ምርጥ የአትክልት ዘሮች ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች | ኤኮኖሚ | DW | 02.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ምርጥ የአትክልት ዘሮች ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች

አቶ ኑሪ አወል በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በየተቦ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ናቸው። አቶ ኑሪ ጫት እና በቆሎን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን ያመርታሉ። ከሁለት አመት ወዲህ ግን «ፌር ፕላኔት» ከተሰኘ የእስራኤል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ቲማቲምም ማምረት ጀምረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:10
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:10 ደቂቃ

የአትክልት ምርጥ ዘር

አርሶ አደሩ ባለፈው ዓመት 2,000 የቲማቲም ችግኞችን ሲተክሉ ወደ 8,000 ብር የሚጠጋ ወጪ አውጥተዋል። «ገበያ ወርዶ ነበረ።» የሚሉት አቶ ኑሪ ከዛ ዓመት ምርታቸው ወደ «10,000 ብር ያህል ጥቅም አግኝቻለሁ።» ሲሉ ይናገራሉ።
አቶ ኑሪ እና የዘር እጦት ክፍተትን መሙላት (Bridging the seed Gap) በተሰኘው ፕሮጀክት የተካተቱ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች በማሳቸው የዕለት ተለት ድጋፍ እና ክትትል ይደረግላቸዋል። በአንድ ጥማድ መሬት (አንድ ሺህ ስኩዌር ሜትር አካባቢ) እስከ 120 ሳጥን ቲማቲም ያመረቱት አቶ ኑሪ «ፌር ፕላኔት» የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባቀረበላቸው ድጋፍ ደስተኛ ናቸው።
«ፌር ፕላኔት» የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ የእስራኤል ድርጅት የተሻለ ጥራት ያላቸውና ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ የአትክልት ዘሮችን አቶ ኑሪ ከሚገኙበት የጉራጌ ዞን በተጨማሪ ለሌሎች አካባቢዎችም ማቅረብ ጀምሯል። የ«ፌር ፕላኔት» መስራች እና ኃላፊ ዶ/ር ሾሻን «የዘር እጦት ክፍተትን መሙላት የተሰኘው ፕሮጀክት አላማ በኢትዮጵያ የሚገኙ መካከለኛ ገበሬዎች ከፍላጎታቸው ጋር የሚጣጣሙ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የዘር አይነቶች እንዲያገኙ ማስቻል» እንደ ሆነ ለዶይቼ ቬለ ገልጠዋል። ፕሮጀክቱ አሁን የተጀመረው በቡታጅራ፤ድሬዳዋ፤ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎንደር ተግባራዊ መደረጉንም ጨምረው አስረድተዋል።

Äthiopien Israeli NGO brings high Quality seed to Ethiopian Farmers

የ«ፌር ፕላኔት» መስራች እና ኃላፊ ዶ/ር ሾሻን ሐራን


በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚገኙ የጥናትና ምርምር ተቋማት እና የዘር አቅራቢ ድርጅቶች የሚያገኙትን የአትክልት ዘሮች ለገበሬዎች ለማቅረብ የዶ/ር ሾሻን ሐራን ተቋም ከኢትዮጵያ የመንግስት እና የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል።
«ከተለያዩ የዘር አቅራቢ ኩባንያዎች እና የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ማዕከል የተለያዩ የዘር አይነቶችን እንቀበላለን። በየአካባቢው ለሚገኙት ገበሬዎች የትኞቹ ዘሮች የተሻለ ጥራት ያለው ከፍተኛ ምርት መስጠት እንደሚችሉ እንሞክራለን። ዘሮቹን ከለየን በኋላ ለገበሬዎቹ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እንሰጣለን። ስልጠናዎቹ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ፤የድሬዳዋ ግብርና ቢሮ እና በቡታጅራ ከሚገኘው የመስቃን ወረዳ ግብርና ቢሮ ጋር በትብብር የሚሰጡ ናቸው።»

ከፕሮጀክቱ አጋሮች መካከል አንዱ ግዙፉ የባየር ኩባንያ ነው። ባየር በዚህ ፕሮጀክት ትግበራ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪነት የቲማቲም፤በርበሬ እና ሽንኩርት የተሻሻሉ ዝርያዎችን ያቀርባል።
«እነዚህ ዝርያዎች ከማራቢያ ማዕከላችን የሚመጡ ሲሆን ለኢትዮጵያ ገበሬዎች እጅግ የተሻሻሉ እና የተዳቀሉትን እናቀርባለን። እነዚህ የተዳቀሉ ዝርያዎች የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በሽታን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ ነው።» ሲሉ በባየር ኩባንያ የአትክልቶች ዝርያ የንግድ ምልክት ኃላፊ የሆኑት ኡቨ ዲየክሾርን ያስረዳሉ።


በዓለም አቀፉ የእርሻ እና የምግብ ድርጅት መረጃ መሰረት 12 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ባለ አነስተኛ ይዞታ ገበሬዎች የግብርናው ዘርፍ 95 በመቶ ምርት ባለቤት ናቸው።በግብርናው ዘርፍ ከተሰማሩት መካከል 40 በመቶ ያክሉ ከ0.5 ሔክታር በታች መሬት ያርሳሉ። በዝናብ ላይ ጥገኛ በሆነው የኢትዮጵያ የእርሻ ሥራ የተሰማሩት አርሶ አደሮች በአማካኝ እስከ ስድስት የቤተሰብ አባላት ያላቸው ሲሆን አመታዊ የቤት ወጪያቸውን ለማሟላት ከ2.5 እስከ 2.8 ሔክታር መሬት ያስፈልጋቸዋል። የግብርና ዘርፉ አርሶ አደሮችን ከመመገብ ተሻግሮ ኢኮኖሚውን መደገፍ ይችል ዘንድ በርካታ መሻሻሎች እንደሚያስፈልጉት እንደ የዓለም የእርሻ እና የምግብ ድርጅት ያሉ ተቋማት ይመክራሉ። ዶ/ር ሾሻን ሐራን አሁን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ በጀመሩት እቅድ ዘመናዊውን የአመራረት ስልት ከነባሩ ጋር በማጣጣም እየሰሩ እንደሆነ ይናገራሉ።
«በአርሶ አደሮቹ ነባር የአመራረት ስልት ላይ ውስን ለውጥ ነው የምናደርገው። በምንሰራባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮቹ አነስተኛ የመስኖ ስራዎችን ይጠቀማሉ። ያላቸውን ነባር የአመራረት ስልት ለማሳደግ ስልጠናዎች የምንሰጣቸው ሲሆን የተከሏቸውን አትክልቶች በአግባቡ እንዲንከባከቧቸው እናግዛቸዋለን። ከፍ ያለ ምርት ለማግኘት በደንብ ውሃ ማጠጣት አስፈላጊ ነው። በኢትዮጵያ የተመዘገቡ እና ግልጋሎት ላይ ለመዋል ፈቃድ ያላቸው ማዳበሪያ እና የእጽዋት ደህንነት መጠበቂያዎች እንጠቀማለን።»


እንደ ኡቨ ዲየክሾርን አስተያየት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ሙሉ ትኩረታቸውን በማሳቸው ላይ ብቻ ሊያደርጉ አይገባም። የለት ተለት የገበያ ዋጋ መከታተል እና የገበያውን ፍላጎት ማጥናት አስፈላጊ መሆኑን ኢቨ ዴክሽሆርን ይጠቁማሉ።
የፌር ፕላኔት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በአራት አካባቢዎች ለጀመረው እቅድ ከባየር ኩባንያ በተጨማሪ ሴንጌንታ፤ሊማግሬን፤ኤንዛ ዛደን፤ ኢስት ዌስት ሲድ ከተሰኙ ኩባንያዎች እና ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ተቋም ከፍተኛ ጥራት ያለው እና ምርታማ የዘር አይነቶች በመቀበል ለአርሶ አደሮች ያቀርባል።ድጋፍ ይደረግለታል። እንዲህ አይነት ምርጥ ዘሮች ለኢትዮጵያ አርሶ አደር ምን ያክል አዋጪ ናቸው? «ለአርሶ አደሮቹ ውድ የሚሆኑት ምርጥ ዘሮቹ አይደሉም።» የሚሉት ዶ/ር ሾሻን ሐራን «በአብዛኛው ማዳበሪያ እና የእርሻ ማሳቸውን በመስኖ ለማልማት የሚያስፈልገው ነዳጅ እና ኬሚካሎች ከዘሮቹ በላይ ወጪ ያስወጧቸዋል። በእርግጥ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ዘሮች ዋጋው ከፍ ይላል። የምናደርገው ምንድነው በቅድሚያ ከፕሮጀክቱ ዘሮቹን እናቀርባለን። ከዚያ አርሶ አደሮቹ ከመጀመሪያው የምርት ዘመን ከሚያገኙት ትርፍ የተወሰነውን ለሚቀጥለው የምርት ዘመን እንቆጥቡ እንመክራቸዋለን። ስለዚህ የሚቀጥለውን የምርት ዘመን ብድር ሳይወስዱ መጀመር ይችላሉ ማለት ነው።» በማለት ገልጠዋል።


በዚህ የ«ፌር ፕላኔት» ፕሮጀክት በአንድ ጊዜ ከ20 እስከ 50 ለሚደርሱ አርሶ አደሮች በቡድን ስልጠና እንደሚሰጡ የሚናገሩት ዶ/ር ሾሻን ሐራን ትልቁ ስኬት ግን የጥቂቶች ሙከራ በጎረቤቶቻቸው እና የአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ መሆኑን ያስረዳሉ። የግብርና ባለሙያዋ ይህ እቅዳቸው 50,000 አርሶ አደሮችን ለማካተት ለማካተት ያለመ ሲሆን እቅዱ ከተሳካ ለመላ ኢትዮጵያውያን አትክልት ማቅረብ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic