1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

ልጃገረዶችን የጠለፉና የደፈሩ ተፈረደባቸዉ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 4 2016

በውሳኔው መሠረትም አሳሳቢ አበራ በ 14 ዓመት ጽኑ እሥራት ፣ ዘላለም ደያሳ በ 7 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እሥራት ፣ እንዲሁም አግዳቸው አድማሱ እና በላይ አዳሙ እያንዳንዳቸው በ7 ዓመት ፅኑ እሥራት እንዲቀጡ ሲል ፈርዷል

https://p.dw.com/p/4gv5V
በኮሬ ዞን የሚገኙ የተለያዩ የተፈጥሮ አቀማመች ካላቸዉ አካባቢዎች በከፊል
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መስተዳድር በኮሬ ዞን አስተዳደር ከሚገኙ መንደሮች አንዱምስል Kore Zone communication office

ልጃገረዶችን የጠለፉና የደፈሩ ተፈረደባቸዉ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሬ ዞን የኮርቃ ወረዳ ፍርድ ቤት ልጃገረዶችን ጠልፈዋል፣ አስገድደዉ ደፍረዋልም ያላቸዉን አራት ተከሳሾች ከ7 እስከ 14 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት ቀጣ፡፡የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ቅጣቱ ከተወሰነባቸው መካከል ተደራራቢ የጠለፋና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ይገኝበታል ፡፡አንድ የተጎጂ ቤተሰብ አባል ‘’ በፍርድ ቤቱ የተላለፈው ውሳኔ ተመጣጣኝ አይደለም ‘’ ብለዋል ፡፡የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት እንዳሉት ግን ቅሬታ ያለው አካል ይግባኝ የማለት መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡

 

ጠለፋና አስገድዶ መድፈር የፈጸሙ ተፈረደባቸው

በኮሬ ዞን የጎርካ ወረዳ ፍርድ ቤትበልጃገረዶች ላይ የጠለፋና የአስገድዶ መደፈር ፈጽመዋል  ያላቸውን ተከሳሾች ጉዳይ ላለፉት ሦስት ሳምንታት ሲመለከት ነው የቆየው  ፡፡ ፍርድ ቤቱ አቃቢ ህግ ባቀረበው የክስ መዝገብ መሠረት የሰው ምስክር ማድመጡን ፤ የሀኪም ማስረጃዎችንም መመርመሩን ጠቅሷል ፡፡ በቀረበው ማስረጃ መሠረት ተከሳሾቹን ጥፋተኛ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ ያለው ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸው ከ 7 እስከ 14 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት እንዲቀጡ መወሰኑን ገልጿል ፡፡

ተደራራቢ ጥፋቶች

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ ቅጣቱን ያሳለፈው በጎርካ የተለያዩ መንደሮች ውስጥ ልጃገረዶችን መጥለፋቸው በማስረጃ በመረጋገጡ መሆኑን ገልጿል፡፡  በውሳኔው መሠረትም አሳሳቢ አበራ በ 14 ዓመት ጽኑ እሥራት ፣ ዘላለም ደያሳ በ 7 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እሥራት ፣ እንዲሁም አግዳቸው አድማሱ እና በላይ አዳሙ እያንዳንዳቸው በ7 ዓመት ፅኑ እሥራት እንዲቀጡ ሲል ፈርዷል ፡፡ የፍርድ ውሳኔ ከተላለፈባቸው መካከል አሳሳቢ አበራ የተባለው አንደኛው ተከሳሽ ተደራራቢ የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የጎርካ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ወንድይፍራው ታየ “ ግለሰቡ በተጎጂ ታዳጊዋ ላይ ሁለት የወንጀል ድርጊቶችን ነው ፈጽሞ የተገኘው ፡፡ ከመንገድ ጠልፎ መውሰዱ የመጀመሪያው ሲሆን አስገድዶ በመድፈር ደግሞ ተደራቢ ጥፋትን ፈጽሟል “ ብለዋል ፡፡

የውሳኔው ሚዛናዊነት

በጠለፋ ምክንያትየሴት ልጆች ወጥቶ መመለስ አሳሳቢ በሆነበት የኮሬ ዞን በፍርድ የተሠጠው ውሳኔ በርካቶች አስተማሪነቱ የጎላ ነው እያሉ ነው ፡፡ ያም ሆኖ የተጎጂ ቤተሰቦች ግን ቅጣቱ ልጆቻቸው ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጉዳት አንጻር ሲመዘን ተመጣጣኝ አይደለም እያሉ ነው ፡፡  በተከሳሾቹ ላይ ውሳኔውን ያስተላለፈው የጎርካ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ወንድይፍራው ታየ ግን ፍርዱ የተሰጠው  በቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሠረት ነው ብለዋል ፡፡ በውሳኔው ቅር የተሰኙ የተጎጂ ቤተሰቦችም ሆኑ አቃቢ ህግ ይግባኝ የመጠየቅ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል ፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ኮሬ ዞን በአካባቢው እየተስፋፋ በመጣው የጠለፋ ድርጊት የተነሳ ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መቸገራቸውን በተደጋጋሚ መግለጻቸውን ዶቼ ቬለ ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለስ