1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ለጥፋት የትንቀሳቀሱ» የተባሉ 50 ተጠርጣሪዎች ተያዙ

ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2016

በህቡዕ የተደራጀ የተባለው ቡድን ዋና ማዕከሉን አዲስ አበባ እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ አድርጎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን አስታውቋል። "አንዳንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮችን" በመጠቀም "ተቋማትን መሰብሰቢያ እና ማደራጃ በማድረግ" በድብቅ ሲንቀሳቀስ እንደነበር መረጋገጡን ግብረ ኃይሉ ይጠቅሳል።

https://p.dw.com/p/4dwHR
እስር ቤት-አመላካች ምሥል
እስር ቤት-አመላካች ምሥልምስል picture alliance/dpa/dpa-Zentralbild

«ለጥፋት የትንቀሳቀሱ» የተባሉ 50 ተጠርጣሪዎች ተያዙ

በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ «ሁከት እና ብጥብጥ ለመፈፀም በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ" የተባሉ50 ተጠርጠሪዎችን መያዙን የፌዴራል መንግሥት አስታወቀ።የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ትናንት ባወጣው መግለጫ ተጠርጣሪዎቹን ያሰማራው ቡድን "አዲስ አበባንና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎችን የሁከት፣ የብጥብጥ እና  የሽብር ሴራው ዒላማ አድርጎ ነበር" ብሏል።የፌዴራል ፖሊስ ግን ከጋራ ግብረ ኃይሉ ውጪ በተናጠል ማብራሪያ መስጠት እንደማይችል አስታውቋል።የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ ተጠርጣሪዎች ሥለተያዙበት ሁኔታ ክትትል እንደሚያደርግ አስታዉቋል።

የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ ዝርዝር ይዘት

የሀገር መከላከያ ሠራዊትን፣ የፌዴራል ፖሊስን እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ያጣመረው የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ተጠርጣሪዎችን አሰማርቷል የተባለው ቡድን ቀደም ሲል አማራ ክልልን አሁን ደግሞ አዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎችን  የሁከትና ብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ጥረት ማድረጉን ገልጿል። ይህ በህቡዕ የተደራጀ የተባለው ቡድን ዋና ማዕከሉን አዲስ አበባ እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ አድርጎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን አስታውቋል። ይሄው ቡድን "አንዳንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮችን" በመጠቀም "ተቋማትን መሰብሰቢያ እና ማደራጃ በማድረግ" በድብቅ ሲንቀሳቀስ እንደነበር መረጋገጡን ግብረ ኃይሉ ያሰራጨው መግለጫ ይጠቅሳል።
በጉዳዩ ላይ የጋራ ግብረ ኃይሉ አባል የሆነውን የፌዴራል ፖሊስን ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀናል። የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጅላን አብዲ ፌዴራል ፖሊስ ከጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ ውጪ በተናጠል ማብራሪያ መስጠት እንደማይችል አስታውቀዋል።

50ዎቹ ተጠርጣሪዎች ሁከት ለመቀስቀስና አደጋ ለመጣል አሲረዉ ነበር የተባለዉ አዲስ አበባ ከተማ አካባቢዋ ነዉ።
የአዲስ አበባ ከተማ በክረምት ወቅት በከፊል ስትታይምስል Solomon Muche/DW

ይህንኑ በተመልከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንንም ጠይቀናል። በተቋሙ የሪጅን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ግርማይ እንዲህ በዛ ያለ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተጠርጥረው በፀጥታ አካላት ሲያዙ ኮሚሽኑ ምን እንደሚያደርግ ጠይቀናቸው ምላሽ ሰጥተዋል።


ለጥፋት ተሰማራ የተባለው ኃይል መሪዎች

ቡድን የጋራ ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት 50 ተጠርጣሪዎች ውስጥ ቡድኑን የሚመራው ሰውም እንደሚገኝበት አመልክቷል። በውጪ ሆነው ቡድኑ ያስተበብራሉ የተባሉት ደግሞ ሺህ ዐለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ፣ ሀብታሙ አያሌው እና መሳይ መኮንን የተባሉ ሰዎች እንዲሁም በሀገር ውስጥ በእስክንድር ነጋ፣ በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው በማረሚያ ቤት በሚገኙ በዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ፣ በረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው እና ሌሎችም እንደሚመራ ዘርዝሯል።በኢሰመኮ የሪጅን ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ሰላማዊት ግርማይ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ እስካሁን ቤተሰብ ታሥሮብናል በሚል ለኮሚሽኑ የቀረበ አቤቱታ አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
 

ተጠርጣሪዎቹ ይዘዋቸዉ ነበር የተባሉ ቁሶች

የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ትናንት መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው ዘለግ ያለ መግለጫ "በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም" የተባሉ ኃይሎች ያሰማሯቸው  አባላቱ ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ መቆየቱንም፣ ቦንቦች፣ ተቀጣጣይ ቁሶች፣ የተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች እና ሌሎችም ሰነዶች ጋር መያዛቸውን ዘርዝሯል።

የእስር ቤት አብነት ፎቶ ግራፍ
የእስር ቤት አብነት ፎቶ ግራፍምስል picture-alliance/dpa/D. Naupold

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው ልዩ ስብሰባ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለመንፈቅ ያህል በአማራ ክልል ተደንግጎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲራዘም በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።ከአዋጁ ጋር አብሮ ኃላፊነቱ የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መርማሪ ቦርድ ዐዋጁ በቆየባቸእ ስድስት ወራት 7,196 ተጠርጣሪዎች ተይዘው እንደነበር እና "ከ 5000 በላይ" ያህሉ በተሃድሶ እና ሥልጠና እንዲለቀቁ  መደረጉን በወቅቱ ገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ