1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"አለቅን በሁለት ቢላ"

እሑድ፣ ጥቅምት 3 2017

ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በሚያደርጉት ግጭት ክፉኛ ዋጋ እየከፈለ ያለው ሰላማዊ ዜጋው ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ትደግፋለህ በሚል ያሳደዳል፡፡ ህብረተሰቡ ያለው ስጋት ሲሰፋ እንጂ ስቀንስ አይስተዋልም፡፡

https://p.dw.com/p/4lidm
Infografik GRAPHIC Karte Amuru Woreda, Äthiopien
ምስል DW

"የሁለቱም ወገን ጥቃት መሮናል"

በኦሮሚያ ወደ ስድስት ዓመታት ለሚሆን ለተራዘመ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ግጭት መልኩን ቀያይሮ ለክልሉ ሰላማዊ ዜጎች አበሳ ሲሆን ቆይቷል፡፡ ግጭቱ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲካሄድበት ከነበረው አከባቢዎች አንዱ በሆነው ምዕራብ ኦሮሚያ የወለጋ ዞኖች አሁንም ድረስ የግጭቱ ዳፋ ንጹሃን ዘጎችን መለብለቡን አላበቃም፡፡

ከምዕራብ ወለጋ ዞን ባምቦ ጋምቤል ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን የአከባቢው ነዋሪ ለዚህ አንዱ ማሳያ ናቸው፡፡ “መስከረም 29 ቀን 6፡00 አከባቢ እኩለ ቀን አምስት ሰላማዊ ሰዎች ልጆቻችሁ በትጥቅ መንግስትን ይወጋሉ በሚል ተይዘው ታስረዋል፡፡ በዚሁ እለት አንድ የ8 ዓመት ታዳጊም ደንግጦ እየሸሸ ባለበት ነው ተተኩሶበት የተገደለው፡፡ በርግጥ በዚህ አከባቢ አሁንም ድረስ መንግስትን የሚወጉ የኦ.ነ.ሰ ታጣቂዎችም በስፋት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ፊትለፊትከመንግስት ኃይሎች ጋር ሲዋጉ ግን የምንመለከተው አልፎ አልፎ ነው፡፡ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በሚያደርጉት ግጭት ክፉኛ ዋጋ እየከፈለ ያለው ሰላማዊ ዜጋው ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ትደግፋለህ በሚል ያሳደዳል፡፡ ህብረተሰቡ ያለው ስጋት ስሰፋ እንጂ ስቀንስ አይስተዋልም፡፡ ተማሪ በብዛት ትምህርት ቤት አይሄድም፡፡ ስሄድም ችግር ስነሳ ወጥቶ መሮጥ ነው፡፡ እናም ስጋቱ ቀላል አይደለም” ነው ያሉት፡፡

ሌላው በዚሁ ሳምንት ውስጥ ወንድማቸውን በሚካሄደው ግጭት መዘዝ ያጡት የቄሌም ወለጋ ዞን አስተያየት ሰጪ ለደህንነታቸው ሲባል ማንነታቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው በሰጡት አስተያየት፤ “ማክሰኞ ጠዋት ነው መጥተው ይዘውት የሄዱ፡፡ የሁለት ልጆች አባት ነበር፡፡ ታጥቀው መንግስትን ለሚወጉ ድጋፍ ታደርጋለህ በሚል ነው በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የተገደለው” ብለዋል፡፡

የተፋላሚዎች ጥቃት

አስተያየት ሰጪዎቹ በሁለቱም ተፋላሚዎች በኩል አንዱ ሌላውን ደግፈሃል በሚል መሰል እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ያነሳሉ፡፡ በቅርቡ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎችን በእጅጉ ያስቆጣው ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሰላማዊ ዜጎች በታጣቂዎች ሲገደሉ መንግስትን ደግፋችሁ ቆማችኋል የሚል ክስ እንደቀረበባቸውም ታውቋል፡፡ ከአርሶ አደር አቅም በእጅጉ የተጋነነ ክፍያ የሚጠየቁባቸው እገታ፣ ዘረፋ እና አፈናዎችም በተለይም በተለያዩ የሸዋ ዞኖች በስፋት የተስተዋለው ጉዳይ ነው፡፡

በመሆኑ ማህበረሰቡ ይህ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን አስተጋብቷል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግስትም ይህንኑን የሰላም ጥሪ በተለያዩ ጊዜያት ማቅረቡን በማሳወቅ፤ ይህንን ጥሪ የተቀበሉ ያሏቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ትጥቅ አውርደው የተሃድሶ ስልጠና መውሰዳቸውን ያመለክታል፡፡

የኦነግ-ኦነሰ ማዕከላዊ ዞን ከመንግስት ጋር ሊደራደር

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ቀደም ሲል  “ለሰላም የተዘረጋው እጅ አይታጠፍም” የሚል ርዕሰ በሰጡት ጽሁፍ የክልሉ መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸው፤ “በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መካከል የማዕከላዊ ዞን አመራር ብሎ ራሱን የሚጠራው፤ ከመንግስት ጋር ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መዘጋጀቱን መሳወቁት ተከትሎ እረጅም ርቀት ሄደን በሰላማዊ ውይይት ልዩነቶችን ለመፍታት ዝግጁነ ነን” ብለዋል፡፡   

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ይህንኑን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠው፤ ይህ የርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ በቡድንም ሆነ በተናጥል ወደ ሰላም የሚመጡትን ታጣቂዎች የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡ “በኦሮሚያ ማዕከላዊ ዞን የሚንቀሳቀስ ቡድን ከመንግስት ጋ በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር ፈቃደኝነቱን አሳይቷል፡፡ ክልላችን መሰል ተግባራን የሚበረታታ በመሆኑ ርዕሰ መስተዳድሩ በቡድንም ሆነ በተናጥል ወደ ሰላም የሚመጡትን ለማስተናገድ በብሔራዊ ክልሉ መንግስት ስም ያለውን ዝግጁነት ያበሰሩበት ጥሪ መሆኑ ነው” ብለዋልም፡፡

አቶ ኃይሉ አክለውም “በሺዎች የሚቆጠሩ ያሏቸው ታጣቂዎች ትጥቅ አውርደው ወደ ሰላም እየተመለሱ በመሆኑ” የሚገቡትን ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ሰጥቶ ከህብረተሰቡ ጋር የመቀላቀል ስራ ከመጠናከሩ ጋር ተያይዞ፤ መሬት ላይም የጸጥታ ይዞታው እየተሸሻለ ለመምጣቱ ማሳያ መኖሩን አስረድተዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር