መጽሐፍትን በተንቀሳቃሽ ስልክ   | ወጣቶች | DW | 15.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ወጣቶች

መጽሐፍትን በተንቀሳቃሽ ስልክ  

በስልክ ወይም በተመሳሳይ የኮምፒውተር መገልገያዎች ለንባብ የቀረቡ መፅሀፍት ኢትዮጵያ ውስጥ መሸጥ እስካሁን ብዙም የተለመደ አይደለም። ለዚህም ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። በአንድ በኩል ይህንን አገልግሎት የሚሰጥ አፕሊኬሽን አለመኖሩ ሲሆን በሌላ ወገን ደግሞ ክፍያው በኦንላይን መፈፀም ስላለበት ነው። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:02
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:02 ደቂቃ

ሎሚ ቡክስ

ኢ-ቡክ ወይም በወረቀት ላይ ታትሞ ሳይሆን በኤሌክትሮኒክስ መገልጋዮች አማካኝነት ሊነበብ የሚቻለው መፅሀፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በምዕራቡ ዓለም ገበያ ላይ የዋለው እኢአ በ1988 ዓም ነበር። ቴክኖሎጂውም እያደገ ሲሄድ ሰዎች መፅሀፉን በCD ይገዙና እና ያነቡ ጀመር። ዛሬ እነዚህ መጽሀፎች በአፕሊኬሽን መልክ ይሸጣሉ። የኢትዮጵያ መጽሀፎችን ለገበያ ያቀረበው ሎሚ ቡክስ ወይም ሎሚ መፅሀፍት ከነዚህ አንዱ ነው። «ሰዎች በቀላሉ ስልካቸውን ተጠቅመው መፅሀፍ ማንበብ እንዲችሉ ነው»ይላል የሎሚ መፅሀፍት መስራች ብሩክ ኃይሉ። ሎሚ ቡክስን ኢንተርኔት ላይ በ PDF መልክ ከሚገኙት የኢትዮጵያ መጽሀፍት የሚለየው አንዱ ነገር ደራሲያኑ ፍቃደኝነታቸውን ተጠይቀው እና ውል ተፈራርመው ነው መፅሀፋቸው ለአንባቢያን የሚቀርቡት። 

Lomi Books (DW/B. Hailu)

የሎሚ ቡክስ መስራች እና ባልደረቦች


ኢትዮጵያ ለሚገኙት ሸማቾች ወይም ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚገኙት ዲያስፖራዎች አከፋፈሉ እንዴት አስተማማኝ እና ቀላል እንደሆነ ብሩክ ያስረዳል።  ለጊዜው ግን የዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑት የአንድሮይድ ተገልጋዮች ብቻ ናቸው። የኢ- ቡክ ወይም በዲጂታል መልክ የሚቀርብ መፅሀፍ ከሚታተመው መፅሀፍ ጋር ሲነፃፀር ዋጋው መለስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አማራጮችንም ይሰጣል። እነዚህ አማራጮችም በሎሚ መፅሀፍት ላይ ተግባራዊ ሆኗል። አንባቢያን የማይችሉት ነገር ቢኖር፤ አንዴ የገዙትን መፅፋት ለሌላ ሰው መላክ ወይም ማጋራት ነው። አንድ ገበያተኛ የሎሚ ቡክስ አፕሊኬሽንን በቅድሚያ ስልኩ ወይም ሌሎች መገልገያዎቹ ላይ ለመጫን የጉግል «ፕሌይስቶር» ውስጥ ገብቶ ሲፈልግ በሎሚ ቡክስ ስር የተለያዩ መፅሀፎችን ዝርዝር ይመለከታል። ሎሚ ቡክስ በአሁኑ ሰዓት ከ 50-60 መፅሀፎች ለገበያ እንዳቀረበ ይናገራል። ከሁሉም ደራሲያንም ጋር ተረራርመናል ይላል ብሩክ። ከዚህም ሌላ ደራሲያኑ ምን ያህል መጽሀፋቸው እንደተሸጠ ራሳቸው ገብተው የሚቆጣጠሩበት መንገድ እንደተዘጋጀላቸው የሎሚ ቡክስ መስራች ይናገራል። አንባብያኑም ከዚህ ቀደም በቀላሉ የማያገኙትን አገልግሎት ይዘን ብቅ ስላልን ጥሩ አስተያየት እየሰጡን ነው ይላል ብሩክ። 

Lomi Books (Lomibooks)

ሎሚ ቡክስ በአሁኑ ሰዓት ከ 50-60 መፅሀፎች ለገበያ አቅርቧል።


ደራሲ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፋ መንገደኛ የሚለው መፅሀፉን በሎሚ መፅሀፍት አማካኝነት በኦንላይን  ከሚሸጡ ደራስያን አንዱ ነው። ደራሲው መፅሀፎቹን በአፕሊኬሽን መልክ የመሸጡ ጥያቄ ሲቀርብለት በደስታ ነው የተቀበለው። ይህም ደራሲው ራሱ የኢ-ቡክ ተጠቃሚ በመሆኑ ነው። ደራሲ እና አንባቢ ዮርዳኖስ በወረቀት ላይ ታትሞ የሚቀርበውን መጽሀፍ ቢመርጥም ኢትዮጵያ ውስጥ የንባብ ፍላጎትን ለማዳበር ኢ-ቡክ ጥሩ አማራጭ ነው ብሎ ያምናል። ደራሲ አለማየሁ ገላጋይም ቢሆን ሎሚ መጽሀፍት ሶስት መፅሀፎቹን ኦንላይን ላይ እንዲሸጥ ፈቅዷል። ፍቃድ ጠይቀውት መፅሀፉ በኦንላይን ሲሸጥ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው። « ከዚህ በፊት ግን ያለ ፍቃድ ስኬን  እያደረጉ መፅሀፎቼን በኦንላይን አሰራጭተዋል» ይላል። ማን እንዳደረገው እንኳን አለማየሁ አያውቅም።
በስልክ እና ሌሎች የኮምፒውተር መገልገያዎች ላይ ለንባብ የቀረቡ የኢትዮጵያ መፅሀፎችን ለኦንላይን ገበያ ያቀረበው ሎሚ ቡክስ ወይም ሎሚ መፅሀፍትን አጠቃቀም እና ምንነትን የቃኘንበትን የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በድምፅም ማግኘት ይችላሉ።

ልደት አበበ
አርያም ተክሌ
 

Audios and videos on the topic