1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መልዕክት፣ የመብት ተሟጋቾች ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 5 2016

ፊት ለፊት በሚደረግ ጦርነትና ዉጊያ ከሚያልቀዉ ሕዝብ በተጨማሪ ገበሬዎች፣ተማሪዎች፣ነጋዴዎች፣የመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ ጄኔራሎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣አባገዳዎች፣የኪነት ሰዎች፣ ፖለቲከኞች አንድም በተናጥል አለያም በጅምላ ተረሽነዋል። ባቴም በጥይት ተደብድቦ በመገደል የመጀመሪያዉ አይደሉም።ምናልባት የመጨረሻዉ አይሆኑምም ይሆናል።

https://p.dw.com/p/4fo4W
ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የኦሮሞና የአማራ አማፂያን ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ አድርገዋል
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ በቅርቡ በነቀምትና ባሕርዳር ባደረጉት ጉብኝት «መገዳደል ይብቃ» ብለዋልምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

ማሕደረ ዜና፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መልዕክት፣ የመብት ተሟጋቾች ዘገባ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈዉ ሳምንት የኢትዮጵያን ሁለት ትላልቅ ግን በአመፅ፣ግጭት፣ሁከትና ዉጊያ  የሚታበጡትን ክልሎችን ጉብኝተዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ ነቀምትና ባሕር ላይ ባደረጉት ንግግር የሰላምን አስፈላጊነት ሰብከዋል፤ በየክልሉ የሸመቁ አማፂያን የየክልሉ መስተዳድሮችን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አድርገዋል።ባማሩ የኦሮምኛና የአማርኛ ቃላት የተሰበከዉ ሰላምና የሰላም ጥሪ ገቢር የሚሆንበትን መንገድ አለመጠቆማቸዉ እንጂ ቅጭቱ።የጠቅላይ ሚንስትሩ የሰላም መልዕክትና ጥሪ ሲንቆረቆር ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች  ድርጅቶች፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ለዕልቂትና ፍጅት እንጂ ከሰላም ሩቅ መሆኗን መዘገባቸዉ ነዉ ሕቅ ባዩ ተቃራኒ ሐቅ። የዛሬ ዝግጅታችንም ትኩረት አድርገነዋል።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

 «ኦሮሞ አሁን ነፃ ወጥቷል» ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ

እዉቁ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦነግ) ፖለቲከኛ ባቴ ኡርጌሳ መቂ-ኦሮሚያ ክልል ዉስጥ በጥይት ከተገደሉ ሶስተኛ ሳምንታቸዉ።ኦሮሚያ ፖለቲከኛ፣ አርቲስት፣ምሁር፣ የጦር መሪ፣የኃይማኖት ሰባኪ፣ ወዘተ በየጊዜዉ ታበቅላለች።የዚያኑ ያክል ብዙዎቹን ለፍሬ ሳታበቃ ትቀጫለች።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ባለፈዉ ሮብ ነቀምት-ወለጋ ስታዲዮም ለተሰበሰብ ሕዝብ ባደረጉት ንግግር የኦሮሞ ሕዝብ ለመብቱ መከበር ለበርካታ ዓመታት ባደረገዉ ትግል ብዙ ሺዎች  መስዋዕትነት ከፍለዋል።ያዘመን ግን ዛሬ አልፏል።ኦሮሞ ነፃ ወጥቷል።
ይሁንና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት ባለፉት 5 ዓመታት ኢትዮጵያን በጥቅል ኦሮሚያን በተናጥል ያመሰቃቀለዉ የሥልጣን፣ የጎሳ፣ የሐብት ክፍፍል ጠብ፣ ግጭትና ዉጊያ የፈጀዉ ሰዉ ቁጥር በረጅም ጊዜ ታሪካቸዉ ታይቶ አይታወቅም።

«አሁን አገሪቱ ያለችበት፣ ሕግ የማይከበርበት፣ ሰብአዊ መብቶች በጣም ባስከፊ ሁኔታ የሚጣስበት፣ እኔ በታሪክ፣ እኑ እንኳን ሰብአዊ መብት ዉስጥ በሰራሁበት ከ20 ዓመት በላይ ጊዜ፣ የመጨረሻ አስከፊም፣ አስፈሪም የሰብአዊ መብት ሁኔታ ገጥሞን አያዉቅም።»

ይላሉ አቶ ያሬድ ሐይለ ማርያም።የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል የበላይ ኃላፊ። ፊት ለፊት በሚደረግ ጦርነትና ዉጊያ ከሚያልቀዉ ሕዝብ በተጨማሪ ገበሬዎች፣ ተማሪዎች፣ነጋዴዎች፣የመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ ጄኔራሎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣አባገዳዎች፣የኪነት ሰዎች፣ ፖለቲከኞች አንድም በተናጥል አለያም በጅምላ ተረሽነዋል።ባቴም በጥይት ተደብድቦ በመገደል የመጀመሪያዉ አይደሉም።ምናልባት የመጨረሻዉ አይሆኑምም ይሆናል።

የኦሮሞ ሕዝብ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት በርግጥ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር፣ በራሱ ቋንቋና ባሕል በነፃነት የሚዳኝ፣የሚገለገልበትን ነፃነት አግኝቷል።ግን ሰላማዊዉ ሰዉ እየተገደለ፣ ታጣቂዎቹ እየተገዳደሉ መሆናቸዉን ጠቅላይ ሚንስትሩ አልካዱም።መገዳደል እንዲቆም ጠይቀዋልም።

የባቴ ኡርጌሳ ገዳዮች ማንነት እስካሁን በግልፅ አልታወቀም
የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦነግ) ታዋቂ ፖለቲከኛ አቶ ባቴ ኡርጌሳ ሚያዚያ መጀመሪያ ላይ መቂ-ኦሮሚያ ክልል ዉስጥ በጥይት ተደብደዉ ተገደሉምስል Private

እንዴት ይቁም? ማንስ ያስቁመዉ? የኦሮሞ ሕዝብ ባለፉት አምስት ዓመታት ያለቁ ዉዶቾን ለመዘከር፣ ገዳዮቹን ለፍርድ ለማቅረብ፣ ሌላ ግድያ እንዳይደርስ ለመከላከል  ሙሉ መብት፣ አቅም፣ነፃነትም አግኝቷል ቢባል በርግጥ እብለት ነዉ።

 

ባሕር ዳር ድልድይ ገነባች ግን----?

ኢትዮጵያ ሁለተኛ ትልቅ ክልል አማራ አምባቸዉ መኮንንን፣ አሳምነዉ ፅጌን፣ ግርማ የሺጥላን ሌሎች ከወለጋ እስከ ሰሜን ሸዋ ያለቁ ወገኖቹን፣ ለማስታወስ፣ ለመርገም ይሁን ለማድነቅ፣ ተፈናቃዮቹን ለማስተናገድ ፋታ የለዉም።የአማራ ሕዝብ መርዓዊ ላይ ያለቁ ወገኖቹን ይሁን የላስታ፣የራያ-አለማጣ ፖለቲከኞችን አሟሟት ለማጣራት ቀርቶ የየራሱንም የነገ ደሕንነት ለማረጋገጥ ምንም ዋስትና የለዉም።
የክልሉ ርዕሰ ከተማ ባሕርዳር ግን አገልግሎት መስጠት አለመስጠቱ ቢያጠያይቅም ድልድይ አስመረቀችን ሰማን።ጠቅላይ ሚንስትር ዐባይ አሕመድም የክልሉን መሪዎች አድንቀዉ እንደነቀምቴዉ ሁሉ ለአመፁ ተዋጊዎች ጥሪ አድረጉ።
«ይብቃን መገዳደል ይብቃን ጥፋት።ይብቃን አላስፈላጊና የማያሻግር ጉዞ።ድልድይ የሌለዉ ጉዞ፣ ኢትዮጵያን አንድ የማያደርግ ጉዞ።የኢትዮጵያን ሕዝቦች በእኩል የማያከብር ጉዞ ሥለማይጠቅመን ኑ ወደ ክልላችሁ ተመለሱ።ከፕሬዝደንታችሁ ጋር ሆናችሁ ክልላችሁን አልሙ።----»
ግን እንደገና እንዴት?የጠቅላይ ሚንስትሩ መልዕክት ከነቀምትና ከባሕርዳር በሚሰማበት መሐል ባለፈዉ አርብ ሁለት ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ ባወጡት ዘገባ እንዳሉት የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ነዉ።

በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባዉ ድልድይ።ባለፈዉ ዕሁድ ተመርቋል
አማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባሕር ዳር ከተማ ዉስጥ በዓባይ ወንዝ ላይ አዲስ የተገነባዉ ድልድይ

 

ኢትዮጵያ ለሰላማዊ ሰዎች እንቅስቃሴ «አደገኛ ሐገር»

ሑዩማን ራይትስ ዎችና ፊዚሽያን ፎር ሁዩማን ራይትስ የተባሉት ድርጅቶች የጥናት ዉጤታቸዉን የሐገራትን የሰብአዊ መብት ይዞታን ለሚገመግመዉ ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት አስረክበዋል።ምክር ቤቱ Univeresal Periodic Review (UPR) የተባለዉን ግምገማ በየሐገራቱ ላይ የሚያደርገዉ በየአራት ዓመቱ ከመንፈቁ ነዉ።
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታ ከዚሕ ቀደም ሶስቴ ተገምግሟል።የመጨረሻዉ የተደረገዉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2019 ነበር።አራተኛዉ ዘንድሮ ይደረጋል።እንደ ሁለቱ ድርጅቶች ሁሉ ለምክር ቤቱ ዘገባ ያቀረበዉ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል የበላይ ኃላፊ ያሬድ ሐብተማርያም እንደሚሉት የግምገማዉ ሒደት ረጅም፣ብዙዎች የሚሳተፉበትና ብዙ፣ ረጅምና ዉስብስብ ሒደት ያለዉ ነዉ።

«ረጅም ሂደት ነዉ ያለዉ፣ የግምገማዉ ሂደት።በዚያ ሐገር ላይ ጉዳይ አለን ብለዉ የሚያስቡ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ባለድርሻ አካላት፣ የተባበሩት መንግስት ድርጅት አባል መንግስታት ጭምር በዚያ (በሚገመገመዉ) ሐገር ዉስጥ ሥለታዘቧቸዉ የሰብአዊ መብት ሁኔታዎች ግምገማዉ ከመጀመሩ ከወራቶች በፊት ዘገባ ያቀርባሉ።»
የዓለም ኃያል፣ሐብታም፣ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ይባሉ የነበሩ መንግስታት ከጋዛ እስከ ዩክሬን በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚያደርሱት ግፍና ሰቆቃ፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ እንዳለዉ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ የፀናዉን የዓለም የሰብአዊ-ፖለቲካዊ ሕግና ሥርዓት እየመነቃቀረዉ ነዉ።

በዚሕ እዉነት መሐል ኃያላን መንግስታት  የሌሎች መንግስታትን የሰብአዊ መብት ይዞታ የመገምገም፣የመተቸትና የመዉቀስ ሞራልና ተዓማኒነት ያገኛሉ ብሎ ማሰብ የዋሕነት ሊሆን ይችላል። የየራሳቸዉን ኃያል መንግስታት የሚያደርሱትን ግፍና በደል የሚያጋልጡት የመብት ተማጋች ድርጅቶች ጩኸት ግን እንደቀጠለ ነዉ።በሚቀጥለዉ ሕዳር በይፋ ይጀመራል ለተባለዉ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ይዞታ ግምገማ የተጠናቀረዉ የሒዩማን ራይትስ ዋችና የፊዚሻንስ ፎር ሁዩማን ራትይትስ ዘገባ እንደሚለዉ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ለሰላማዊ ሰዎች እንቅስቃሴ አደገኛ ሐገር ናት።
በዘገባዉ መሰረት ከትግራይ ጦርነት እስከ ወለጋ ጭፍጨፋ፣ከአማራ ክልል ግጭት እስከ ሸገር ሲቲ ቤት ፈረሳ፣ ከመንገድ ላይ እገታ፣ ግድያ እስከ መርዓዊ ርሸና፣ ከጋዜጠኞች እስራት እስከ እንተርኔት መቋረጥ፣ ኢትዮጵያ ሁሉም ዓይነት ግፍና በደል የሚፈፀምባት፣ ተጠያቂነት የሌለባት፣ ሕግና ሥርዓት የፈረሰባት ሐገር ናት።ዘገባዉ በጣም ያስፈራል።አቶ ያሬድ ግን ያነበበከዉ ከሆነና ከሚሆነዉ በጣም ትንሹን ነዉ ይላሉ።
«አንተ እዚሕ ላይ የተዘረዘሩት ነዉ ያስፈሩሕ ግን ወደፊት ዶክሜንት የሚደረገዉ ነገር ወደፊት ምናልባት በዚሕ ሪፖርት ከተዘረዘረዉ ነገር በብዙ እጥፍ የገዘፈ ነዉ የሚሆነዉ።ወለጋ ዉስጥ የተፈፀሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አካባቢዉ የግጭት ቀጠና በመሆኑ ገና አልተሰነዱም።አልተመረመሩም።በቤኒ ሻንጉል በጋምቤ---ምክንያቱም ባንድ ጊዜ»
የሁዩማን ራትይስ ወችና የፊዚሻንስ ፎር ሑዩማን ራይትስ ዘገባ እንደሚለዉ ትግራይ፣አማራ፣ኦሮሚያ፣ አፋር፣በኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላ ሌሎች ሥፍራዎች ለተፈፀሙ ግድያ፣እገታ፣ የሴቶች መደፈር፣ የሰዎች መፈናቀል ወዘተ የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች፣የኤርትራ ጦር፣ የትግራይ ተዋጊዎች፣ የአማራና የኦሮሚያ ክልል  አማፂ ኃይላት፣የሁሉም ወገኖች ተባባሪ ሚሊሻዎችና ሌሎች ታጣቂዎችና ዘራፊዎች በሙሉ ደረጃዉ ይለያይ እንጂ ተጠያቂ ናቸዉ።

የሑዩማን ራይትስ ዋችና የፊዚሽያን ፎር ሑዩማን ራይትስ ዘገባ እንደሚለዉ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ይዞታ እያሽቆለቆለ ነዉ
የሑዩማን ራይትስ ዋች አርማ።ድርጅቱ ባለፈዉ አርብ ከአንድ ሌላ ድርጅት ጋር ሥለኢትዮጵያ ያጠናቀረዉን ዘገባ ለተመድ አስረክቧል።ምስል Human Rights Watch

ከ6 ዓመት በፊት የጋዜጠኞች ነፃነትን በማክበር የአፍሪቃ አብነት ተብላ የነበረችዉ ኢትዮጵያ ዘንድሮ ብዙ ጋዜጠኞችን በማሰርና የመናገር ነፀነትን በመገደብ ከ180 ሐገራት 141ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።ዛሬ፣ ያዩ እንደሚመሰክሩት ከአዲስ አበባ አዳማ ወይም ናዝሬት፣ ሐዋሳ ወይም ደሴ  መጓዝ በነብስ ከመወራረድ እኩል ይቆጠራል።ከአዲስ አበባ ደብረ ማርቆስ፣ መቀሌ፣አሶሳ፣ ድሬዳዋ ወይም ጂጂጋ ለመሒድ ዉድ ዋጋ ከፍሎ አዉሮፕላን መጠበቅ ግድ ነዉ።

ኢትዮጵያ የግጭት ቀጠና ሐገር

የአፍሪቃ የነፃነት አብነት፣የብሔር ብሔረሰቦች ሙዝየም፣አብሮ የመኖር ምሳሌ፣ የሚባሉ የኢትዮጵያ ማድነቂያ ቅፅሎች አንድም በፊትም አልነበሩም ሁለትም ለኢትዮጵያዉን የነበር ታሪክ ናቸዉ። ኢትዮጵያዉያን ወደዱም ጠሉ ያቺ ጥንታዊ፣ ታሪካዊ፣ «የአትንኩኝ» ባዮች መፍለቂያ ሐገራቸዉ ዛሬ የግጭት ቀጠና ናት።እንደገና አቶ ያሬድ።
«አሁን አገሪቷ፣ የግጭት ቀጠና ተብለዉ በሚፈረጁ አገሮች ዉስጥ እዚያ ደረጃ ትገኛለች።ምክንያቱ የሐገሪቱ ትልቅ፣ ሰፊ የሚባለዉ ክፍል የታጠቁ ኃይሎች ከመንግስት ጋር የሚፋለሙባቸዉ፣ እንቅስቃሴ የማይደረግባቸዉ---» 

ኢትዮጵያ ባጭር ጊዜ ዉስጥ መቶ ሺሕዎች ያለቁ፣የተደፈሩ፣ ሚሊዮኖች የተፈናቃሉ፣ ብዙ ሚሊዮኖች የተራቡና የተሰደዱበት ጦርነት፣ግጭት፣ዉጊያ፣ ጥቃትና በሕይወት ያሉ ዜጎችዋን በሰላም የመኖር ዋስትና ያሳጣዉ ምክንያት ብዙዎች ብዙ ጊዜ እንዳሉት ብዙ ነዉ።መሰረታዊዉ ምክንያት ግን አቶ ያሬድ እንደሚሉት መንግስት ሕግና ሥርዓት አለማስከበሩ ነዉ።
ከምስቅልቅሉ መዉጪያ መንገድ አለ ይሆን? አማፂያን፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የፖለቲካ ተንታኞች፣ ገዢዉ ፓርቲም ጭምር በየጊዜዉ በየፊናቸዉ መፍትሔ የሚሉትን ሐሳብ መጠቆማቸዉ አልቀረም።ሰብሳሰብ ብለዉ፣ ሰፋ፣ ጠለቅ፣ በሰል አድርገዉ በየመፍሔ ሐሳቦቹ ላይ ለመነጋገር ግን ሐሳብ ሰጪዎቹ ራሳቸዉ አልቻሉም፣ አልፈለጉም፣ አይስማሙም ወይም የአሜሪካ አዉሮጶችን ጫናና ሽምግልና ይጠብቃሉ።ልክ እንደ ፕሪቶሪያዉ።

ያዩ እንደሚሉት ከኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ወደ አዳማ ወይም ወደ ሌላ ቅርብ ከተማ መጓዝ አደገኛ ነዉ
ያዩ እንደሚሉት ከኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ወደ አዳማ ወይም ወደ ሌላ ቅርብ ከተማ መጓዝ አደገኛ ነዉምስል Seyoum Getu/DW

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ