1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ ሱዳን፣ ሁሉም የሚፈልጋት፣ ሁሉም የዘነጋት ሐገር

ሰኞ፣ ሰኔ 3 2016

አስር ሺዎችን የፈጀና የሚፈጀዉን ጦርነት ብዙዎች የሁለቱ የቀድሞ ወዳጅ ጄኔራሎች የሥልጣን ጥማት ያስከተለዉ ይሉታል።ሌሎች የነባሩ የሱዳን ጦር ኃይልና የአዲሱ የሱዳን ልዩ ኃይል ፍጥጫ ዉጤት ያደርጉታል።የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች በሰሜናዊና ደቡባዊ ሱዳን ዜጎች መካከል የፈጠሩት የሐብት፣ የሥልጣንና ሥልጣኔ መበላለጥ ዉጤት ነዉ ባዮችም አሉ።

https://p.dw.com/p/4gsfq
ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች አንዳሉት በጦርነቱ ከተገደሉት በተጨማሪ ከ9 ሚሊዮን ያክል ተፈናቅለዋል ወይም ተሰድደዋል
የዳርፉር ተፈናቃይ።አንድ ዓመት ባስቆጠረዉ ጦርነት ከተገደሉ፣ ከተፈናቃሉና ከተሰደዱት አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት ናቸዉምስል Albert Gonzalez Faran/Unamid/Han/dpa/picture alliance

ማሕደረ ዜና፣ ሱዳን፣ ሁሉም የሚፈልጋት፣ ሁሉም የዘነጋት ሐገር


የሱዳን ወታደራዊ ገዢ ጄኔራል አቡዱል ፈታሕ አል ቡርሐን «ሽፍታ» ካሏቸዉ ከዋና ባላንጣቸዉ ከጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐምዲቲ) ጋር አልደራደርም እንዳሉ ነዉ።ሐምዲቲ የሚያዙት ፈጥኖ ደራሽ ጦር የአል ቡርሐን ጠላቱን ለማበርከክ ከእንዱሩማን እስከ ዳርፉር እያጠቃ ነዉ።በመሐሉ የሱዳን ሕዝብ በተፋላሚ ኃይላት ዉጊያ፣በረሐብና በሽታ እያለቀ፣ ቀሪዉ እየተፈናቀለ፣ እየተሰደደ፣በየተሰደደበት ሐገርም እየተጠቃ፣ እየተሰቃየ ነዉ።ከዩክሬን እስከ ጋዛ በሚደረገዉ ጦርነት የተዘፈቀዉ ዓለም ተንታኞች እንደሚሉት ለአፍሪቃ-አረባዊቱ ሐገር ሕዝብ እልቂት ካለፍ አገደም መግለጫ ሌላ ሌላ ማድረግ አልፈቀደም።እስከ መቼ? ያፍታ ዝግጅታችን ጥያቄ ነዉ። 

ሱዳን በ1960ዎቹ መጀመሪያ (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ከመፈንቅለ መንግስት፣ ከፖለቲካ ቀዉስ፣ ከግጭትና ጦርነት ተለይታ አዉታዉቅም።በዚሕ ሁሉ ፈተና መሐል፣ ሱዳን የኖሩ ወይም በሱዳን በኩል ያለፉ የዉጪ ዜጎች በተደጋጋሚ እንደሚመሰክሩት የሱዳን ሕዝብ ሩሕሩሕ፣ ደግ፣ ፈጣሪዉን አጥብቆ አማኝ፣ የዋሕም ነዉ።

ያቺን የደጎች ሐገር አሁን ያመሰቃቀለዉ ጦርነት እምና ሚያዚያ እስከተጫረበት ጊዜ ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን፣ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያና የማዕከላዊ አፍሪቃ ሥደተኞችን ያ ሕዝብ ያስተናግድ ነበር።ዛሬ ሟች፣ ተፈናቃይ፣ ስደተኛ፣ ረሐብተኛዉ ሱዳናዊ ነዉ።በጣም ጥቂቱ ኢትዮጵያ ቢገቡ የኢትዮጵያ ተጣቂዎች ላንድ ዓመት እንኳን መታገስአቅቷቸዉ ተኩስ ከፈቱባቸዉ።

የሠላማዊዉ ሕዝብ መከራና የርዳታ እጦት

የዓለም ምግብ ድርጅት የምሥራቅ አፍሪቃ ኃላፊ ማይክል ደንፎርድ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ደግሞ ከሞትና ስደት የተረፈዉ ሱዳናዊ በረሐብና በምግብ እጥረት እየተሰቃየ ነዉ።
«ሱዳን ያለዉ ሁኔታ ከፍተኛ ድቀት ነዉ።ሐገሪቱ ረሐብና የምግብ እጥረት እያጋጠማት ነዉ።ለ5 ሚሊዮን ሕዝብ ምግብ ለማቅረብ እየጣርን ነዉ።ይሕ ቢሳካልን እንኳ በቂ አይደለም።ችግረኛዉ ህዝብ ጋ መድረስ ካልቻልን፣ ከሁሉም በላይ ግጭቱ ካልቆመ ርዳታ የሚፈልገዉን ሕዝብ መርዳት አንችልም»  

የርዳታ ድርጅቶች ለሱዳን ሕዝብ መርጃ ከጠየቁት ገንዘብ እስካሁን ያገኙት ከሚያስፈልገዉ ከ15 በመቶ ያነሰ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ሐብታም መንግስታት ገንዘብ ካልሰጡ፣ ርዳታዉ ለችግረኛዉ ፈጥኖ ካልደረሰ በሚቀጥለዉ መስከረም እስከ 2.5 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ በረሐብ ያልቃል።

ዓመት ያለፈዉ ጦርነት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሰዉ ጉዳትና የረሐቡ ስጋት ተተንትኖ ሳያበቃ አል ፋሽር የተባለችዉን የደቡብ ምዕራብ ሱዳን ከተማን ለመያዝና ላለማስያዝ በሚደረግ ዉጊያ በሁለት ሳምንት ዉስጥ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸዉ ተዘገበ።ድንበር የለሽ ሐኪሞች የተሰኘዉ ግብረ ሰናይ ድርጅት እንደሚለዉ አል ፋሽር አጠገብ በተደረገዉ ዉጊያ ከተገደሉት በተጨማሪ አንድ ሺሕ ያክል ሰዎች ቆስለዋል።አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰዎች ናቸዉ።

የቀድሞዎቹ ወዳጅ ጄኔራሎች በከፈቱት ጦርነት 10 ሺዎች አልቀዋል።ሚሊዮኖች ተሰድደዋል ወይም ተፈናቅለዋል።
ነበር።ከግራ ወደቀኝ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎና የመከላከያ ሠራዊት አዛዥ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አልቡርሐን።ምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

ሱዳን በተፈናቃዮች፣ በስደተኞችና ችግረኞች ብዛት የመንን በልጣለች።ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝቧ አንድም ተፈናቃይ አለያም ሥደተኛ ነዉ።ከ25 ሚሊዮን የሚበልጠዉ ሕዝቧ ሰብአዊ ርዳታ ፈላጊ ነዉ።

«የምድር ላይ ጀሐነቧ» ከተማ

የጀርመን፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን የጋራ መድረክ ሊቀመንበር ማሪና ፔተር እንደሚሉት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የሠፈሩባትን የዳርፉርን ትልቅ ከተማ የከበበዉ ፈጥኖ ደራሽ ጦር ከተማይቱን ከተቆጣጠረ ደግሞ የሚደርሰዉ ሰብአዊ ጥፋት ሲበዛ ከባድ ነዉ።
«ባሁኑ ጊዜ ትልቁ ጭንቀት ዳርፉር ዋና ከተማ አል ፈሻር የሚደረገዉ ዉጊያ ነዉ።እዚያ የኃይል የበላይነቱ እየተለዋወጠ ነዉ።ፈጥኖ ደራሹ ጦር ከተማይቱን ከተቆጣጠረ ሊከሰት የሚችለዉ ከፍተኛ  የስደተኞች ማዕበል ያስፈረናል።ከተማይቱ ፈጠኖ ደራሹ ጦር እጅ ከወደቀች የምግባ ዋጋ በእጅጉ ያሻቅባል።ከዚሕ ቀደም ቡድኑ በተቆጣጠራቸዉ ከተሞች ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል።አል ፋሽር ዉስጥ ገንዘብ ያላቸዉ ጥቂት ጥቂት ሰዎች ከከተማይቱ መሸሽ ይችላሉ።ምንም የሌላቸዉ ግን ይገደላሉ።»

አንድ ጋዜጠኛ «የምድር ላይ ጀሐነብ»ያላት የአል ፋሸር ነዋሪዎችና ሠፋሪዎች ዕጣ ፈንታ ዛሬም አለየም።ማዕከላዊ ሱዳን አልጀዚራ ግዛት ባለፈዉ ሳምንት ባንድ ቀን ጥቃት ከ100 በላይ  ሰዎች ተገደሉ።ሮብ።የአካባቢዉ ነዋሪዎችና የመብት ተሟጋቾች እንዳሉት የፈጥኖ ደራሽ ጦር ዋድ አል-ኑር በተባለችዉ መንደርና አካባቢ ላይ በከፈተዉ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት 104 ሰዎች ተገድለዋል።
ለሰላማዊ ሰዎቹ መገደል የሱዳን መከላከያ ሠራዊትና የፈጥኖ ደራሹ ጦር አዛዦች እንደተለመደዉ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ያወግዛሉ።የመከላከያ ሠራዊቱ ጦር አዛዦች ፈጥኖ ደራሹ ጦር ሠላማዊ ሰዎችን ሆን ብሎ ፈጃቸዉ በማለት ጠላቶቹን ሲያወግዝ የፈጥኖ ደራሹ ጦር ባንፃሩ ጥቃቱን ያደረሰዉ በመከላከያ ሠራዊቱ ወታደሮችና በተባባሪዎቹ ሚሊሺያዎች ላይ ነዉ ብሏል።
የሱዳን ጉዳይ ተንታኝ ኢድሪስ አል በሽር ባለፈዉ ሐሙስ እንዳሉት ግን ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉት የፈጥኖ ደራሹ ተዋጊዎች መሆናቸዉ አያጠራጥርም።የጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ጦር ሰላማዊ ሰዎችን ከመግደል አልፎ የሟቾች ማንነት እንዳይታወቅ እስከሬናቸዉን በከባድ መሳሪያ አጋይቶታል ተብሏልም።
«ዛሬ ጠዋት የወጡ ዘገቦች የፈጥኖ ደራሹ ጦር የዋዳ ኑራ መንደርን ዳግም ማጥቃታቸዉን አረጋግጠዋል።በጥቃቱ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከሟቾቹ የ29ኙ ሰዎች ማንነት ተለይቷል።ፈጥኖ ደራሹ ጦር ባሁኑ ወቅት ወደ መንደሪቱ የሚገባና የሚወጣዉን የሚቆጣጠርበት ኬላ መሥርቷል።ከጥቃቱ ያመለጡ ሰዎች እንዳሉት ፈጥኖ ደራሹ ጦር የሟቾች ማንነት እንዳይታወቅ አስከሬናቸዉን በከባድ ጦር መሳሪያ ደብድቦታል።»

ባለፈዉ ሳምንት 100 በላይ ሰዎች የተገደሉትም በአል ጀዢራ ግዛት በምትገኝ አንድ መንድር ነዉ
አል ጀዚራ ግዛት ከሠፈሩ ሕጻናት ተፈናቃዮች በከፊል።መጠለያ፤ ትምሕርት፣ ንፅሕና በቂ ምግብም የለምምስል Ebrahim Hamid/AFP

የጄኔራሎቹ ምርጫ፣  ዓለም የዘነጋዉ ጦርነት

አስር ሺዎችን የፈጀና የሚፈጀዉን ጦርነት ብዙዎች የሁለቱ የቀድሞ ወዳጅ ጄኔራሎች የሥልጣን ጥማት ያስከተለዉ ይሉታል።ሌሎች የነባሩ የሱዳን ጦር ኃይልና የአዲሱ የሱዳን ልዩ ኃይል ፍጥጫ ዉጤት ያደርጉታል።የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች በሰሜናዊና ደቡባዊ ሱዳን ዜጎች መካከል የፈጠሩት የሐብት፣ የሥልጣንና ሥልጣኔ መበላለጥ ዉጤት ነዉ ባዮችም አሉ።
ምክንያቱ አንዱም ሆነ ሁሉም የተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ጦርነቱን ለማሸነፍ ድጋፍ ከማፈላለግ ዉጪ በድርድር ለመፍታት ፍላጎት ያላቸዉ አይመስልም።ወይም አልተማመኑም።

የሱዳን ወታደራዊ ገዢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ባለፈዉ ግንቦት መጀመሪያ ላይ «ወንጀለኛ» ካሉት ጠላታቸዉ ጋር እንደማይደራደሩ አስታዉቀዋል።በቅርቡ ጂዳ-ሳዑዲ አረቢያ ሊደረግ ታቅዶ የነበረዉ ቀጣይ ድርድርም የጄኔራል የአብዱል ፈታሕ ቡድን «አልካፈልም» በማለቱ ድርድሩ ሳይደረግ ቀርቷል።የፖለቲካ ተንታኝ ኢድሪስ አል በሽር እንደሚሉት የመከላከያዉ ሠራዊት ተወካዮች በድርድሩ አንካፈልም ያሉት ከዚሕ ቀደም በተደረጉ ድርድሮች መግባባት የተደረገባቸዉን ጉዳዮች ፈጥኖ ደራሹ ጦር በመጣሱ ነዉ።

«የፈጥኖ ደራሹ ጦርና የመከላከያ ሠራዊት ተወካዮች ጂዳ ዉስጥ ሊደረግ በታቀደዉ ሶስተኛ ዙር  ድርድር መካፈል ነበረባቸዉ።ይሁንና የመከላከያ ሠራዊቱ በጂዳዉ ድርድር እንደማይካፈል ያስታወቀ ይመስለኛል።በድርድሩ አንካፈልም ያሉበት ምክንያት ግልፅ ነዉ።ፈጥኖ ደራሹ ጦር ከዚሕ ቀደም በተደረጉ ድርድሮች ሰላማዊ ሰዎችና የመሰረተ ልማት አዉታሮች ጥቃት እንዳይደርስባቸዉ የተደረሰባቸዉን መግባባቶች ባለማክበሩ ነዉ።» 

ጊጋ በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የጀርመን ጥናት ተቋም ባልደረባ ሐገር ዓሊ እንደሉት ሱዳን የቀይ ባሕር በር በመሆንዋ ለአፍሪቃ\ ለተቀረዉ ዓለምም ጠቃሚ ናት።ይሁንና በተፋላሚ ኃይላት ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉት የአፍሪቃ፣ የዓረብ ከሁሉም በላይ ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራቸዉ  የምዕራብ መንግስታትም አሉ ለማለት ያክል ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠት አልፎ ሰላም ለማዉረድ ብዙም የፈለጉ አይመስልም።

 

ሁሉም የሚፈልጋት፣ ሁሉም ችላ ያላት ሐገር

የጂዳዉን ስምምነት በጣሱ ወይም አንደራደርም በሚሉ ኃይላት ላይ ሁነኛ ጫና ካልተደረገ የሱዳን ሕዝብ አበሳ እየከፋ፣ የጦርነቱ መዘዝም እየሰፋ፣የሩሲያና የምዕራባዉን ሽሚያም እየበረታ መሔዱ አይቀርም።ሐገር ዓሊ እንደሚሉት ሁሉም የሚሻትን ሐገር ጥፋት ሁሉም መዘንጋቱ ግራ አጋቢ ነዉ።
«ለሁሉም መንግስታት ሱዳን ወደ አፍሪቃ የሚያስገባና  የሚያስወጣዉ የቀይ ባሕር በር ናት።ሩሲያ በተለይ አሁን ኒዠርን ለመቆጣጠር እየጣረች ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ባንፃሩ ከኒዠር እየወጣች ነዉ።ከሰዎች ዝዉዉር እስከ ንግድ ያሉ የአካባቢዉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር የተያያዙ ናቸዉ።የሱዳን የመንግስት (መዋቅር) ከፈረሰ ሕጋዊና ይፋዊ መስመሮች በሙሉ ይዘጋሉ።ሥለዚሕ ጦር ሠፈር ለመመስረትም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ብዙ መጠበቅ አያስፈልግም።ሁሉም ነገር ጦር መሳሪያ በማቀበል በጣም በፍጥነት እየሆነ ነዉ።--ይሕ ግራ አጋቢ ሁኔታ መፍጠሩ አይቅርም።»

የሱዳን መከላከያ ሠራዊትም ሆነ የፈጥኖ ደራሹ ጦር አዛዦች በድርድሩ መሠመር ብዙም መፍትሔ ይመጣል ብለዉ የሚያስቡ አይመስልም።ሁለቱም ኃይሎች በጦርነቱ የበላይነት ለማግኘት ጦር መሳሪያ ከሚረዳቸዉ ከየትኛዉም መንግስት ወይም ኃይል ጋር ለመተባበር፣ብዙዎች እንዳሉት፣ ዝግጁ ናቸዉ።በዩክሬን ሰበብ ተዘዋዋሪ ጦርነት የገጠሙት የሩሲያና የምዕራባዉያን መንግሥታትም የየራሳቸዉን ተፅዕኖ ለማሳረፍ መሻኮታቸዉ አልቀረም።

አሁንም አል ፋሸር የተባለችዉን ከተማ ለመያዝና ላለማስያዝ የሚደረገዉ ዉጊያ ሰሞኑንም እንደቀጠለ ነዉ
የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ዳርፉር ዉስጥ በሚያደርሱት ጥቃት ከወደሙ የምግብ መሸጪያና ማከማቻ መጋዘኖች አንዱምስል AFP

ባለፈዉ መስከረም የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዣዥ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን የዩክሬኑን ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዜለንስኪን ካነጋገሩ ወዲሕ አል ቡርሐን የምዕራባዉያኑ ድጋፍ እንደማይለያቸዉ ተስፋ ያደረጉ መስለዉ ነበር።ይሁንና ባሰቡት ልክ የሚሹትን ድጋፍ ያገኙ አይመስልም።

የዚያኑ ያክል ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ የቡርሐን-ዜሌንስኪ ግንኙነት የፈጠረላቸዉን አጋጣሚ ከሩሲያ ጦር መሳሪያ ለማግኘት አይጠቀሙበትም ማለት በርግጥ ጅልነት ነዉ።የሱዳን ጉዳይ አጥኚ ኢድሪስ አል በሽር «የተረሳ» ከማለት ይልቅ «የተዘነጋ» ማለትን የሚመርጡት የሱዳን ጦርነት እንደተዘነጋ ከቀጠለ ለድፍን ዓለም ጊዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ መዘዝ፣ የስደተኞች ማዕበልና ትርምስ ማስከተሉ አይቀርም-እንደ ኢድሪስ አልበሽር እምነት።


ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ