተው ንጋት ላይ ሰዎች በመኝታ ላይ እንዳሉ መሆኑ ለጉዳቱ በምክንያትነት እየተጠቀሰ ነው።
ከዚህ አንፃር ዶክተር ምንያህል ጉዳቱ ከመከሰቱ በፊትም ሆነ፤ በኋላ መደረግ አለበት የሚሏቸው የጥንቃቄ ርምጃዎች አሉ።

Syrien UN-Konvoi mit Hilfsgütern aus Türkei
ምስል BAKR ALKASEM/AFP

«እንደዚህ አይነት አእካባቢዎቸ ላይ የከተሞች መስፋፋት እንዳይኖር ጃኦሎጅስቶች ትልቅ አእሰተዋጻኦ አእላቸው።ከተማ ምስረታ ወይም «ሴትልመንት»  ሊሆን ይችላል። ስለዚህ «ሳይቲኒክ አእክቲቭ»  የሆነበት ቦታ ላይ አማራጭ ካልጠፋ ለምሳሌ አንደ ጃፓን ሌላ የሚህይዱበት ኮንተኔት ቢኖር ደስ ይላቸዋል።ስለሌለ ግን እየኖሩ ነው።እየኖሩ ግን ርዕደ መሬትን  በቴክኖሎጅ እየተቋቋሙት ነው።ግን እንደኛ አይነት ሀገር በዙ ቦታ ባለበት አዳዲስ ከተማዎች መስፋፋት « ሴተልመንት»  የህንጻ ኮንስትራክሽን ያሉበት ቦታ ከሆነ ጃኦሎጅስቶች ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል። ቢያንስ ከተሰራም ጠንካራ ህንጻ ቢሆንና በዙ «ሴትልመንት» ባይኖር ይመከራል። ስለዚህ ቅድመ ትንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።ዞሮ ዞሮ ግን በቦታው እየኖሩ ከሆነ ግን»  ካሉ በኋላ፤ ከባለሙያ መረጃ ማግኜት እና ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት ቦታውን መልቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር ምንያህል ተፈሪ ተናግረዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ