1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈጥሮ ጥበቃ በሐረማያ ሐይቅ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 10 2016

ያ የጀልባዎች መንሳፈፊያ የነበረው ሐይቅ የጭነት መኪኖች የሚያቋርጡበት፤ ያ አሶች የሚርመሰመሱበት ሐይቅ የተራረፉ ሳሮችን የሚቃርሙ ከብትና ፍየሎች የሚሰማሩበት፤ ያ ሰማያዊ ቀለም ይዞ የአካባቢውን ውበት አድማቂ የነበረ ሐይቅ በደለል ተሞልቶ ወደ ነበር ተቀየረ፤ ለምን ?

https://p.dw.com/p/4drSa
የሐረማያ ሐይቅ
የሐረማያ ሐይቅምስል Mesay Teklu/DW

የተፈጥሮ ጥበቃ በሐረማያ ሐይቅ


ወደ ነበር ለምን ተቀየረ?

የያኔው ህጻን ይስሃቅ ዩሱፍ ከተወለደባት የሐረር ከተማ ከወላጅ አባቱ ጋር በየጊዜው ወደ ሐረማያ ሐይቅ በመጓዝ በጀልባ ሲያደርገው የነበረው ሽርሽር አሁንም ድረስ አይኑ ላይ ውልብ እንደሚልበት ያጫወተን። ለሀረር፣ ሐረማያና አወዳይ የመሳሰሉ ከተሞችን ጨምሮ ለአካባቢው ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ ምንጭ፣ ለመስኖ ስራ የሚጠቀሙበት፣ የዓሳ ማስገሪያ በመሆን ረሃባቸውን የሚያስታግሱበት፤ ብቻ ሀረማያ ሐይቅ ለአካባቢው ነዋሪዎች ትርጉሙ ብዙ ነው።
ይህ ለአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ጠቀሜታ የነበረው የሐረማያ ሀይቅ የውሃ መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአስደንጋጭ ፍጥነት እየቀነሰ በመሄድ እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2011 ሙሉ በሙሉ ደረቀ። ያ የጀልባዎች መዋያ የነበረው ሐይቅ የጭነት መኪኖች የሚያቋርጡበት፤ ያ አሶች የሚርመሰመሱበት ሐይቅ የተራረፉ ሳሮችን የሚቃርሙ ከብትና ፍየሎች የሚሰማሩበት፤ ያ ሰማያዊ ቀለም ይዞ የአካባቢውን ውበት አድማቂ የነበረ ሐይቅ በደለል ተሞልቶ ወደ ነበር ተቀየረ፤ ለምን ? በሐረማያ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማሕበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕረዚደንትና የሐረማያ ሐይቅ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ይስሃቅ ዩሱፍ።
" ይህ ሃይቅ ላለፉት 80 እና መቶ አመታት ለሐረር ከተማና ለሌሎች ትንንሽ ከተሞች ሐረማያ፣ አወዳይ የውሃ ምንች ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። የሐረር ከተማ የነዋሪው ሕዝብ ብዛት ከዛሬ መቶ ዓመታት በፊት ከነበረው በእጅጉ ጨምሯል። "

ዶክተር ይስሃቅ ዩሱፍ በሐረማያ ዩኑቨርስቲ የምርምርና የማሕበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕረዚደንት
ዶክተር ይስሃቅ ዩሱፍ በሐረማያ ዩኑቨርስቲ የምርምርና የማሕበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕረዚደንትምስል Mesay Teklu/DW


በሐረማያ ሀይቅ ላይ የተጠቃሚው ሕዝብ ቁጥር አለቅጥ መጨመር በሐይቁ ዓቅም መመናመን ላይ አሉታዊ ጫናው እንዲበረታ እንዳደረገው በምርምር ከተጠቀሱ የመድረቁ ችግሮች አንዱ ነው። ዋናው ጉዳይ ግን አለምአቀፍ ችግር የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ለሐይቁ መድረቅና በደለል መሞላት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ተመራማሪው ዶክተር ይስሐቅ ያስረዳሉ።
" ዋናው የምንለው ዓለም አቀፍ እይታ ያለው የአየር ለውጥ ችግር ነው ሐይቁን እንዲደርቅ ያደረገው። ይህ በሒeቁ ላይ ካለው የተጠቃሚ ቁጥር መጨመርና ሐይቁ በደለል የመሞላት ጋር ተያይዘው ሐይቁ ሊያደርቁት ችለዋል።"
ሐይቁ ለመድረቁ በምርምር የተደገፉ ምክንያታዊ ምክንያቶች ቢኖሩም ቅድመ ማስጠንቀቅያዎችን በመስጠትና ጨርሶ ሳይደርቅ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማፍለቅ በኩል በየሚመለከታቸው አካላት በወቅቱ ተገቢ ሚናቸውን አልተወጡም የሚል ወቀሳ በብርቱ ተሰንዝሮባቸው እንደነበር የሚታወስ ነው። 


ሀይቁን የማገገም ሥራዎች
የሐረማያ ሐይቅ መልሶ እንዲያገግምና ቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠብቆ እንዲሄድ ዩኒቨርስቲው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰፋፊ የአካባቢ ጥበቃና መልሶ ግንባታ ስራዎችን አከናውኗል በማከናወንላይም ይገኛል። ከስራዎቹ በጥቂቱ አስመልክተው ዶክተር ይስሃቅ 
" አንዱ የሰራነው ሕብረተሰቡን የማንቃት ሥራ ነው። በዚህ መልኩ ብዙም አልቸገረንም። ምክንያም ሕብረተሰቡ ችግሩን አይቶታልና።እኤአ በ2013 አዲስ ፕሮጀክት ቀረጽን፤ ይህ አዲስ ፕሮጀክት ውሃ መመለሻ ነው። ቢሮ አደራጅተን ዩኒቨርስቲው አንድ የችግኝ ማፍያ ጣቢያ ቢኖረም ለሃይቁ አንድ ተጨማሪ የችግኝ ማፍያ አቋቋምን። የአካባቢው ማሕበረሰብ የማይጠቀምባቸው የተፋሰሱ አካል የሆኑ ከ200 እስከ300 ሄክታር ስፋት ያላቸውን ተራሮችን በመከለል ጥበቃ ተቀጥሮላቸው እንዲለሙ አደረግን። የዩኒቨርስቲው ማሕበረሰብና ሕዝቡ በመሆን በየአመቱ እስከ400,000 ችግኞች እንዲተከሉ አድርገናል።"

የሐረማያ ሐይቅ በአሁኑ ሰአት ወደ ቀድሞ ይዞታው እየተመለሰ ነው
የሐረማያ ሐይቅ በአሁኑ ሰአት ወደ ቀድሞ ይዞታው እየተመለሰ ነውምስል Messay Teklu/DW

እንደቀድሞው የመሆን ተስፋ
ሕብረተሰቡ በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ከሐይቁ ውጭ በየማሳው ጉድጓዶችን በመቆፈር ውሃው ወደ ውስጥ እንዳይሰርግ ፕላስቲክ ተጠቅሞ ውሃ የማቆር ስራዎች እያከናወነ ሲሆን በዚህ ባቆረው ውሃም ዓሳዎችን እያመረተ እንደሚገኝ ዶክተር ይስሃቅ አጫውተውናል።
በሐይቁና በዙሪያው ባሉ ተፋሰሶች በተካሄዱ የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራዎች በአሁኑ ሰአት የሐረማያ ሐይቅ ከቀድሞ ይዞታው 80 በመቶ ያህል እንደተመለሰ ጥናቶች ያመለክታሉ። የሐይቁ የውሃ መጠን በየዓመቱ በነጥብ 2 ሚልዮን ሜትር ኪዩብ እየጨመረ እንደሚገኝ ዶክተር ይስሃቅ አጫውተውናል። በውጤቱም እንደቀድሞው ለአካባቢው ከተሞች የመጠጥ ውሃ ምንጭነቱን መልሶ ተቀዳጅቷል። ጀልባዎች የሚርመሰመሱበትና ዓሶች የሚጠመዱበት፤ በውጤቱም ለበርካታ ነዋሪዎች የገቢ ምንጭነቱን መልሶ ቀጥሏል። የተፈጥሮ ሐብት ሲወድም ቀላል ነው ያሉት ዶክተር ይስሀቅ መልሶ ለማገገም ግን ከባድ እና ጊዜንም የሚጠይቅ በመሆኑ አካባቢያችንን እንንከባከብ መልዕክታቸው ነው።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 

ታምራት ዲንሳ