1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መተማ የሠፈሩ የሱዳን ስደተኞች ወደ መጠለያ አንገባም አሉ

ረቡዕ፣ ግንቦት 14 2016

ከመጠለያ ጣቢያው በወጡት ስደተኞች ቁጥር ላይ ስደተኞችና ባለስልጣናት የተራራቀ መረጃ አላቸው። ስደተኞቹ ከ4ሺህ እስከ 5ሺህ ሰዎች እንደወጡ ሲገልፁ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በበኩሉ አሁን ከመጠለያው ውጪ ያሉት ከ 6 መቶ አይበልጡም ብሏል።

https://p.dw.com/p/4g6t9
አማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ድንበራማ አካባቢ
ኢትዮጵያና ሱዳንን ከሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎች አንዱ የሆነዉ የመተማ አካባቢምስል DW/Alemenew Mekonnen

መተማ የሠፈሩ የሱዳን ስደተኞች ወደ መጠለያ አንገባም አሉ


 ባለፈው ሳምንት ምዕራብ ጎንደር መተማ አካባቢ ከሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች የወጡ የሱዳን ስደተኖች  አሁንም ወደየመጠለያ ጣቢያቸዉ እንዳልተመለሱ አስታወቁ። ስደተኞቹ የንፁህ መጠጥ ውሀ፣ የምግብና መጠለያ ችግር እንዳጋጠማቸው አመልክተዋል። የአካባቢው ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በበኩሉ ስደተኞች ወደ መጠለያ እንዲመለሱ የማይፈልጉ አካላት ግፊት አለበት ይላል። ከመጠለያ ጣቢያው በወጡት ስደተኞች ቁጥር ላይ ስደተኞችና ባለስልጣናት የተራራቀ መረጃ አላቸው። ስደተኞቹ ከ4ሺህ እስከ 5ሺህ ሰዎች እንደወጡ ሲገልፁ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በበኩሉ አሁን ከመጠለያው ውጪ ያሉት ከ 6 መቶ አይበልጡም ብሏል።

መጠለያውን ጥለው ከወጡ ስደተኞች መካከል አንዱ፣“ግንቦት መጀመሪያ ከስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ወጥተናል፣ ምክንታችን ደግሞ የመጠጥ ውሀ አለመኖር፣  በቂ የምግብ አቅርቦት ችግርና የፀጥታ ሁኔታው አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፣ ያለንበት መጠለያ ጣቢያም ጭቃማና ጎርፍ የሚያጠቃው በመሆኑ ይህ እንዲቀየር ብንጠይቅም ትባራዊ ባለመሆኑ ነው” ብላል፡፡
 “ከመመጠለያ ጣቢያው ከወጣን በኋላ ንፅህናው ያልተጠበቀ የወንዝና የኩሬ ውሀ እየጠጣን ነው፣ ቀድሞ እንኖርበት ከነበረው የመጠለያ ጣቢያም ከወጣን ጀምሮ ውሀ እንዳንቀዳ ተከልክለናል፡፡” ሲል ይኸው ስደተኛ አመልክቷል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው ከመጠለያ ጣቢያ የወጡ ስደተኞች ቁጥር ወደ 6ሺህ ይደርሳል፡፡

በአውላላ መጠለያ ጣቢያ ከመጠለያው ያልወጣ ስደተኛ በበኩሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ስደተኞቹ ወደ መጠለየቸው እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያደርግም ሰዎቹ ሊመለሱ አልቻሉም ነው ያለው፡፡ በመጠለያው የነበሩ ድንኳኖችም በዝናብና በነፋስ እየተወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፣ ይህ አስተያየት ሰጪም ከመጠለያ ጣቢያው የወጡት ስደተኞች ከ4ሺህ እስከ 5ሺህ ሊደርሱ ይችላሉ ብሏል፡፡

ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር ከሚያዋስኑ አካባቢዎች አንዱ የሆነዉ መተማ
ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር ከሚያዋስኑ አካባቢዎች አንዱ የሆነዉ መተማምስል Alemenew Mekonnen/DW

የኩመር፣ የአውላላና አለምዋጪ ስደተኞችና ተመላሾች አስተባባሪ አቶ ታምራት ደምሴ ጉዳዩን አስመልክተው ለዶይቼ ቬሌ  በሰጡት መግለጫ የፀጥታው ሁኔታ ተሸሽሏል ተመለሱ ቢባሉም ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም ነው ያሉት፣ እንደ አቶ ታምራት አሁን ከመጠለያ ውጪ ያሉት ከ5መቶና 6 መቶ አይበልጡም፡፡፡፡
ስደተኞቹ ለመመለስ ለምን ፈቃደኛ አልሆኑም? አቶ ታምራት ያብራራሉ፣
“... የማይፈልጉበት ምክንያት በአንድም በሌላ መልኩ ልትጠራጠረው የምትችለው ነገር አለ፣ ሰው የፀጥታ ችግር አለብኝ ካለ “ፀጥታህን አስጠብቅልሀለሁ” ካልከው አልመለስም የሚል ከሆነ የፀጥታ ብቻ አይደለም ችግሩ ማለት ነው፣ አሁን ከመጠለያ የወጡት ቁጥራቸው ወደ 5 እና 6 መቶ ደርሷል፣ እነኚህን ሰዎች መጠቀሚያ የሚያደርግ ከጀርባ ያለ የሆነ አካል ሊኖር ይችላል፣ እሱን ክትትል እናደርጋለን ስደተኛው እንዲረበሽ፣ “አገሪቱ ስደተኛ መቀበል የምትችልበት ቁመና ላይ አይደለችም” ለማስባል ስደተኞችንም ወደ ሌላ ሶስተኛ እንዲሄዱ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ የሚሰሩት ስራ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
 አቶ ታምራት፣ እንደችግር የሚነሱ ጉዳዮች ካሉም በሁሉም የመጠለያ ጣቢያዎች የሚታዩ እንጂ በአውላላና በኩመር ብቻ የሚታዩ ባለመሆናቸው ስደተኞች ወደ መጠለያቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡
ተጨማሪ እስተያየት ለማካተት በኢትዮጵያ ለተበባሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) የህዝብ ግንኙነት ክፍል ከትናንት ጠዋት 4 ሰዓት ጀምሮ በኢሜይል ያደረግሁት ተደጋጋሚ ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ አልተሳካም፡፡
ይሁን እንጂ ድርጅቱ ከዚህ በፊት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ከኩመርና አውላላ የስደተኞች ጣቢዎች 1ሺህ 300 ስደተኞች በፀጥታና በሌሎች ምክንቶች ወትተዋል፣ ችግሩን ለመፍታትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያይናችግሮች እንዲፈቱ ይደረጋልም ብሎ ነበር፡፡

ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ