1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከምዕራብ ጉጂ ወደ ኮሬ ዞን መሸሻቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ

ቅዳሜ፣ የካቲት 30 2016

በኦሮሚያ ክልል ከምዕራብ ጉጂ ዞን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች፣ የቀበሌ አመራሮች እና ሚሊሺያዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወደሚገኘው ኮሬ ዞን መሸሻቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ። ሰዎቹ የሸሹት ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላት በገላና ወረዳ የምትገኘውን መጠሪ ቀበሌ ከተቆጣጠሩ በኋላ ነው።

https://p.dw.com/p/4dKxO
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የሚገኝ ቦታ
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላት በገላና ወረዳ መጠሪ ቀበሌ መንደሮች ከተቆጣጠሩ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች፣ የቀበሌ አመራሮች እና ሚሊሺያዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወደሚገኘው ኮሬ ዞን መሸሻቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከምዕራብ ጉጂ ወደ ኮሬ ዞን መሸሻቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ

የግብርና ባለሙያው ሀሰን ጉዮ እና የቀበሌ ሚሊሺያ ታጣቂው ገልገሎ ቃጦ እስካለፈው ሰኞ በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ መጠሪ ቀበሌ በሥራቸው ላይ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ከሰኞ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ብዛት አላቸው ያሏቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት  ወደ ቀበሌው በመግባት መንደሮችንና አገናኝ ጎዳናዎችን  መቆጣጠራቸውን  ሀሰንና ገልገሎ ገልጸዋል፡፡

የቀበሌውን በታጣቂዎቹ መያዝ ተከትሎ እነሱን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ፣ የቀበሌ አመራሮች እና  ሚሊሺያዎች በሥጋት ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን  መሸሻቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን የኪሌ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር አበበ ጣሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ከአጎራባች የገላና ወረዳ ወደ ኬሌ ከተማ መግባታቸውን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡

ጉጂ ዞን 12 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

“ ነዋሪዎችና አመራሮቹ ታጣቂዎቹ ጉዳት ሊያደርሱብን ይችላሉ በሚል ሥጋት ወደ ኬሌ ከተማ ተፈናቅለው በእኛ ዘንድ ይገኛሉ “ ያሉት  አዛዡ ማህበረሰቡን አሥፈላጊውን የምግብና ሌሎች ድጋፎች  እያደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡ 

የቀበሌያቱ መያዝና የመንገዶች መዘጋት

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ውስጥ ከሚገኙት ቀበሌያት አብዛኞቹ ራሱን “ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “ ብሎ በሚጠራው አማጺ ቡድን ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ፡፡

በጎሮዶላ ወረዳ የትምህርትና ጤና አገልግሎት ተቋርጧል

ታጣቂዎቹ የገላና ወረዳ መስተዳድር መቀመጫ ከሆነችው ቶሬ በስተቀር አብዛኞቹን ቀበሌያት ይዘው እንደሚገኙ የሚናገሩት የመጠሪ ቀበሌ ተፈናቃዮቹ ሀሰን ጉዮ እና ገልገሎ  ቃጦ “ አሁን ላይ ከኬሌ ወደ ዲላ ፤ ቶሬ ፣ ይርጋጨፌ እና ሀዋሳ የመሳሰሉ ከተሞችን የሚያገኛኙ መንገዶችም ተዘግተው ይገኛሉ ፡፡ ምክንያቱም ወደእነዚህ ከተሞች የሚወስዱ መንገዶች በሸኔ ተይዘው የሚገኙ ቀበሌያትን አቋርጠው የሚልፉ ናቸው “ ብለዋል ፡፡

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር የምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት
የምዕራብ ጉጂ ዞን ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ግጭቶች እና የታጣቂዎች ጥቃት ከተከሰተባቸው የኦሮሚያ ክልል ዞኖች አንዱ ነው። ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

እራሱን “ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “ ብሎ የሚጠራው አማጺ ቡድን ግን በተፈናቃዮችም ሆነ በእጁ ይገኛሉ በተባሉት ቀበሌያት ዙሪያ እስከአሁን ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጠም ፡፡

የሃላፊዎቹ ዝምታና የምክር  ቤት አባሉ ጥሪ

ዶቼ ቬለ የገላና ወረዳ እና የምዕራብ ጉጂ ዞን የሰላምና የጸጥታ የሥራ ሃላፊዎች ለማነጋገር ጥረት ቢያደረግም አንዳንዶቹ ስብሰባ ላይ ሌሎች ደግሞ ጉዞ ላይ መሆናቸውን በመግለጻቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡ የኮሬ ህዝብን በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር አወቀ ሀምዛዬ በገላና ሸለቆ ቆላማ ቀበሌያት የሚታየው የፀጥታ ችግር የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሥጋቱ እየጨመረ ፤ ወጥረቱም እየተባባሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የጉጂው ውዝግብና የተወካዮችና የባለስልጣናት ውይይት

በተለይም ባለፉት አራት ቀናት የኮሬን ዞን በሚያዋስኑ የምዕራብ ጉጂ ዞን ቀበሌያት “ ሸኔ” የተባለው ታጣቂ ቡድን እንቅስቃሴ ማድረጉን የጠቀሱት የምክር ቤት አባሉ “ ታጣቂ ቡድኑ በሚዘዋወሩባቸው የሁለቱ አዋሳኝ ዞኖች ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ሥጋት ውስጥ ወድቀዋል ፡፡ ከዚህ በፊት ሥንገልጽ እንደነበረው አሁንም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት እንዲያስጠብቅ አንጠይቃለን “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ