1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምያንማር ውስጥ ለችግር የተጋለጡት ኢትዮጵያውያን

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 5 2017

ወይዘሮ አበበች ሽመል ወንድ ልጃቸው የተሻለ ክፍያ ያለው ሥራ ለማግኘት በሚል ወደ ደቡብ ምስራቅ የኤስያዋ ሀገር ሚያንማር ሲጓዝ ያልገመተው የወንጀል ተግባር ውስጥ ይገባል የሚል ግምት አልነበራቸውም። የአካሄዱ ሁኔታም ያንን ለመገመት የሚመች አልነበረም።

https://p.dw.com/p/4lpLv
የኢትዮጵያ መንግሥት ለስቃይና መከራ የተጋለጡ ሥራ ፈላጊ ኢትዮጵያዉያንን ወደ ሐገራቸዉ እንዲመልስ ቤተሰቦቻቸዉ ጠይቀዋል
ሥራ ፍለጋ ወደ ምያንማር ከተሰደዱ ኢትዮጵያዉያን አንዱ በተፈፀመበት ድብደባ ሰዉነቱ ክፉኛ ተጎድቷል።የሥራ ፈላጊዎቹ ቤተሰቦች አንዳሉት በርካታ ወጣቶች በአጭበርባሪ ደላሎች ተታልለዉ ወደ ምያንማር ተሰደዋል።ምስል Privat

ምያንማር ውስጥ ለችግር የተጋለጡት ኢትዮጵያውያን

ከሚያንማር እና ታይላንድ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋ የደላሎች መረብ ኢትዮጵያውያን ሚያንማር ውስጥ ለችግር እንዲጋለጡ እየዳረጋቸው መሆኑን የዚህ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች ለዶቼ ቬለ ተናገሩ።

ሃያ ያህል ሰዎች ከአንድ ወር በፊት ጉዳዩን በተመለከተ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስገቡት ማመልከቻ ምን ላይ እንደደረሰ ለመጠየቅ ዛሬ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄደው እንደነበር የገለፁ አንድ ልጃቸው የዚህ ችግር ሰለባ የሆነባቸው እናት ጉዳዩ እየታየ መሆኑ እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል።

ከችግሩ አሳሳቢነት መነሻ ጉዳይ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲታይ እንደሚፈልጉም እነዚህ ቤተሰቦች ጠይቀዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ወደ ጠቅላይ ምኒስትር ጽ/ቤት ለአቤቱታ እንደሚያመሩም ያነጋገርናቸው እናት ገልፀዋል።

ጉዳዩ እንደሚያውቀው ያገለፀው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጃፓን እና ሕንድ በሚገኙት ኤምባሲዎች እንዲሁም ታይላንድ ውስጥ ባለው ቆንስላ ጽ/ቤት በኩል ጉዳዩን ለመረዳትና መፍትሔ ለመስጠት "ክትትል እና ጥረት እየተደረገ" መሆኑን አስታውቋል።// 

ደላሎች ሕጋዊ አስመስለው ነው በፕሌን የሚወስዷቸው - ቤተሰብ

ወይዘሮ አበበች ሽመል ወንድ ልጃቸው የተሻለ ክፍያ ያለው ሥራ ለማግኘት በሚል ወደ ደቡብ ምስራቅ የኤስያዋ ሀገር ሚያንማር ሲጓዝ ያልገመተው የወንጀል ተግባር ውስጥ ይገባል የሚል ግምት አልነበራቸውም። የአካሄዱ ሁኔታም ያንን ለመገመት የሚመች አልነበረም።

"በደላላ ነው እየተጭበረበሩ በፕሌን ቲኬት ተቆርጦላቸው ነው ሕጋዊ አስመስለው ነው ታይላንድ ካደረሱ በኋላ ወደ ማረፊያ ሆቴላችሁ ትሄዳላችሁ እየተባሉ፤ መኪና ውስጥ ያስገቧቸዋል ከዚያ በኋላ ልጆቹ ታገቱ ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ምንም መንቀሳቀሻ የላቸውም"።

የዚህን ጉዞ ሂደት ከሚያንማርና ታይላንድ እስከ አዲስ አበባ የግንኙነት መረብ የዘረጉ ደላሎች በወኪሎቻቸው በኩል እንደሚያከናውኑት የመረጃ ምንጮቻችን ገልፀዋል። ይህንን ሐቅ ካወቁ ማግስት ጀምሮ ጉዳዩን ለመንግሥት ለማስረዳት ያልገቡበት ቦታ ጥቂት መሆኑን የሚናገሩት እኒሁ እናት "መመላልስ ከጀመርኩ 11 ወር ሆኖኛል" ይላሉ። 

ሥራ ፍለጋ ወደ ምያንማርና ታይላድ የተጓዙ ኢትዮጵያዉያን ለከፋ ችግር መጋለጣቸዉን ቤተሰቦቻቸዉ ገልጠዋል
የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ጃፓን፣ ሕንድና ታይላንድ ባሉት ሚሲዮኖቹ በኩል ወደ ምያንማርና ታይላድ የተጓዙ ኢትዮጵያዉያንን ጉዳይ እንደሚከታተል አስታዉቋል።ምስል Solomon Muchie/DW

ሴቶችን ሆቴል እና መስተንግዶ፣ ወንዶችን የኦንላይን ንግድ ትሠራላችሁ የሚለው ማማለያ

ልጃቸው ምን ተነግሮት፣ ምን ያህል ከፍሎ ወደ ሚያንማር እንደወጣም ነግረውናል። መስከረም 7 ቀን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስገቡት ማመልከቻ የት ደረሰ የሚለውን ለማጣራት ዛሬ 20 ያህል ሰዎች እዚያው እንደነበሩም ነግረውናል።
   
"ሴቶችን ሆቴል እና መስተንግዶ ነው የምትሠሩት ይሏቸዋል። ወንዶችን ደግሞ ኦንላይን የንግድ ሥራ ነው የምትሠሩት እያሉ ነው የሚወስዷቸው። ቲኬቱንም፣ የወባ ክትባቱንም፣ አሻራውንም፣ ሁሉን ነገር በአንድ ሳምንት ውስጥ ተሯሩጠው ለራሳቸው ይጨርሳሉ። የተወሰነ ብር ያስከፍላሉ፣ ቲኬት ይቆርጡላቸዋል፣ ኑ ሂዱ ይሏቸዋል። ከዚያም በኋላ ቤተሰብ ሕጋዊ ይመስለው እና ይሸኛቸዋል ማለት ነው"። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ጉዳዩን ለመረዳትና መፍትሔ ለመስጠት "ክትትል እና ጥረት እየተደረገ" መሆኑን በሰሞኑ መግለጫቸው ተናግረዋል።

"በእኛ በኩል ሚያንማር ላይ ሚሲዮን የለንም። የጃፖን እና በታይላንድ ወይም ደግሞ በሕንድ ሚሲዮኖቻችን በኩል ነው ክትትል የሚደረግበት። በተቻለ መጠን ችግሩን ለመረዳት እና ዜጎችን መርዳት የሚቻልበትን ነገር ኤምባሲዎቹ በተቻላቸው አቅም ሁሉ ክትትል እና ጥረት እያደረጉ ነው ያለው"።

አቶ ነብያት ጌታቸዉ የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት ወደ ምያንማርና ታይላንድ የተጓዙ ኢትዮጵያዉያንን ጉዳይ መስሪያ ቤታቸዉ እንደሚከታተል ገልጠዋል
አቶ ነብያት ጌታቸዉ የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት ወደ ምያንማርና ታይላንድ የተጓዙ ኢትዮጵያዉያንን ጉዳይ መስሪያ ቤታቸዉ እንደሚከታተል ገልጠዋልምስል DW/G. Tedla

ጉዳይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ይታይልን - ወላጅ

በዚህ ጉዳይ ላይ ሌሎች ሰዎችም እየደወሉ ችግሩን ነግረውናል። ከውጭ ጉዳይ ለተለያዩ የፌዴራል የፀጥታ ተቋማት እና ለኢሚግሬሽን ደብዳቤ መፃፉን የገለፁት ወይዘሮ አበበች ትናንትም ዛሬም ወደዚያው ስፍራ የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ስለመስማታቸው ገልፀዋል። የሀገሪቱ ከፍተኛው የአስፈፃሚ አካል ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።

"ይሄን ጉዳይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲታይልን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ የራሱን ውሳኔ ሀሳብ እንዲሰጥበት ነው የምንፈልገው"።

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ወደ ጠቅላይ ምኒስትር ጽ/ቤት ጉዳዩን ይዘው እንደሚያመሩ እኒሁ እናት ተናግረዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ