ለታዋቂው ድምጻዊና ደራሲ ታምራት አበበ አክብሮት የሰጠው መድረክ በቨርጂኒያ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 22 2016ድምጻዊና ደራሲ ታምራት አበበን የማክበር፣ የማመስገንና የመደገፍ ምሽት በቨርጂኒያ አሜሪካ ተካሄደ። ይሄው የምስጋና ምሽት «የሠራን ማክበር አዲስ ጀግናን ይፈጥራል» በሚል መርህ የተካሄደ ነው። አርቲስት ታምራት ከ34 ዓመታት በላይ በሙዚቃው አለም የቆየ፣ ራሱ ካወጣቸው አልበሞች በተጨማሪ ለበርካታ ድምጻውያን ግጥምና ዜማን ያበረከተ መሆኑ በዚሁ ዝግጅት ላይ ተገልጿል። በምሽቱ አርቲስት ማህሙድ አህመድና ግርማ በየነን ጨምሮ በዲሲ፣ ቨርጂኒያና ሜሪላንድ የሚገኙ አርቲስቶችና የሙያው አድናቂዎች ተገኝተዋል።
ድምጻዊና ደራሲ ታምራት አበበን የማክበር፣ የማመስገንና የመደገፍ ምሽት በቨርጂኒያ ውስጥ ተካሄደ። ይሄው የምስጋና ምሽት የሠራን ማክበር አዲስ ጀግናን ይፈጥራል በሚል መርህ የተካሄደ ነው። አርቲስት ታምራት ከ34 ዓመታት በላይ በሙዚቃው ዓለም የቆየ፣ ራሱ ካወጣቸው አልበሞች በተጨማሪ ለበርካታ ድምጻውያን ግጥምና ዜማን ያበረከተ መሆኑ በዚሁ ዝግጅት ላይ ተገልጿል። በምሽቱ አርቲስት ማህሙድ አህመድና ግርማ በየነን ጨምሮ በዲሲ፣ ቨርጂኒያና ሜሪላንድ የሚገኙ አርቲስቶችና የሙያው አድናቂዎች ተገኝተዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት አንጋፋውን የኪነጥበብ ባለሞያ ኩራባቸው ደነቀንና አርቲስት ጌታቸው እጅጉን በድንገት ማጣታችን ይታወቃል። ጥሎብን የምናደንቃቸው አርቲስቶች ድንገት ሲለዩን የምንደነግጠውን ያህል በሕይወት እያሉ የማክበርና የማመስገን ባህል እንደሰማይ የራቀን ይመስላል።
በትናንትናው ምሽት በቨርጂኒያው የመዓዛ ሬስቶራንት የተሰናዳው ዝግጅትም፣ የሠራን እናመስግን በሚል ርዕስ፣ ይሄንኑ ባህላችንን ለመመለስ እና ድምጻዊና ደራሲ ታምራት አበበን ለማመስገንና ለመደገፍ የተካሄደ ነበር። ድምጻዊና ደራሲ ታምራት በ1965 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ሥራውን ከጀመረ ጀምሮ በሙዚቃው ዘርፍ ጉልህ አስተዋጾ አድርጓል። ሦስት አልበሞችንና ከ40 በላይ ግጥምና ዜማወችን ማህሙድ አህመድ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ቴዎድሮስ ታደሰና፣ ሃመልማል አባተን ጨምሮ ለበርካታ ድምጻውያን ሰጥቷል።
ይሄው ዝግጅት «የሠራን ማክበር፣ አዲስ ጀግናን ይፈጥራል» የሚለው መርህ አንድ አካል እንደሆነ የዝግጅቱ አስተባባሪና የኢትዮጵያን ኪነጥበባዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁነቶችን በመረጃና በማስረጃ አስደግፎ በመሰነድ የሚታወቀው ተወልደ በየነ ገልጿል። አርቲስት ታምራት ሥራወቹ እንዲናገሩለት ከማድረግ ባለፈ ድምጹ የማይሰማ መሆኑን የገለጸው ተወልደ፣ በ1981 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ ከመጣም በኋላ ከሙዚቃው ርቆ ሌላ ትምህርት ተምሮ በሌላ ሞያ እየሠራ ላስ ቬጋስ ውስጥ መኖሩን ጠቁሟል።
ድምጻዊ ማህሙድ አህመድና ግርማ በየነ የምሽቱን በዓል በክብር እንግድነት ተገኝተው አድምቀውታል። አንጋፋው አርቲስት ማህሙድ አህመድ «ተው ልመድ ገላዬ»ን ጨምሮ ግጥምና ዜማዎችን እንደሰጠው አስታውስዋል። የሙዚቃ ኢንደስትሪውን በመደገፍ የሚታወቀው አብረሃም ብዙነህም የአርቲስት ታምራት አበበን ሥራዎች አስታውሷል። ተወልደ በየነ እንደገለጸው፣ ድምጻዊና ደራሲ ታምራት አበበ ህመም ላይ ስለሆነ የሁላችንንም ድጋፍ ይፈልጋል። በዲሲ፣ ቨርጂኒያና ሜሪላንድ የሚገኙ አርቲስቶች በራስና በኢትዮ ባንዶች ታጅበው ሥራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ የሙያው አድናቂዎች ተገኝተዋል።
አበበ ፈለቀ
ሸዋየ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ