1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መጋቢት ወር የአንጀት ካንሰር ሲታሰብ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 17 2016

በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን አቆጣጠር ማርች ማለትም መጋቢት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለአንጀት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት ወር ነው። የአንጀት ካንሰር በመላው ዓለም በካንሰር ምክንያት ከሚከሰተው ሞት በሁለተኛ ደረጃ እንደሚገኝ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

https://p.dw.com/p/4e9Lt
ለካንሰር እንጓዝ በናዝሬት አዳማ
የካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫው ጉዞ በአዳማ (ናዝሬት) ከተማ እሑድ መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ተካሂዷል። ምስል DW

መጋቢት ወር የአንጀት ካንሰር ሲታሰብ

 

በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓ,ም በመላው ዓለም ከ1,9 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለአንጀት ካንሰር መጋለጣቸውን የዓለም የጤና ድርጅት አመልክቷል። ከእነዚህ መካከል ከ930 ሺህ በላይ የሚሆኑት በዚሁ መዘዝ ሕይወታቸው አልፏል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ያሳስብ የነበረው የአንጀት ካንሰር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወጣቶች ላይም እየተከሰተ ነው።

በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን አቆጣጠር ማርች ማለትም መጋቢት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለአንጀት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት ወር ነው። የአንጀት ካንሰር በመላው ዓለም በካንሰር ምክንያት ከሚከሰተው ሞት በሁለተኛ ደረጃ እንደሚገኝ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። የዘርፉ ሀኪሞች ሰዎች የካንሰር ምልክቶችን አስቀድመው በመረዳት ስር ከመስደዱ አስቀድሞ ወደ ህክምና እንዲሄዱና አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርጉ ይመክራሉ።

የአንጀት ካንሰር ምልክቶች

በህክምናው ኮሎሬክታል ካንሰር በመባል የሚታወቀው የአንጀት ካንሰር በተለይ በትልቁ የአንጀት ክፍል ላይ የሚከሰት የጤና ችግር መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ይገልጻል። በተለይም ዕድሜ በገፋ መጠን ለዚህ የጤና ችግር የመጋለጥ እድሉም ከፍ እንደሚል የጠቆመው የድርጅቱ ማብራሪያ በአብዛኛው በሽታው ሲጀምር ምልክቶች ስለማያሳይ ሰዎች አስቀድመው የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ይመክራል።

የአንጀት ካንሰር ህመም ምልክቶች ማስቀመጥ፤ ድርቀት፤ ደም የተቀላቀለበት አይነምድር፤ በታችኛው የሆድ ክፍል ህመም፤ ድንገት ክብደት መቀነስ፤ የድካም ስሜት እንዲሁም በሰውነት የብረት ማዕድን መጠን መቀነስ መሆናቸውንም ገልጿል።

ዶክተር ቢንያም ተፈራ የካንሰር ከፍተኛ ሀኪም
ስለካንሳር ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው የገለጹት የካንሰር ከፍተኛ የህክምና ባለሙያው ዶክተር ቢንያም ተፈራ፤ እስካሁን በተደረጉት ጥረቶች የማሕጸን እና የጡን ካንሰር ምርመራ ለማድረግ ወደ ሀኪም ቤት የሚሄዱ ሴቶች ቁጥር መጨመሩን ይናገራሉ። ምስል DW

ስለካንሰር የማሳወቂያ መርሃግብሮች

የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። ኢትዮጵያ ውስጥም ካንሰር የብዙዎችን ቤት እያንኳኳ መሆኑ ነው የሚነገረው። እንዲያም ሆኖ ዛሬም ብዙዎች ወደ ሀኪም ቤት የሚሄዱት ዘግይተውና ህመሙ ስር ከሰደደ በኋላ በመሆኑ በህክምና አዎንታዊ ውጤት ለማግኘት እንቅፋት እንደሆነ የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜ ይናገራሉ።

ሰዎች ስለካንሰር ህመም በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በየጊዜው የተለያዩ መርሃግብሮች ይዘጋጃሉ። እንዲህ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች ታዲያ ሰዎች የጤና ችግሩን ገና እንደጀመረ እንዲያውቁት፤ ምልክቶቹንም እንዲገነዘቡ፤ በዚህ መነሻነትም በፍጥነት የህክምና እርዳታ እንዲፈልጉ ለማድረግ ያለሙ ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ታዲያ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አዳማ/ናዝሬት/ ላይ ካንሰር ላይ ያተኮረ የእግር ጉዞ ተዘጋጅቶ በርካቶች ተሳትፈውበታል። በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት የካንሰር ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር ቢንያም ተፈራ የግንዛቤ ማስጨበጫው የእግር ጉዞ ሁለት ዓላማ እንደነበረው ነግረውናል።

የአንጀት ካንሰር
የአንጀት ካንሰር ህመም ምልክቶች ማስቀመጥ፤ ድርቀት፤ ደም የተቀላቀለበት አይነምድር መኖር፤ በታችኛው የሆድ ክፍል ህመም፤ መንስኤው ያልታወቀ ክብደት መቀነስ፤ ድካም እንዲሁም በሰውነት የብረት ማዕድን መጠን መቀነስ መሆናቸውን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ምስል Fotolia/Sebastian Kaulitzki

ስለካንሰር ግንዛቤ ለመፍጠር የሚከናወኑት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ወቅትን የጠበቁ ሆነው ነው የሚታዩት። ጥቅምት ላይ ስለጡት ካንሰር ይወራል፤ መጋቢት ደግሞ ስለአንጀት ካንሰር። ለመሆኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ ለውጥ አምጥቶ ይሆን? ያልናቸው  ዶክተር ቢንያም፤ ምንም እንኳን እንዲህ ያሉት እንቅስቃሴዎች ወቅትን ጠብቀው ቢደረጉም ጅምሩ መኖሩ በራሱ መልካም እንደሆነ ይናገራሉ። ሰዎች እስካሉ ድረስ ካንሰር እንደሚኖር ያመለከቱት ዶክተር ቢንያም፤ በሰጡት ማብራሪያ ውጤቱን በተመለከተ ግን ብዙ እንደሚቀር እና የበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅ አንስተዋል። እንዲያም ሆኖ ግን በተለይ የማሕጸን እና የጡት ካንሰርን ለመመርመር የሚመጡ ሴቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የካንሰር ከፍተኛ የህክምና ባለሙያው አያይዘውም ኢትዮጵያ ውስጥ የካንሰር ህመም አይነትና የታማሚዎችን ብዛት በአግባቡ መዝግቦ መያዝ በሽታውን ለመከላከል ብሎም ትክክለኛ ፖሊሲ ለመቅረጽ እንደሚረዳ ነው የተናገሩት። ምዝገባው በየትኛው አካባቢ የትኛው የካንሰር አይነት ይበዛል የሚለውን ለመረዳት እንደሚያስችል፤ በሁሉም አካባቢዎችም ትኩረት ተሰጥቶት በትክክል ሊመዘገብ እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም ገልጸውልናል።

ፎቶ፤ በአዳማ የተካሄደው ለካንሰር እንጓዝ መርሃግብር
ካንሰር የብዙዎችን ቤት እያንኳኳ መሆኑ ቢነገርም፤ ኢትዮጵያ ውስጥም ዛሬም ብዙዎች ወደ ሀኪም ቤት የሚሄዱት ዘግይተውና ህመሙ ስር ከሰደደ በኋላ እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ፎቶ፤ በአዳማ የተካሄደው ለካንሰር እንጓዝ መርሃግብር ምስል DW

የመጋቢት ወር የአንጀት ካንሰር    

በዓለም አቀፍ ደረጃ የያዝነው መጋቢት ወር ስለአንጀት ካንሰር ይታሰባል፤ የተለያዩ መረጃዎችና የጥንቃቄ መልእክቶችም ይተላለፋሉ። ቀደም ሲል በበለጸጉት ሃገራት ብቻ እንደሚከሰት ይታሰብ የነበረው ካንሰር በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ በማደግ ላይ ባሉ ሃገራትም በብዛት መገኘቱ ትኩረትን እየሳበ ነው። ዶክተር ቢንያም እንደሚሉትም ምንም እንኳን የታማሚዎች ብዛት በበለጸጉት ሃገራት ቁጥራቸው ከፍ ቢልም በካንሰርምክንያት የሚሞቱት የሚበዙት በድሀና አዳጊ ሃገራት ነው። ለዚህም ለበሽታው የሚሰጠው ትኩረት እና ክትትል፤ እንዲሁም የህክምናው መስፋፋትና በስፋት መገኘት ዋነኛ የልዩነት ምክንያት መሆኑንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥም የአንጀት ካንሰር በብዛት እንደሚገኝና እጅግ አሳሳቢ እንደሆነም ነው ያመለከቱት።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ 30 በመቶ የሚሆነውን ለካንሰር የሚያጋልጥ ዋነኛ መንስኤ የአኗኗር ስልትልን በመለወጥ እንዲሁም ለዚያ የሚያጋልጡ ምክንያቶችን በማስወገድ መከላከል ይቻላል። የዓለም የጤና ድርጅት ጤናማ አመጋገብን በመከተል፤ የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ፤ ከዚህም ሌላ ትንባሆ ማጨስም ሆነ የአልክሆል መጠጦችን በማስወገድ ለአንጀት ካንሰር የመጋለጥ ሁኔታን ለመቀነስ እንደሚቻል ይመክራል። ከዚህም ሌላ አስቀድሞ የሚደረግ ምርመራ ችግሩ ከመባባሱ በፊት ለመድረስ እንደሚረዳ የዘርፉ ሀኪሞች በየጊዜው ያሳስባሉ። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ የካንሰር ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑትን የዘወትር ተባባሪያችንን ዶክተር ቢንያም ተፈራን ከልብ እናመሰግናለን።

 ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ