1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሦስት የአውሮጳ አገሮች ለፍልስጤም እዉቅና ሊሰጡ መሆኑ

ሐሙስ፣ ግንቦት 15 2016

የአየርላንድ፣ ስፔንና ኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ትናንት ከዋና ከተሞቻቸው ደብሊን፣ ማድሬድና ኦስሎ በተመሳሳይ ግዜ በሰጧቸው መግለጫዎች ከፊታችን ማክሰኞ ሜይ 28 እለት 2024 ዓ.ም ጀምሮ ለፍልስጤም ነጻ አገርነት በይፋ ዕውቅና የሚሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል። ፍልስጤሞች እርምጃውን ትክክለኛና ወቅታዊ በማለት አወድሰውታል።

https://p.dw.com/p/4gCyv
የእስራኤል የቅርብ ጊዜ ጥቃት ከጀመረ በኋላ በአይርላንድ ዋና ከተማ ዱብሊን ብዙ የፍልስጤም ደጋፊ ሰልፎች ተካሂደዋል
የእስራኤል የቅርብ ጊዜ ጥቃት ከጀመረ በኋላ በአይርላንድ ዋና ከተማ ዱብሊን ብዙ የፍልስጤም ደጋፊ ሰልፎች ተካሂደዋል ምስል Artur Widak/NurPhoto/picture alliance

ሦስት የአውሮጳ አገሮች ለፍልስጤም እዉቅና ሊሰጡ መሆኑ

የአየርላንድ፣ ስፔንና ኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ትናንት ከዋና ከተሞቻቸው ደብሊን፣ ማድሬድና ኦስሎ በተመሳሳይ ግዜ በሰጧቸው መግለጫዎች ከፊታችን ማክሰኞ ሜይ 28 እለት 2024 ዓ.ም ጀምሮ ለፍልስጤም ነጻ አገርነት በይፋ ዕውቅና የሚሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል። የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሚስተር  ሲሞን ኽሪስ ከደብሊን በሰጡት መግለጫ የፍልስጤም ጥያቄ አገራቸው እ እ እ በ1919 ዓ.ም ለዓለማቀፉ ህብረተሰብ አቅርባው ከነበረው የነጻነት ዕውቅና ጥያቄ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን አውስተዋል፤ “ ዛሬ ለፍልስጤም ነጻነትና አገርነት እውቅና የምንሰጠው አየርላንድ ከብዙ ዓመታት በፊት በተመሳሳይ አቅርባው በነበረው የዕውቅና ጥያቄ ቋንቋና አረዳድ መሰረት ነው” በማለት ለፍልስጤም የተሰጠውን ውሳኔ ታሪካዊነትና ትክክለኛነት ገልጸዋል።

የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ሚስተር ፐድሮ ሳንቼዝ በተመሳሳይ ከማድሬድ በሰጡት መግለጫ አገራቸው በዚህ ውሳኔ የፍልስጤምን አገርነት ተቀብለው ዕውቅና ከሰጡት ከአንድ መቶ አርባ በላይ አገሮች የምትቀላቀል መሆኑን አብስረዋል። ሚስተር ሳንቼዝ አክለውም፤ ውሳኔው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፍልስጤም የድርጅቱ አባል እንድትሆን በክፍተኛ ድምጽ ያሳለፈውን ውስኔ ተከትሎ የተውሰነ እንደሆነና ሌሎች የምዕራብ አገሮችም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስዱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትርም አገራቸው  የፍልስጤምን ጥያቄ ደግፋ እንደቆየችና በአሁኑ ወቅት ግን አገራዊ ዕውቅና መሰጠት ማስፈልጉን ጠቅሰዋል።

የፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ለምን አሁን

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ሚስተር ኤስፔን ባርዝ ኤይዲ የውሳኔውን ወቅታዊነትና ለምን በዚህ ወቅት እንዳስፈልገ ሲያባራሩ፡ “አንደኛው  የፍልጤም ህዝብ ነጻ የፍልስጤም አገር ሊኖረው የሚገባ በመሆኑ ነው። ሁለተኛው፤ በርካታዎቹ የምራብ አገራት ለፍልስጤም ዕውቅና ከመስጠት የዘገዩት የሰላም ድርድሩ እስከሚቋጭ የነበር ቢሆንም፤  በአሁኑ ወቅት ግን የሁለት አገሮች የሰላም ስምምነት እንደውም አደጋ ላይ በመሆኑ ውሳኔው እሱንም ለመታደግ መሆኑን ገልጸዋል።

የስፔን ጠ/ሚ ሳንቼዝ እና አይሪሽ ታኦይዝሽ ሲሞን ሃሪስ ነፃ የፍልስጤም መንግስትን ይደግፋሉ
የስፔን ጠ/ሚ ሳንቼዝ እና አይሪሽ ታኦይዝሽ ሲሞን ሃሪስ ነፃ የፍልስጤም መንግስትን ይደግፋሉምስል Paul Faith/PA Wire/empics/picture alliance

ለውሳኔው ከፍልስጤም፤ እስራኤልና ሌሎች የተሰጠ ምላሽ

ፍልስጤሞች እርምጃውን ትክክለኛና ወቅታዊ  በማለት አወድሰውታል። የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ቃል አቀባይ ሚስተር ናቢል አቡ፤ በሶስቱ አገሮች የተሰጠው እውቅና ለፍልስጤምና ለአካባቢው ሰላም ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ነው የገለጹት። “ በሶስት የአውሮጳ አገሮች የተስጠው ዕውቅና ለስላምና ለሁለት አገሮች የመፍትሄ ሀስብ በጣም ጠቃሚ ነው” በማለት ለሰላም ያለው ብቸኛ አማራጭ ይኸው ብቻ እንደሆነና  ለሌቹ የአውሮጳ አገሮችም የነዚህን አገሮች ፈለግ እንደሚከተሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል

እስራኤል ግን ውሳኔውን በእስራኤል ህልውና ላይ የተቃጣና  ለአሸባሪዎች የተስጠ ሽልማትነው በማለት አውግዛ፤ በሶስቱ አገሮች የሚገኙ አምባሳደሮቿን ጠርታለች። አሜርካና ከአውሮጳም ፈረንሳይና ጀርመንን ጨምሮ ሌሎች፤ አጣዳፊውና ወቅታዊው ጉዳይ የፍልስጤም መንግስት ዕውቅና ጉዳይ አለመሆኑን በመጥቀስ ውሳኔው ይልቁንም ችግሩን የበለጠ እንዳያወሳስብ ያላቸውን ስጋት ሲገልጹ ተሰምተዋል

በእስራኤል ላይ የተቃጡት የዲፕሎማሲ ጫናዎችና አንደምታቸው   

እስራኤል ባለፈው መስከረም ወር ምራባውያን አሸባሪ የሚሉት ሃማስ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተክትሎ፤ በጋዛ በከፍተችው ጦርነትና ባደረሰችው ጉዳት ደቡብ አፍካ በዓለማቀፉ ፍርድቤት ከመሰረትችባት የዘር ማጥፋት ወንጅል ክስ በተጨማሪ መሪዎቿ ከሀማስ መሪዋች ጋር በጦር ወንጀል ክስ የእስር ማዘዣ እንዲቆረጥባቸው፤ ያለም የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድቤት አቃቢ ህግ ጠይቆባቸዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ  ለበርካታ አመታት እውቅና ከመስጠት ተቆጥበው የነበሩት የምራብ አገሮች የፍልስጤም አገርነትን መቀበላቸው በእስራኤል ላይ ትልቅ የዲፕሎምሲ ኪሳራ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ሁኗል።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከሃማስ ጋር መዋጋት ከጀመረች ወደ ስምንት ወራት ሊሆነዉ ነዉ
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከሃማስ ጋር መዋጋት ከጀመረች ወደ ስምንት ወራት ሊሆነዉ ነዉምስል Amir Cohen/REUTERS

የነጻ አገርነት እውቅናው ፋይዳ

 ሆኖም ግን እውቅናው ብቻውን የእስራኤል-ፍልስጤም ችግርን ሊፈታ እንደማይችል ነው የፖለቲካ ተንታኖች የሚናገሩት። ቀድሞ በመንግስታቱ ድርጅት የብርታኒያ ዲፕሎማት የነበሩት ሚስተር ካርኔ ሮስ የፍልስጤምን አገርነት ሁሉም አገሮች እውቅና ቢሰጡት እንኳ ብቻውን ፍልስጤሞችን የነጻ አገር ባለቤት እንደማያደርግ ነው የሚናገሩት፡ “ የሁለት አገሮች የመፍትሄ ሀሳብን እውን ማድረጊያ ብቸኛው መንገድ በእስራእል ላይ ተጨባጭ ጫና መፍጠር ነው። በሁሉም አገሮች ለፍልስጤም አገርነት እውቅና መስጠት፤ለፍልስጠም ጋዛን ወይንም የምራብ ዳራቻ ፍልስጤምን፤ ወይንም የምስራቅ እየሩሳሌምን አያስገኝላቸውም” በማለት ከዕውቅናው የፖለቲክ ድጋፍ ውጭ ለዘላቂ መፍሄ ተጨባጭና የተግባር እርምጃ የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል።

 በእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ ልዩነታቸው እየሰፋ የሄዱት የአውሮጳ ህብረት አገሮች ሚኒስትሮች  በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሚደርጉት ስብሰባም ዋና አጀንዳቸው ይኸው ጉዳይ እንደሚሆን ተገልጿል።

ገበይው ንጉሴ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ