1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለረሃብ የተጋለጡ ህጻናት በትግራይ

ዓርብ፣ የካቲት 8 2016

በትግራይ ለረሃብ በተጋለጡ አካባቢዎች በተለይም ህፃናት ለከፋ ሁኔታ እየተጋለጡ ይገኛሉ። በክልሉ አበርገለ የጭላ ወረዳ በሦስት ወራት ብቻ 120 ህፃናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠው ወደ ሆስፒታል ገብተዋል። በተከተሰው ድርቅና ረሃብ ምክንያት በምግብ እጥረት የተጠቁ ህፃናት ቁጥር በሶስት እጥፍ ጨምሯል።

https://p.dw.com/p/4cUVx
ህጻናት ላይ ያንጫበበዉ የረሃብ አደጋ በትግራይ
ህጻናት ላይ ያንጫበበዉ የረሃብ አደጋ በትግራይ ምስል Haileselassie Million/DW

Ber.Tigray_16.02_(Children in Tigray_high risk of famine) - MP3-Stereo

በትግራይ ለረሃብ በተጋለጡ አካባቢዎች በተለይም ህፃናት ለከፋ ሁኔታ እየተጋለጡ ይገኛሉ። በክልሉ አበርገለ የጭላ ወረዳ በሦስት ወራት ብቻ 120 ህፃናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠው ወደ ሆስፒታል ገብተዋል። የሁለት ዓመቱ ህፃን ሀፍቱ እናት የሆነችው ለተዝጊሄር፥ በአካባቢያቸው አበርገለ የጭላ ወረዳ ድርቅ የወለደው ረሃብሲጠና ወደ ልመና የወጣችው ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ ነው። የመጨረሻ ህፃን ልጅዋ ሀፍቱ ሁለት ዓመቱ ቢያልፍም የሰውነት ዕድገቱ እና ክብደቱ ከሚጠበቀው በታች ነው።

የህጻኑ እናት "የህፃን ልጄ ችግር ረሃብ ነው። የምንበላው የደረቀ እንጀራ ነው። ለህፃን አይሆንም። መሬታችን በአብዛኛው በወራሪዎች ቁጥጥር ነው። ባለፈው ክረምት ያለችው መሬታችን አርሰን ነበር። ይሁንና ዝናብ ባለመዝነቡ የበቀለ ነገር የለም። ከጥቅምት ወር ወዲህ በልመና እየተተዳደርኩኝ ነው። ልጄ ሌላ ችግር የለበትም ረሃብ ብቻ ነው" ባይ ናት።

"ልጄ በጣም ሲጎዳ ሆስፒታል ይዤው መጣሁ። ፕላምፕሌት የተባለ ገንቢ ምግብ ሰጡት። እሱ እየተመገበ ይገኛል። በተለይም ለህፃናት ምግብ ቢሰጥ፣ ሕክምና ቢደረግ በጣም ጥሩ ነው" ትላለች የሀብቱ እናት። በየጭላ ሆስፒታል አግኝተን ያነጋገርናት ይህች እናት በአጠቃላይ አራት ልጆች ያልዋት ሲሆን፥ በረሃብ እጅግ መጎዳታ ተነግሯት በሆስፒታል ሕክምና ከሚከታተለው ህፃን ልጅዋ ውጭ ያሉ ሌሎቹ በከተማ እየተዘዋወሩ ለምነው ያገኙት ምግብ ይበላሉ።

ህጻናት ላይ ያንጫበበዉ የረሃብ አደጋ በትግራይ
ህጻናት ላይ ያንጫበበዉ የረሃብ አደጋ በትግራይ ምስል Haileselassie Million/DW

በየጭላ ሆስፒታል የህፃናት ሕክምና ክፍል አስተባባሪ የሆነው ነርስ ዮሴፍ ገብረሚካኤል በአካባቢያቸው በተከተሰው ድርቅና ረሃብ ምክንያት በምግብ እጥረት የተጠቁ ህፃናት ቁጥር በሶስት እጥፍ ማደጉ ይገልፃል። እንደ ዮሴፍ ገለፃ፥ ባለፉት 3 ወራት ብቻ ወደ ጤና ተቋማቸው 120ህፃናት በከፋ የምግብ እጥረት ተጠቅተው መምጣታቸው የሚገልፅ ሲሆን፥ ሆስፒታሉ በቂ አቅም ስለሌለው ሌላች የሚመጡ በርካቶች ማስተናገድ አለመቻሉ ይገልፃል። ዮሴፍ "በአጭር ግዜ ብቻ 120 በማልኒቱርሽን የተጎዱ ህፃናት ተቀብለናል። እነዚህም ቢሆን በቂ ድጋፍ እያገኙ አይደለም። ሌሎች በርካቶች ደግሞ ግብአት ስለሌለን ልንቀበላቸው አልቻልንም" ይላል።

እንደ አበርገለ የጭላ ወረዳ አስተዳደር ገለፃ ካለፈው ወርሀ መስከረም ወዲህ ባለው ግዜ 83 ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሞተዋል። በወረዳዋ ነዋሪ የሆኑት እና የአምስት ልጆች አባት እና ቤተሰብ መሪው እምባየ ገብረስላሴ ረሃቡ በየግዜ እየከፋ ነው ይላሉ። የሕክምና ባለሙያው ዮሴፍ በበኩሉ በተለይም ለህፃናት ትኩረት ያደረገ መፍትሔ ከመንግስት እና እርዳታ ሰጪ ተቋማት ይጠበቃል ባይ ነው።

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በክልሉ የሚገኝ 91 በመቶ ህዝብ ለድርቅ ተጋልጦ እንደሚገኝ አስቀድሞ ገልፃ አፋጣኝ እርዳታ እንዲቀርብ ጥሪ አቅርቧል። በትግራይ ባለው ረሃብ ጉዳይ የፌደራል መንግስቱ እና የክልሉ አስተዳደር የተለያዩ መረጃ ይሰጣሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም የምግብ ድርጅት እና ሌሎች ለጋሽ ተቋማት ለረዥም ግዜ አቋርጠውት የነበረ የምግብ እርዳታ አቅርቦት በቅርቡ በተወሰነ መጠን ማቅረብ መጀመራቸው ተገልጿል።

 

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ