ሪታ ፓንክኸርስት የኢትዮጵያ ባለውለታ | ባህል | DW | 07.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ሪታ ፓንክኸርስት የኢትዮጵያ ባለውለታ

አዲስ አበባ ላይ ትዳር የመሰረቱት የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪዎች በትዳር ከ60 ዓመታት በላይ ዘልቀዋል። የአንድ ወንድና የአንድ ሴት ልጅም ወላጆች ነበሩ። አራት የልጅ ልጆችንም አይተዋል። ወ/ሮ ሪታ ፓንክኸርስት በቤተ-መፅሕፍት ባለሙያነታቸው በብሔራዊ ቤተ-መፅሕፍት፣ አገልግለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:01

በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ሕያዉ ሆነዉ ሲታወሱ ይኖራሉ

ሀገራችን ሀገሯ፣ ህዝባችን ህዝቧ፣ ኑሯችን ኑሮዋ ሆኖ ስታገለግለን እድሜዋን ጨርሳ ከእኛው ዘንድ አረፈች። ሪታ ፓንክኸርስት የኢትዮጵያ ባለውለታ! ደህና ሁኚ፤ ይላል ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ በፌስቡክ ድረገፁ ያስቀመጠዉ ጽሑፍ። ከስድሳ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ኖረዉ ትዳር ይዘዉ ወልደዉ ከብደዉ የልጅ ልጅ አይተዉ ብሎም የኢትዮጵያን ታሪክ ባህል ላይ የተለያዩ አስተዋፆዎችን ያበረከቱት ወ/ሮ ሪታ ፓንክኸርስት ባለፈዉ ሃሙስ በ 92 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ባለቤታቸዉ አጋፋዉ የኢትዮጵያ የታሪክ ተመራማሪ የፕሮፊሰር ሪቻርድ ፓንክኸርስት ከሁለት ዓመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉ ይታወሳል። በዚህ ዝግጅታችን የሪታ ፓንክኸርስትን የሕይወት ታሪክና በኢትዮጵያ ሳሉ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ እንቃኛለን።

በጎርጎረሳዉያኑ 1927 ዓ.ም በሩሜንያ የተወለዱት ወ/ሮ ሪታ ፓንክኸርስት በ11 ዓመታቸዉ ከወላጆቻቸዉ ጋር ወደ እንጊሊዝ ተሰደዱ። ታዳጊዋ ሪታ በእንጊሊዝ ሃገር ካምብሪጅ ከተማ በሚገኝ የልጃገረዶች ት/ቤት የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ተከታትለዋል። የከፍተኛ ትምህርታቸዉን በኦክስፎድ ዩንቨርስቲ ፈረንሳይኛና ሩስያንኛን በሚያካትተዉ የዘመናዊ ቋንቋች ጥናት በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል። ሪታ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን እንዳጠናቀቁ በመጀመርያ የተቀጠሩት ቻተም ሃዉስ በሚገኘዉ ፕሬስ ቤተ-መፅሕፍት ዉስጥ ነዉ። ከዝያም ሪታ የዝያን ግዜ የፍቅር ጓደኛቸዉ ሪቻርድን እና የሪቻርድን እናት ሲልቪያ ፓንክኸርስትን ተከትለዉ ወደ ኢትዮጵያ በጎርጎረሳዉያኑ 1956 ዓ.ም ይመጣሉ።

የሪታ ፓንክኸርስት ልጅ አሉላ ፓንክኸርስት ስለእናቱ ማንነት እንዲነግረን ቀጠሮ ልንይዝ የደወልነት በለቅሶ ላይ ሳለ ነበር። እንድያም ሆኖ ለነገ ቀጠረንና ግንቦት 28 የእናቱ ግባዕተ መሬት ከተፈፀመ ከአንድ ቀን በኋላ በስልክ ስለናቱ አጫወተን። እናቱ ሪታ በብሪታንያ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን አጠናቀዉ በመፀሐፍ ትርጉም በቋንቋ አስተማሪነት እንዲሁም በቤተ- መፅሐፍ ዉስጥ ሲሰሩ ሳለ ሪቻርድን ይተዋወቃሉ። ከዝያም ነዉ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት።

«ሪታ እናቴ፤ አባቴን እንደ አጋጣሚ ለንደን ከተማ ላይ ተዋዉቃዉ ነበር።  አባቴ ከእናቴጋር ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ መወሰኑን ነግሮ አብራ እንድትመጣ ጋበዛት፤ እስዋም ወድያዉኑ ከሱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ ወሰነች። እናት እና አባትዋ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ መወሰንዋን ሲሰሙ በጣም ሰግተዉ ነበር። የአባቴ እናት የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያስተዋዉቅ መጽሔት ነበራት። የአባቴ እናት ጃንሆይ ኢትዮጵያን እንድትጎበኝ ሲጋብዝዋት፤ መጀመርያ ለብቻዋ ኢትዮጵያን ጎበኘች ፤ ከዝያም ለሁለተኛ ጊዜ ከአባቴ ጋር ወደኢትዮጵያ ሄዱ፤ ከጥቄት ወራቶች በኋላ እናቴም ወደ ኢትዮጵያ መጣች። ይህ የሆነዉ በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ 1957 ዓ.ም ነዉ። በዚሁ ዓመት እናትና አባቴ እዚሁ አዲስ አበባ ጋብቻቸዉን ፈፀሙ። ሚዜዎቻቸዉ  ሜትር አርቴስት አፈወርቅ ተክሌ እና መንግስቱ ለማ ነበሩ። 

      

አዲስ አበባ ላይ ትዳር የመሰረቱት የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪዎች በትዳር ከ60 ዓመታት በላይ ዘልቀዋል። የአንድ ወንድና የአንድ ሴት ልጅም ወላጆች ነበሩ። የአራት የልጅ ልጆችንም አይተዋል። ወ/ሮ ሪታ ፓንክኸርስት በቤተ-መፅሕፍት ባለሙያነታቸው በብሔራዊ ቤተ-መፅሕፍት፣ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬኔዲ ቤተ-መፅሕፍትና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቤተ-መፅሕፍት አገልግለዋል። በረጅም ዓመታት የስራ ዘመናቸው ወ/ሮ ሪታ የኢትዮጵያን ባሕል፣ የኢትዮጵያውያን ሴቶች ታሪክን እንዲሁም በኢትዮጵያ የቤተ-መፅሕፍት ታሪክና ዕድገትን መርምረዋል፣ዘክረዋል።

«በኢትዮጵያ ኖሮ እንደጀመሩ በደርግ ዘመነ መንግሥት በቀይ ሽብር ጊዜ ወላጆቼ ወደ ለንደን ተሰደዉ ሳለ እናቴ ሪታ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ታሪክ ጉባኤ እንዲዘጋጅ መጀመርያ ሃሳብ አቅርባ ነበር። ወደ ለንደን የተሰደዱት በወቅቱ በሃገሪቱ በነበረዉ አስከፊ ሁኔታ ልጆቻችንን ለማሳደግ ከባድነ ነበር የሚል ስጋት አድሮባቸዉ ስለነበረ ነዉ። በርግጥ አባቴ ኢትዮጵያን መልቀቅ አልፈለገም ነበር። በለንደን ሲኖሩ ሪታ ፓንክኸርስት የተለያዩ ጉባዔዎችን ስታከፈል የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ የንባብ ባህልን ማዳበር እንደሚያስፈልግ በተለያዩ የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ላይ ጥናቶች እና ጽሑፎችን አቅርባለች። እግረ መንገድዋን አባቴ ሪቻርድ በሚያዘጋጀዉ «ኢትዮጵያን ኦብዘርቬሽን» በተባለዉ መጽሔት ላይ በጽሑፍ ታግዘዉ ነበር። በቤተ-መጻሕፍት በተለይ የአጼ-ቴድሮስ በብራና ላይ የተፃፉ ደብዳቤዎችን እና ጽሑፎችን በተመለከተ የተለያዩ ጽሑፎችን በማቅረብ አስተዋዉቃለች። በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሴቶች ታሪክን ለማጥናት ሞክራ ነበር። 

በተለይ አሁንም  አርዓያ የሆኑ የኢትዮጵያ ሴቶችን እንደ ስንዱ ገብሩ የመሳሰሉ ታዋቂ ኢትዮጵያዉያን ሴቶችን ታሪክ በመፃፍ ይበልጥ ለማስተዋወቅ እና ታሪካቸዉንም ለማሳየት ጥረት አድርጋለች።   

አቶ አሉላ በቀይ ሽብር ጊዜ ወላጆቼ እኛን ይዘዉ ወደ ብሪታንያ ተሰደዉ ነበር ብለኸኛል እስቴ ስለ ስደት ታሪክ ንገረን?

« በወቅቱ የደርግ መንግሥት የጃንሆይን መንግስት ገርስሶ ስልጣን በተቆጣጠረበት ወቅት አባቴ በቀድሞ ጊዜ ኃይለሥላሴ ዩንቨርስቲ በሚባለዉ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ዉስጥ በሚገኘዉ  የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ሆኖ ያገለግል ነበር፤ እናቴ ደግሞ በዚሁ ዩንቨርስቲ ኬኔዲ ላይብረሪ የሚባለዉ ቤተ-መጽሐፍት ዋና ተጠሪ ነበረች። ኑሮዋቸዉ ሙሉ በሙሉ እዚሁ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ዉስጥ ነበር። ደርግ ወደ ስልጣን በመጣ ጊዜ መጀመርያ ሁኔታዉ ተቀይሮ ብሩህ ተስፋ ይመስል ነበር ። ግን ትንሽም ሳይቆይ ሁኔታዎች አስከፊና አሳዛኝ አቅጣጫን ሲይዝ ፤ በተለይ የደርግ መንግሥት ስድሳ ባለስልጣናትን በረሸነበት ወቅት፤ በተለይ አማን አብዶ ሲገደል አባቴ ወደ ለንደን ለመመለስ ወሰነ። አማን አብዶ የአባቴ ተማሪ ነበር፤ በጣም ጎበዝ ተማሪ በጣም የሚያደንቀዉ ተማሪ ነበር። የሚኖረዉም እዚሁ እኛ በምንኖርበት አካባቢ ነበር። አካባቢዉ ላይ ታንኮች ገብተዉ አማን አብዶ በተገደለ ጊዜ እና ሁኔታዉ አሳሳቢ እየሆነ ሄደ። እኔ እና እህቴ ደግሞ ገና ታዳጊ ሕጻናት ነበርን፤ ሁኔታዉ በጣም አሳሳቢ መሆኑን የተረዳዉ አባቴ እና ልጆቹን ይዞ ወደ እንግሊዝ ሃገር እንሂድ የሚል ዉሳኔ ላይ ደረሰ። አባቴ እንግሊዝ ለንደን እንደገባ ስራ አልነበረዉም፤ ከዝያም ለንደን በሚገኝ ዩንቨርስቲ የአፍሪቃ ጥናት ተቋም ዉስጥ ለማስተማር የአንድ ዓመት ኮንትራት አገኘ። እናቴም በቤተ-መፅሐፍት ጉዳይ ሞያ በለንደን በአንድ ዩንቨርስቲ ዉስጥ ስራን ጀመረች። እንድያም ሆኖ ወላጆቼ ለንደን ይኑሩ እንጂ ሃሳባቸዉ ወደ ኢትዮጵያ ነበር።

ሁለቱም በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥናታቸዉን ቀጠሉ። በዝያዉ በለንደን ሲኖሩ የመጀመርያዉ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ የዓለም አቀፍ ጉባኤ ለንደን ላይ እንዲጀመር አብረዉ ነበር ስራን የሰሩት። ከዝያም አባቴ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ እድልን ሲያገኝ ለመመለስ ፈለገ። የወላጆቼ ከኢትዮጵያ ወደ ብሪታንያ አካሄዳቸዉና አመላለሳቸዉ ይሄንን ይመስላል።

በብሪታንያ በስደት ስንት ዓመት አመት ኖሩ?

«በለንደን ወደ አስር ዓመት ግድም ቆይተዋል። ከዝያም አባቴ ተመልሶ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ማገልገል ጀመረ። እናቴም እንዲሁ የተለያዩ የጥናት ጽሑፎችን እንዲሁም የተማሪዎች የመመረቅያ ጽሑፎችን አርትዓይ በማድረግ ሥራን መስራት እገዛን ጀመረች። ከዚህ ሌላ በጣም የምትወዳቸዉ ነገር ነበርዋት። ለምሳሌ ለኢትዮጵያዉያን ወጣት ተማሪዎች በየዉጭ ትምህርት እድል እንዲያገኙ በአንድ ዓለም አቀፍ ተቋም ዉስጥ በመስራት ትልቅ እገዛን አድርጋለች። በመንታ እናቶች የርዳታ ድርጅት የቦርድ አባል በመሆን አገልግላለች። በተለይ የአትክልቶች የዕጽዋት ልዩ ፍቅር ነበራት። በተለይ ግቢዋ ዉስጥ የምትተክላቸዉን የተለያዩ ተክሎች አበቦች በጣም ትወድ ነበር። በዚህም ወጣት አታክልተኞችን ለማበረታታት በሚደረገዉ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ስተዋጾን አበርክታለች። በሃገሪቱ በሚካሄድ የአትክልት ትርኢት ዉድድር ላይ በዳኝነት ወንበር ላይ ትቀመጥ ነበር።»      

ኢሌኒ መኩርያ የድሮ ጋዜጠኛ የአሁን ጡረተኛ ስትል በዶይቼ ቬሌ ለቃለ ምልልስ የቀረበችዉ የሪታ ፓንክኸርስት የቅርብ ወዳጅ አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ኢሌኒ መኩርያ ከሪታ ጋር በተለይ በኢትዮጵያ የታሪክ ጥናት ተቋም በጋራ አገልግለዋል።

የፓንክኸርስት ቤተሰብ ወደ እንግሊዝ አገር ተመለሶ እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር ከ1976 ዓ.ም እስከ 1987 በኖረባቸው 10 -11 ዓመታት ውስጥ ወ/ሮ ሪታ ለንደን በሚገኘው የፖሊቴክኒክ ት/ቤት የቤተ-መፅሕፍትት አገልግሎት ኃላፊ በመሆን አግልግለዋል። ወ/ሮ ሪታ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በለንደን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ምስረታን እውን ካደረጉት ሰዎችመካከል አንዷ ነበሩ። ወ/ሮ ሪታ ፓንክኸርስት ባለፉት ስድስት አምስት ዓመታት ከባለቤታቸዉ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ታሪካቸዉን መፃፍ ጀምረዉ ነበር። ኢትዮጵያን ወዳጅዋ ሲቭሊያ ፓንክኸርስት ለኢትዮጵያ ሰርተዉ እዉቀት ፍቅርን አስተላልፈዉ አልፈዋል። የፓንክኸርስት ቤተሰቦች ለኢትዮጵያዉያ ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ትዉልድ ሲማርበት እንዲሁም በስራቸዉ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ሕያዉ ሆነዉ ሲታወሱ ይኖራሉ። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ! 

 

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic