“ማዊስሌ” ፀረ-አሸባብ ቡድን በሶማልያ | አፍሪቃ | DW | 09.10.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

“ማዊስሌ” ፀረ-አሸባብ ቡድን በሶማልያ

በሶማሊያ መካከለኛው ሸበሌ እና ሒራን ክልሎች ጎሳን መሠረት ያደረገ “ማዊስሌ” የተባለ ጸረ-አሸባብ የአካባቢ ሚሊሺያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥሩ ዝና እያተረፈ መጥቷል፡፡ “ማዊሲሌይ” በሱማሊኛ “ዩኒፎርም የማይለብሱ” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:51

“ማዊሲሌይ” በሱማሊኛ “ዩኒፎርም የማይለብሱ” የሚል ትርጓሜ አለው

በተለይ ባለፈው ሳምንት መግቢያ የማውሲሌይ ሚሊሺያዎች ከአሸባብ ታጣቂዎች ጋር በሒራን ክልል ለሦስት ቀናት ውጊያ ካደረጉ ወዲህ የሀገሪቱ መገናኛ አውታሮችን እና ማህበራዊ ሜዲያ ትኩረትን ስበው ነው የሰነበቱት፡፡ በውጊያውም ባለፈው ባለፈው ሳምንት ሒባድ አሊ ባሳር የተባለው መሪያቸው እና ምክትሉ “አደን ያባል” ከተባለች ከተማ አቅራቢያ እንደተገደሉበት ተዘግቧል፡፡

አሸባብ በሒራን ክልል ከአምስት ዐመታት በፊት ልጆቻችሁን ለታጣቂነት ካልሰጣችሁኝ፣ ግብርም ካላዋጣችሁ እያለ ጎሳዎችን ማስገደድ ሲጀምር እና በእንስሳት ሃብታቸው ላይ “ዘካት” የተሰኘ ግብር ሲጥል፣ ጥቂት በጎ ፍቃደኞች ማውሲሌይ ሚሊሻን እንዳቋቋሙ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ “ማዊሲሌይ” በሱማሊኛ “ዩኒፎርም የማይለብሱ” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡

ማውሲሌይ ሚሊሻዎች የራሳቸው ሐይማኖታዊ ርዕዮት ይኖራቸው እንደሆነ ወደ ሞቃዲሾ ስልክ ደውዬ ሱማሊያዊውን የድረ ገጽ አዘጋጅ እና ለተለያዩ ዐለም ዐቀፍ ዜና አውታሮች ወኪል በመሆን የሚሰራውን ጋዜጠኛ ሞሃመድ ኦዶዋን ጠይቄው ነበር፤

ርዕዮተ ዐለም እንኳ የላቸውም፤ የተቋቋሙበት ዋነኛው ምክንያት ንብረታቸውን ከአሸባብ ንጥቂያ ለመከላከል ሰሉ ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ጎሳዎች አርብቶ አደሮች በመሆናቸው ግመሎቻቸውን እና ፍየሎቻቸውን ከአሸባብ ዝርፊያ ለመጠበቅ እና ልጆቻቸውን ከአሸባብ ግዳጅ ምልመላ ለመከላከል ሲሉ ነው፡፡ 

የሱማሊያን ጉዳይ የሚከታተሉ ተንታኞች ሚሊሺያውን በኢራቅ አልቃይዳን ካሸነፈው የሱኒዎች ንቅናቄ ጋር ያመሳስሉታል፡፡

የሱማሌ መንግሥት ለማውሲሌይ ሚሊሻዎች የጦር መሳሪያ እገዛ ያደርግላቸው እንደሆነ እና ሚሊሺያዎቹም አሸባብን በማሸነፍ ረገድ አስተማማኝ አጋር ይሆኑት እንደሆነ ላነሳሁለት ጥያቄም መሐመድ እንዲህ ሲል ይመልሳል፤

አስተማማኝ አጋር መሆን እንኳ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ሚሊሺያዎቹ እኮ በደንብ የተደራጁ አይደሉም፡፡ የጎሳ ሚሊሺያዎች ናቸው፡፡ እንደሚመስለኝ ላሁኑ መንግሥት ዘመናዊ ጦር መሳሪያ ድጋፍ ቢያደርግላቸው ጥሩ ላይሆንለት ይችላል፡፡ ለምን ቢባል አሸባብ ከእነዚህ አካባቢዎች ከተባረረ በኋላ እኮ ሚሊሺያዎች የታጠቁ እስከሆኑ ድረስ ወደፊት ለመንግሥት ራሱ የጸጥታ ስጋት ሊሆኑበት ይችላሉ፡፡ እናም መንግሥት ሚሊሺያዎቹን በዘመናዊ ጦር መሳሪያ ለመደገፍ ከመጣደፍ ይልቅ ጉዳዩን በጥንቃቄ እያጤነው ያለ ይመስለኛል፡፡ በመካከለኛው ሸበሌ እና ሒራን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ሚሊሻዎችም እኮ ብቅ እያሉ ነው፡፡ ማውሲሌይ የተበታተኑ ሚሊሺያዎች ናቸው፡፡ ነገሩ ለሱማሊያዊያን ጥሩ ዜና ቢሆንም አሸባብ ግን ከሚሊሺያዎቹ አንጻር በጣም የተደራጀ ነው፡፡ 

ማውሲሌይ ሚሊሻዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው ያሉ ሲሆን ማዕከላዊ ዕዝም የላቸውም፡፡ እናም በቁጥር ምን ያህል እንደሚሆኑም አስተማማኝ መረጃ የለም፡፡ መሐመድ ግን በጠቅላላው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ሚሊሻዎች ከ500 አይበልጡም የሚል ዕምነት አለው፡፡

የአካባቢ አስተዳዳሪዎች እና የፓርላማ ተመራጮች ፌደራል መንግሥቱ ለሚሊሻዎቹ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ሲወተውቱ እንደቆዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ባለፈው ረቡዕ ግን የሀገሪቱ ጦር ሃይል አዛዥ ጄኔራል ዳሂር አደን ኤልሚ ለማውሲሌይ ሚሊሻ የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ድጋፎችን ሊያደርጉ መሆኑን ለሀገሪቱ ዜና አውታሮች ተናግረዋል፡፡ ሚሊሻዎቹ በቂ ድጋፍ ካገኙ ደሞ በአካባቢው በረጅም ጊዜ ለአሸባብ ስጋት እንደሚሆኑበት እና ሌሎችም ጎሳዎች የእነሱን ፈለግ ሊከተሉ እንደሚችሉ ብዙ ታዛቢዎች እምነት አላቸው፡፡

አሸባብም በበኩሉ የአካባቢው ጎሳዎች እና ንዑስ ጎሳዎች የውጭ ቅጥረኞች ከሚላቸው የማውሲሌ ሚሊሻዎች ጋር እንዳይተባበሩ ጥሪ በማድረግ ተጠምዷል፡፡

የማውሲሌይ ሚሊሻዎች ትኩረት የሳቡበት ዋነኛው ምክንያት የሱማሊያ ብሄራዊ ጦር ሠራዊት አሸባብን ለማሸነፍ ያለው ብቃት ክፉኛ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ነው፡፡ የአፍሪካ ሕብረት ተዋጊ ሃይል አሚሶምም ቢሆን በገንዘብ፣ ቁሳቁስ እና በወታደር እጥረት ክፉኛ መቸገሩን ደጋግሞ ሲገልጽ ይሰማል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደሞ አምስት የሱማሊያ ፌደራል ክልሎች የፕሬዝዳንት ሞሃመድ ፎርማጆ መንግሥት አሸባብን የሚዋጋበትን ወታደራዊ ስትራቴጅ እና ጣልቃ ገብነቱን በመቃወም ካለፈው ወር ጀምሮ ከሞቃዲሾው መንግሥት ጋር ትብብራቸውን አቋርጠዋል፡፡ ውጥረቱም ከአሸባብ ጋር የሚደረገውን ውጊያ እንዳያቀዛቅዘው ተሰግቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጭው ሕዳር በሚደረገው የክልል አስተዳዳሪነት ምርጫ የአሸባብ መስራች የነበረው እና ታች አምና ለመንግስት እጁን የሰጠው ሙክታር ሮቦው ለደቡባዊ ምዕራብ ክልል አስተዳዳሪነት እንደሚወዳደር ባለፈው ሳምንት ማስታወቁን ተከትሎ፣ መንግስት እገዳ ጥሎበታል፡፡ ሮቦው ተወዳድሮ ካሸነፈ ግን በአካባቢው ከአሸባብ ጋር በሚደረገው ውጊያ ላይ ሁነኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ጋዜጠኛ ሞሃመድም ሆነ በርካታ ታዛቢዎች ያምናሉ፡፡

ዐለም ዐቀፉ የግጭት አጥኝ ቡድን «International Crisis Group» ባለፈው ወር መገባደጃ አሸባብን አስመልክቶ ባወጣው ሰፊ ሪፖርት የሽብር ቡድኑ አሁንም በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሰፊ መረብ እንዳለው እና ከባድ የጸጥታ ስጋትም ደቅኖ እንደሚቀጥል ገልጧል፡፡ የአውሮፓ ሕብረት ከ30 ዐመታት በኋላ የመጀመሪያው የሆነውን የ100 ሚሊዮን ዩሮ ቀጥተኛ የበጀት ድጎማ ለሱማሊያ መፍቀዱን ተከትሎ እንኳ ባለፈው ሳምንት መባቻ ሞቃዲሾ ውስጥ በኅብረቱ ኮንቮይ ላይ የቦንብ ጥቃት ማድረሱ ይታወሳል፡፡

 

ቻላቸው ታደሠ

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic