1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት የተገበረዉን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መልሶ እንዲያጤነው ተጠየቀ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 21 2016

መንግሥት ተግባራዊ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ እንደገና እንዲያጤነው እናት ፓርቲ ጠየቀ። ፓርቲው የሚፈራ ያለው ማኅበራዊ ቀውስ "ሊታከም ከማይችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት" መንግሥት ጉዳዩን መልሶ እንዲያየው ጠይቋል። የማሻሻያውን ትግበራ ተከትሎ አለአግባብ "ሱቅ ማሸግ እና እጅ መንሻ መቀበል" መስተዋሉን ፓርቲው ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4jy9J
እናት ፓርቲ
እናት ፓርቲ ምስል Enat Party

መንግሥት እየተገበረ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መልሶ እንዲያጤነው ተጠየቀ

መንግሥት እየተገበረ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መልሶ እንዲያጤነው ተጠየቀ 

መንግሥት ተግባራዊ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ እንደገና እንዲያጤነው እናት ፓርቲ ጠየቀ። ፓርቲው የሚፈራ ያለው ማኅበራዊ ቀውስ "ሊታከም ከማይችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት" መንግሥት ጉዳዩን መልሶ እንዲያየው ጠይቋል። ለመንግሥት ሠራተኞች "የደሞዝ ጭማሪ በአስቸኳይ እንዲደረግ" የጠየቀው ፓርቲው፣ የማሻሻያውን ትግበራ ተከትሎ አለአግባብ "ሱቅ ማሸግ እና እጅ መንሻ መቀበል" በተለይም አዲስ አበባ መርካቶ ገበያ ውስጥ በአሳሳቢ ሁኔታ መስተዋሉን ገልጿል።

የመንግሥትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ እርምጃ ኢሕአፓ፣ ባልደራስ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ኮከስ ከዚህ ቀደም ብለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሊያስከትል ይችላል በሚል ተቃውመውታል።  

የፓርቲው የመግለጫው መነሻዎች ምንድን ናቸው?

እናት ፓርቲ በመግለጫው እንዳለው መንግሥት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በብድር ያገኘውን የብድር ገንዘብ ተከትሎ የወሰደው ጉልህ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሻሻያ በሀገሪቱ የሚፈራ ማኅበራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ይጠቅሳል። 

መንግሥት "በግል ዘርፉና ማኅበረሰቡ ላይ" እንቅፋቶችን መጫኑን የሚጠቅሰው ይሄው የፖለቲካ ድርጅት ይህንኑ እየመረመረ "በአስቸኳይ እንዲያነሳ"ይጠይቃል። አቶ ዳዊት ብርሃኑ የእናት ፓርቲ ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ አባል እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው። 

"መንግሥት አኹን ላይ እየተገበረ የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ከወዲሁ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና ኅብረተሰብ ላይ የተለያዩ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ማሳደር ጀምሯል። በገበያው እየተዛመተ የሚገኘው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ለማኅበረሰባችን ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል።" 

 

የምርት ግብዓቶች ከመንግሥት ዕጅ እንዲወጡ መጠየቁ 

የምርት ግብዓት የሚባሉት ሐብቶች "ከካድሬ እጅ" ይውጡ የሚለው እናት ፓርቲ፣ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ "በባለሙያዎች እንዲመራ በማድረግ ግልጽ የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ እንዲቀመጥ" ፣ለመንግሥት ሠራተኛውም የደሞዝ ጭማሪ በአስቸኳይ እንዲያደርግጠይቋል።

"መንግሥት ራሱ ፈቅዶና ፈርሞ ያመጣው ፖሊሲ የፈጠረውን ምስቅልቅል በነጋዴው ማኅበረሰብ ላይ እያመካኙ ሱቅ ማሸግና እጅ መንሻ መቀበል ሥራዬ ብለው የያዙትን ባለስልጣኖቹን አደብ እንዲያስገዛ እናሳስባለን፡፡" የመንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ እርምጃን ኢሕአፓ፣ ባልደራስ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ኮከስ የፖለቲካ አለመረጋጋት ሊያስከትል ይችላል በሚል ቀደም ብለው ተቃውመውታል።

መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ ክትትሎች እና እርምጃዎች

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የማሻሻያ እርምጃውን ተከትሎ ምርት በመደበቅ፣ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የተጠረጠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ተቋማትን አሽጓል፣ ሌሎች እርምጃዎችንም ወስዶባቸዋል። ሚኒስቴሩ የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል እና የበዓል የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት የሚውል 50 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ከጅቡቲ ወደ የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተጓጓዘ መሆኑን አስታውቋል።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ